የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት፤ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ እያካሄደ ነው

• የተመድ የጸጥታው ምክር ቤትም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ዛሬ ይወያያል

በተስፋለም ወልደየስ

የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት በሰሜን ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለመምከር ለዛሬ የጠራው አስቸኳይ ስብሰባ እየተካሄደ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ለሌላ ጊዜ አስተላልፎት የነበረው ኢትዮጵያን የተመለከተ ውይይትም፤ በዛሬው ዕለት ይካሄዳል ተብሏል።

የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት የዛሬውን ስብሰባ የጠራው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ባሉ “ወቅታዊ ለውጦች” ምክንያት እንደሆነ በአፍሪካ ህብረት እና በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ጥናት እና ምርምር የሚያደርገው “አማኒ አፍሪካ” የተሰኘው ድርጅት አስታውቋል። ምክር ቤቱ በዛሬው አስቸኳይ ስብሰባው፤ የህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሌሴንጎ አባሳንጆ በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚያቀርቡትን ገለጻ እንደሚያዳምጥ ድርጅቱ ገልጿል።

የህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይነት ሹመታቸውን በነሐሴ ወር አጋማሽ የተቀበሉት አባሳንጆ፤ ስለ ተሰጣቸው ሃላፊነት እና ሃላፊነታቸውን ለማስፈጸም ስለወጠኗቸው እቅዶች ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጥቅምት 18፤ 2014 በምክር ቤቱ ተገኝተው ማብራሪያ መስጠታቸውን “አማኒ አፍሪካ” አስታውሷል። በዛሬው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ደግሞ ኦባሳንጆ የሰሜን ኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተ፤ በኢትዮጵያም ሆነ በቀጠናው ካሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ስላካሄዷቸው ውይይቶች እና እስካሁን ስላደረጓቸው እንቅስቃሴዎች ያብራራሉ ተብሎ ይጠበቃል ብሏል።   

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት በትላንትናው ዕለት ወደ ትግራይ ክልል መቐለ ተጉዘው ከህወሓት ሊቀመንበር ከዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል ጋር መነጋገራቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን በምስል ጭምር አስደግፈው ዘግበዋል። ዶ/ር ደብረጽዮን የኢትዮጵያን ቀውስ በተመለከተ የትግራይን አቋም ለአቦሳንጆ እንደገለጹላቸው የህወሓት ቃል አቃባይ ጌታቸው ረዳ አስታውቀዋል። ቃል አቃባዩ ውይይቱን “በጣም ፍሬያማ” ሲሉ ጠርተውታል። 

የአህጉሪቱ የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት አባላት ከውይይቶቹ ባሻገር፤ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የአፍሪካ ህብረት ያለውን “ዕይታ” ማድመጥ እንደሚፈልጉ “አማኒ አፍሪካ” ጠቁሟል። የኢትዮጵያ ሁኔታ አሁን ካለበት በባሰ እንዳያሽቆለቁል ህብረቱ የሚያደርገውን ጥረት፤ ምክር ቤቱ የበለጠ ሊደግፍ የሚችልበትን ሁኔታ በተመለከተም በዛሬው ስብሰባ ማብራሪያ እንዲቀርብላቸው እንደሚሹም ድርጅቱ አመልክቷል። 

በአፍሪካ አህጉር ያሉ ግጭቶችን የመከላከል እና ግጭቶች ከተከሰቱም በኋላ የመቆጣጠርና መፍትሄ የማበጀት ዓላማ ያለው የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት 15 አባል ሀገራት አሉት። ሀገራት በየሁለት እና ሶስት ዓመት በሚደረግ ምርጫ በሚተካኩበት በዚህ ምክር ቤት ውስጥ፤ ኢትዮጵያ አንዷ አባል ነች። እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን በመወከል የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ጅቡቲ እና ኬንያ ናቸው። 

የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት በትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በመደበኛ አጀንዳነት ይዞ ሲወያይ የዛሬው የመጀመሪያ እንደሚሆን የምክር ቤቱን ስብሰባዎችን በቅርበት የሚከታተለው “አማኒ አፍሪካ” ገልጿል። ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ በመሪዎች ደረጃ በቪዲዮ ኮንፍረንስ በተካሄደ የምክር ቤቱ ጉባኤ፤ የሰሜን ኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተዘጋጀው መግለጫ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም መደበኛ ውይይት አለመደረጉን ድርጅቱ አስታውሷል። 

