ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ “ማንነትን መሰረት ባደረገ በሚመስል ሁኔታ” እስር እየተፈጸመ መሆኑን ኢሰመኮ ገለጸ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሀገሪቱ ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ “ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ በሚመስል ሁኔታ” ሰዎች እያታሰሩ መሆኑን ገለጸ። ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ ሰዎች ከስራ ቦታቸው፣ ከመኖሪያ ቤታቸው እና ከመንገድ ላይ ጭምር ተይዘው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል።

የመብት ተሟጋቹ ተቋም ትላንት እሁድ ምሽት ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ በመዲናይቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ከጥቅምት 23 ጀምሮ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች በከተማዋ ባሉ የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ተይዘው እንደሚገኙ ገልጿል። እስሩ “ህጻናት ልጆች ያሏቸውን እናቶች እና አረጋውያንን ጭምር ያካተተ” መሆኑን በመግለጫው የጠቀሰው ኢሰመኮ፤ ይህ ሁኔታ “እጅግ እንደሚያሳስበው” አመልክቷል። 

በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች “የቤተሰብ ጥየቃ፣ ልብስ እና ስንቅ ማቀበል” ተከልክሏል ያለው ኮሚሽኑ፤ ይህ የእስረኞች አያያዝ ሂደትም “ያሳስበኛል” ብሏል። የህግ አስከባሪ አካላት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጠረጠሯውን ሰዎች ይዘው የማቆየት ስልጣን እንደተሰጣቸው ያስታወሰው ኢሰመኮ፤ ሆኖም የህግ አስከባሪ አካላት አዋጁን እና መመሪያዎቹን በስራ ላይ ሲያውሉ ሊያከብሯቸው የሚገባቸው የሰብዓዊ መብት መርሆዎች እንዳሉ ጠቁሟል።

እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ፤ የህግ አስከባሪ አካላት ሊያከብሯቸው ይገባሉ የተባሉት መርሆዎች “የህጋዊነት፣ የጥብቅ አስፈላጊነትና ተመጣጣኝነት እንዲሁም ከመድልዎ ነጻ መሆን” የሚሉት ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም የህግ አስከባሪ አካላት “በማንኛውም ሁኔታ ሊገደቡ የማይችሉ ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር እና የማስከበር ተግባራቶቻቸውንም በከፍተኛ የሙያ ስነምግባር በመመራት የማከናወን ኃላፊነት አለባቸው” ሲል አሳስቧል።

ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 25 በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በሚያወጣቸው መመሪያዎች፣ በሚወስናቸው ውሳኔዎች እና በሚወስዳቸው እርምጃዎች በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 93 (4)(ሐ) መሰረት ሊታገዱ የማይችሉ የሕገ መንግስት ድንጋጌዎችን እና መብቶችን ማክበር ይኖርበታል” ሲል ደንጓል። 

በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት መሰረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማይገደቡ መብቶች በሚል የተጠቀሱት የኢ-ሰብዓዊ አያያዝ መከልከል፣ የእኩልነት መብት እና የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች መብት ናቸው። የኢ-ሰብዓዊ አያያዝን የሚከለክለው የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 18፤ “ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢ-ሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው” ሲል ይደነግጋል።

ኢሰመኮ በትላንት መግለጫው አጽንኦት የሰጠው ሌላው ጉዳይ፤ በእስር ላይ የሚገኙ አረጋውያንን፣ እናቶችን፣ የህክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸውን እና ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን አያያዝ የተመለከተ ነው። ኮሚሽኑ እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች በተመለከተ “ፈጣንና ልዩ የማጣራት አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል” ሲል ምክረ ሃሳብ አቅርቧል። 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ከሁለት ቀናት በኋላ ይፋ በተደረገው መመሪያ መሰረት፤ ለእንደዚህ አይነት መሰል ጉዳዮች መፍትሄ የመስጠት ኃላፊነት ያለበት አካል “የፌዴራል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የክትትል ኮሚቴ” ነው። ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነው ይህ ኮሚቴ፤ “ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም ጋር በተገናኘ የሚኖሩ የህዝብ ቅሬታዎች ምላሽ እንዲያገኙ ክትትል እና ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት” በመመሪያው ተሰጥቶታል። 

ዘጠኝ አባላት ያሉት የፌዴራል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የክትትል ኮሚቴን በሰብሳቢነት የሚመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ናቸው። በኮሚቴው ውስጥ ባለፈው ወር በሚኒስትርነት የተሾሙ ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም በአባልነት ተካትተዋል። ሶስቱ ሚኒስትሮች ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ በለጠ ሞላ እና አቶ ቀጄላ መርዳሳ ናቸው። 

በተወካዮች ምክር ቤት በተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አፈጻጸምን በሚመረምረው ቦርድ ውስጥም እንደዚሁ የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ በአባልነት ተመርጠዋል። ሰባት አባላት ያሉት ይህ ቦርድ “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚወሰዱት እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢ-ሰብዓዊ አለመሆናቸውን የመቆጣጠርና የመከታተል” ስልጣን አለው። 

ቦርዱ “ማናቸውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ ኢ-ሰብዓዊ መሆኑን ሲያምንበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት እርምጃውን እንዲያስተካክል ሀሳብ የመስጠት” ስልጣን እንዳለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ይደነግጋል። ከመርማሪ ቦርዱ እና ከክትትል ኮሚቴው በተጨማሪ፤ ኢሰመኮም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የሰብዓዊ መብቶችን ሁኔታ የመከታተል ስልጣን አለኝ ብሏል።

ኮሚሽኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ በሚደረግባቸው ጊዜያት የክትትል ተግባራትን የሚያከናውነው፤ በማቋቋሚያ አዋጁ በተሰጠው ስልጣን መሰረት መሆኑን በትላንትናው መግለጫው ጠቅሷል። በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ የሚሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ ተፈጻሚ ሆኖ የሚቆየው ለስድስት ወራት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)