በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በታህሳስ ወር ሊካሄድ ለነበረው ምርጫ የሚደረገው ዝግጅት ተቋረጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በታህሳስ ወር ሊያካሂድ ለነበረው ምርጫ የሚያደርገውን ዝግጅት ማቋረጡን አስታወቀ። የምርጫው ዝግጅት የተቋረጠው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላው ኢትዮጵያ በመታወጁ ምክንያት መሆኑን ቦርዱ ገልጿል።

በሰኔ 14፤ 2013 በተደረገው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምርጫ የተከናወነው በከፊል ነው። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ውስጥ ባሉ 17 የምርጫ ክልሎች ምርጫ ያልተከናወነው በአካባቢዎቹ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት መሆኑ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

ምርጫ ቦርድ በእነዚህ አካባቢዎች “የሚያስፈልገው የጸጥታ ፍላጎቶች ከተሟሉ” በታህሳስ 21 ምርጫውን ለማከናወን እንደሚችል ገልጾ፤ ወደ ምርጫ ዝግጅት መግባቱን አስታውቆ ነበር። ቦርዱ ባወጣው ጊዜያዊ የምርጫ ሰሌዳ መሰረት፤ ከጥቅምት 10 እስከ ዛሬ ጥቅምት 26 ድረስ ያሉት ቀናት የተመደቡት የምርጫ የጸጥታ እቅድ ለማዘጋጀት ነው። በእነዚሁ ቀናት ምርጫውን ለማስፈጸም የሚረዳ የጋራ የጸጥታ ኮሚቴ እንደሚቋቋም በጊዜ ሰሌዳው ተቀምጧል።

በምርጫ የጊዜ ሰሌዳው ላይ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ከጥቅምት 20 ጀምሮ እንደሚከናወን የተገለጸ ሲሆን ቦርዱም ይህንን ተከትሎ ይፋዊ ማስታወቂያ በማውጣት አመልካቾችን መቀበል ጀምሮ ነበር። የምልመላው ሂደት አንድ ሳምንት እንኳን ሳይሞላው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ጨምሮ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተግባራዊ የሚደረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ፤ የምርጫውን ዝግጅት እንዲስተጓጎል አድርጎታል። 

“የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የተዘጋጀውን አገር አቀፍ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትላንትና ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ማጽደቁን ተከትሎ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የምርጫ ሰሌዳን እና ዝግጅትን ያቋረጠ መሆኑን ለማሳወቅ ይወዳል” ሲል ቦርዱ ዛሬ ሐሙስ ባወጣው መግለጫው አስታውቋል።

ቦርዱ የምርጫ ዝግጅቱን ያቋረጠው ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ በመግለጫው አልጠቀሰም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተደነገገበት ጊዜ አንስቶ ስድስት ወራት ያህል ተፈጻሚ ሆኖ የሚቆይ መሆኑ በአዋጁ ተቀምጧል። አዋጁን ያጸደቀው የተወካዮች ምክር ቤት፤ የስድስት ወር የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት የአዋጁ ተፈጻሚነት “ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ ሊወስን እንደሚችልም” ተደንጓግል። 

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተከለከሉ ተግባራት መካከል  ማንኛውንም የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ይገኝበታል። የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርግ አካል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ በተዋረድ ውክልና ከሰጣቸው አካላት ፈቃድ ማግኘት እንደሚገባው አዋጁ ደንግጓል። 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሊካሄድ የታሰበው ምርጫ በታቀደለት ጊዜ አለመደረጉ፤ እስካሁንም ያልተከናወነውን የክልሉን መንግስት ምስረታ ለተጨማሪ ወራት እንዲዘገይ ያደርገዋል። የክልሉ ምክር ቤት ካሉት 99 መቀመጫዎች ውስጥ መቀመጫዎች ውስጥ ምርጫ የተካሄደው ለ34 ያህሉ ብቻ ነው። ከእነዚህ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ፤ ሃያ ስምንቱን ሲያሸነፍ በስድስቱ በድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ ተወስኖ ነበር። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)