የህብረቱ ምክር ቤት ከዛሬው አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ አቋሙን በመግለጫ ያሳውቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ “አማኒ አፍሪካ” ገልጿል። ምክር ቤቱ በሰሜን ኢትዮጵያ በርካታ ቦታዎችን እያካለለ እና እየተባበሰ በመጣው ውጊያ ላይ ያለውን ስጋት በመግለጫው እንደሚያካትት ድርጅቱ ግምቱን አስቀምጧል። 

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት በቅርቡ ባወጡት መግለጫ ያነሱትን “ግጭቶችን የማቆም ጥሪ” እና “የፖለቲካ ሂደቶችን የመጀመር አስፈላጊነት” ምክር ቤቱ በመግለጫው ያስተጋባዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም “አማኒ አፍሪካ” ጠቁሟል። ለዚህ ሂደት ተፈጻሚነት የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሌሴንጎ ኦባሳንጆ ላላቸው ሚና፤ ምክር ቤቱ ድጋፉን ሊገልጽ እንደሚችልም ድርጅቱ በትንታኔው ላይ አመልክቷል።

ባለፈው አርብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ይዞ የነበረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፤ ስብሰባውን ለሌላ ጊዜ ካስተላለፈ በኋላ ባወጣው መግለጫም ኦባሳንጆ ለሚያደርጉት የሽምግልና ጥረት ድጋፉን ገልጿል። ለሌላ ጊዜ የተላለፈው የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ በዛሬው ዕለት እንደሚካሄድ ከምክር ቤቱ የወጡ ይፋዊ መረጃዎች አሳይተዋል።

በዛሬው ስብሰባ ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ዋና ጸሀፊ የሆኑት ጋናዊቷ ማርታ አማ አካያ ፖቤ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሏል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይህን ሁኔታ ለመቀልበስ እያደረገ ያለውን ጥረት አስመልክቶ ገለጻ እንደሚያደርጉም ከምክር ቤቱ የተገኘ መረጃ ጠቁሟል። 

ረዳት ዋና ጸሀፊዋ በዛሬው ስብሰባ ላይ የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ከዚህ ቀደም ያቀረቧቸውን ጥሪዎች ያነሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም መረጃው ጠቁሟል። ጉተሬዝ ግጭቶች እንዲቆሙ፣ የሰብዓዊ ድጋፎች ያለ ገደብ ማቅረብ እንዲቻል እና ሁሉን አካታች ብሔራዊ ውይይት እንዲካሄድ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ዋና ጸሀፊው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ጥቅምት 24 ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፤ ተመድ ለውይይት የሚያበረታቱ ሁኔታዎችን የማገዝ ሀሳብ እንዳለው በትዊተር ገጻቸው አሳውቀው ነበር። የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ይህ የዋና ጸሀፊው ሀሳብ ተቀባይነት አግኝቶ እንደው ምላሹን የማድመጥ ፍላጎት እንዳላቸው የምክር ቤቱን አጀንዳዎች የሚተነትነው ድረ ገጽ አመልክቷል። 

የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እንዲወያይ ሀሳቡን ያቀረቡ አባል ሀገራት ሜክሲኮ፣ አየርላንድ እና “ኤ3 ፕላስ ዋን” በሚል የቡድን ስም የሚጠሩ አራት ሀገራት ናቸው። በዚህ ቡድን ስር የተካተቱት ኬንያ፣ ኒጀር፣ ቱኒዝያ እንዲሁም ሴንት ቪንሰንት እና ግሬናዲንስ ናቸው። ሜክሲኮ በፈረንጆቹ ህዳር ወር የጸጥታው ምክር ቤትን በሊቀመንበርነት የምትመራ ስትሆን አየርላንድ ደግሞ በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰ አንስቶ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የጸጥታው ምክር ቤት እንዲሰበሰብ እና እርምጃ እንዲወስድ ተደጋጋሚ ግፊት ስታደርግ የቆየች ናት። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)