ጄፍሪ ፌልትማን ከሶስት ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ተወያዩ

636

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን በትላንትናው ዕለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ከሶስት ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ ገለጹ።  ልዩ መልዕክተኛው በዛሬው ዕለትም ከሌሎች የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን አግኝተው እንደሚነጋገሩ ገልጸዋል። 

ጄፍሪ ፌልትማን በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው ጦርነት መፍትሔ ለማፈላለግ ወደ አዲስ አበባ የመጡት ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ጥቅምት 24 ነው። የልዩ መልዕክተኛው ጉብኝት በትግራይ ክልል ጦርነት ከተቀሰቀሰበት አንደኛ ዓመት ጋር ተገጣጥሟል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ ኔድ ፕራይስ ትላንት ሐሙስ ምሽት በሰጡት ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ እንዳሉት፤ ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣው ግጭት ተቀባይነት ያለው የመፍትሔ አቅጣጫ ለማፈላለግ ነው። ፌልትማን በትላንቱ ውሏቸው ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር የተገናኙ ሲሆን የኢትዮጵያ ባለስልጣናትንም አግኝተዋል። 

ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልዩ መልዕከተኛ ጋር ትላንት ተገናኝተው ከተወያዩ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት መካከል፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን አንዱ እንደሆኑ ኔድ ፕራይስ ተናግረዋል። ፌልትማን ባለፈው ነሐሴ ወር ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸው ይታወሳል።  

አሜሪካዊው ዲፕሎማት፤ ከአቶ ደመቀ በተጨማሪ ከመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በላይ እና ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ፕራይስ ከባለስልጣናቱ ጋር የተደረገውን ውይይት በደፈናው “ፍሬያማ ነበር” ሲሉ ገልጸውታል።

ፌልትማን በዛሬው ዕለትም ከሌሎች የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ይነጋገራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቃል አቃባዩ ቢናገሩም፤ ማንነታቸውን ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል። ስለ ትላንቱ ውይይት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እስካሁን በይፋ የወጣ መረጃ የለም። አሜሪካ፤ የትግራይ ግጭትን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ አሳሳቢ ላለቻቸው ችግሮች መፍትሔ እንዲያፈላልጉ ፌልትማንን በልዩ መልዕክተኛነት የሾመቻቸው ባለፈው ሚያዝያ ወር ነበር። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)