በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምን ተግባራት ተከለከሉ?

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 23፤ 2014 ባካሔደው ስብሰባ ያጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስምንት የተከለከሉ ተግባራት እና ግዴታዎች ይዟል። የኢትዮጵያ መንግስት ይፋ ባደረገው የአዋጁ ዝርዝር መሰረት፤ ሁሉም ሰው የአስቸኳይ ጊዜውን አዋጅ የሚያስፈጽመው አካል “የሚያወጣቸውን መመሪያዎች እና የሚሰጣቸውን ትዕዛዞች የመቀበል ግዴታ” አለበት። 

የአዋጁን የማስፈጸም እና አፈጻጸሙን የመከታተል ኃላፊነት በዋነኝነት የተሰጠው “በመምሪያ ዕዝ” ደረጃ ለተዋቀረ አካል መሆኑን የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የሚመራው ይህ ዕዝ፤ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑ በአዋጁ ተደንግጓል።

ከዛሬ ጀምሮ ሥራ ላይ በዋለው አዋጅ ከተከለከሉ ተግባራት መካከል፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙን እንቅስቃሴ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ዓላማ የሚቃረን፣ የሚቃወም ንግግር በማንኛውም መንገድ ማድረግ ወይም ማሰራጨትን የሚያግደው አንዱ ነው። በአዋጁ መሰረት ለሽብር ቡድኖች ዓላማ መሳካት አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣ የሽብር ቡድኖችን የሚያበረታታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያሸብር ንግግር ማድረግ ወይም በማንኛውም መንገድ ማሰራጨትም በተመሳሳይ መልኩ ተከልክሏል። 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በከለከላቸው ተግባራት ውስጥ የተካተተው ሌላኛው ጉዳይ፤ በየትኛውም መንገድ፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች የገንዘብ፣ የመረጃ የቁስም ሆነ የሞራል ድጋፍ ማድረግን ነው። አዋጁን የሚያስፈጽመው ዕዝ፤ በተዋረድ ውክልና ከሰጣቸው አካላት ፈቃድ ውጪ፤ “ማንኛውንም የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ” እንደማይቻልም ተገልጿል። ከመከላከያ፣ ከፌደራል ፖሊስ ወይም ሌሎች ፈቃድ ከሚሰጣቸው የጸጥታ አካላት ወይም ከእነዚህ አካላት እውቅና እና ፈቃድ ውጭ ማናቸውንም የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ በአዋጁ ተከልክሏል። 

በከተሞች አካባቢ የነዋሪ መታወቂያ፣ የመንጃ ፈቃድ፣ የሰራተኛ መታወቂያ፣ ፓስፖርት ወይም ተመጣጣኝ የሆነ መታወቂያ ሳይዙ መንቀሳቀስም እንዲሁ ተመሳሳይ ክልከላ ተደርጎበታል። የተጠቀሱት ሰነዶች የሌለው ግለሰብ፤ በሁለት ሳምንት ውስጥ በአቅራቢያው በሚገኝ የቀበሌ፣ የወረዳ የጸጥታ እና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ወይም ፖሊስ ጣቢያ በመመዝገብ ጊዜያዊ የመታወቂያ ወረቀት የመያዝ ግዴታም ተጥሏል።   

ማንኛውንም ወሳኝ በሆነ የአገልግሎት ዘርፍም ሆነ በምርት ሂደት ላይ የሥራ ማስተጓጎል ወይም የኢኮኖሚ አሻጥር መፈጸምን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከልክሏል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም ሰበብ በማድረግ፤ “የግል ጥቅም ለማግኘት ስልጣንን አላግባብ መጠቀም፣ ምክንያታዊ የሆነ ጥርጣሬ ሳይኖር ሆን ብሎ ዜጎችን ማሰር ወይም መሰል እርምጃ መውሰድ” መከልከሉም ተገልጿል።  

በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽድቅ የሚጠበቅበት እና ከዛሬ ማክሰኞ ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት የተደነገገ ነው። “አዋጁ በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በምክር ቤቱ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል” ሲሉ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዎን ዛሬ ማክሰኞ ማምሻውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። 

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገጉ ያስፈለገው፤ “በኢትዮጵያ ህልውና፣ ሉዓላዊነት እና አንድነት” ላይ አደጋ በመደቀኑ እንደሆነ ጠቁመዋል። ይህ አደጋ “መደበኛ በሆነው የሕግ ማስከበር ስርዓት እና አካሄድ ብቻ በቁጥጥር ስር ሊውል የሚችል ባለመሆኑ” አዋጁ መደንገጉን ተናግረዋል።

“ጠንከር ባለ፤ በተደራጀ ሁኔታ የጸጥታ እና የደህንነት ተቋማት እንዲሁም ዜጎችም በመተባበር እና በመቀናጀት፤ የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ ይችሉ ዘንድ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እና የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማድረግ የጸደቀ አዋጅ ነው” ሲሉ ዶ/ር ጌዲዎን በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ አስረድተዋል። 

አዋጁ ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት እንደሚቆይ ቢገለጽም፤ “የአደጋው መጠን እና አካባቢያዊ አድማስ እየቀነሰ በሄደ ጊዜ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈጻሚነት ወሰን በዚያው ልክ እየጠበበ ሊሔድ እንደሚችል” የኢትዮጵያ መንግስት ይፋ ያደረገው ማብራሪያ ያሳያል። የድንጋጌው “ተፈጻሚነት በከፊልም ሆነ በሙሉ ቀሪ የሚሆንባቸውን አካባቢዎች” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ የመወሰን ሥልጣን ተሰጥቶታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)