የዘንድሮው የጣና ፎረም ጉባኤ “በወቅታዊ ሁኔታ” ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ

በሃሚድ አወል

በአፍሪካ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው ዓመታዊው “የጣና ፎረም” ጉባኤ “በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ” ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ። የዘንድሮው ጉባኤ ሲራዘም የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። 

የጣና ፎረም የአማራ ክልል መዲና በሆነችው የባህርዳር ከተማ ከህዳር 16 ቀን 19 ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት ነበር። የዘንድሮው ጉባኤ “የደህንነት ስጋቶችን መቆጣጠር፤ የምንፈልጋት አፍሪካን ጽናት ለመገንባት” በሚል የመወያያ ርዕስ ስር እንዲካሄድ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፤ ስብሰባውን በታቀደለት ጊዜ ማካሄድ እንደማይቻል ተገልጿል።

የ“ጣና ፎረም” የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ዮናስ ብርሃኔ ጉባኤው የተራዘመው “በወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ ነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።   የሀገር መሪዎችን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ይሳተፉበታል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ይህ ጉባኤ መቼ እንደሚካሄድ ገና እንዳልተወሰነም ተናግረዋል።

በዘንድሮው ፎረም ላይ ይገኛሉ ከተባሉ ርዕሳነ ብሔር መካከል የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አንዷ ናቸው። የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴንጎ ኦባሳንጆ እና የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝም በጉባኤው ይሳተፋሉ ከተባሉ ተጋባዥ እንግዶች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

በዚህ ዓመት የሚካሄደው የ“ጣና ፎረም” ጉባኤ፤ የአስረኛ ዓመት ክብረ በዓል በመሆኑ ለየት ባለ መልኩ ለማካሄድ ታስቦ እንደነበር አቶ ዮናስ ይናገራሉ። ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን የተካሄዱ የ“ጣና ፎረም” ስምንት ጉባኤዎችን ያስተናገደችው ባህርዳር፤ የክብረ በዓሉን ዝግጅት እንድታሰናዳ ተመርጣ እንደነበር ይገልጻሉ። 

ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ዘጠነኛውን የ“ጣና ፎረም” በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ማስተናገድ ሳትችል የቀረችው ባህርዳር፤ የዘንድሮውን ስብሰባም በከተማይቱ በሚገኘው አቫንቲ ብሉ ናይል ሆቴል ለማካሄድ ተሰናድታ ነበር። የኮሮና ወረርሽኝ ያለፈው ዓመት ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ከማስገደዱ በተጨማሪ፤ የተሳታፊዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ አድርጎት እንደነበር የ“ጣና ፎረም” የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩት እንግዶች ውጭ ሌሎቹ [ፎረሙን የተካፈሉት] በቪዲዮ ነበር” ሲሉ ዘጠነኛው የጣና ፎረም የተካሄደበት ሁኔታ ያስታውሳሉ አቶ ዮናስ።

በህዳር ወር አጋማሽ ይካሄዳል ተብሎ በነበረው የ“ጣና ፎረም” ጉባኤ ላይ በቁጥር በርካታ የሆኑ እንግዶች በአካል ባህርዳር ተገኝተው ይታደማሉ የሚል ግምት እንደነበርም አቶ ዮናስ ጠቁመዋል። በስፍራው ተገኝተው ፎረሙን መታደም የማይችሉ ሰዎች ደግሞ በበይነ መረብ መካፈል እንዲችሉ ለማድረግ ታስቦ እንደነበርም አስረድተዋል። 

የ“ጣና ፎረም”ን በዚህ ዓመት ለማካሄድ በመጀመሪያ ታቅዶ የነበረው በያዝነው የጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ነበር። ፎረሙ ወደ ህዳር አጋማሽ እንዲራዘም የተደረገው “ከአስተናጋጇ ሀገር ኢትዮጵያ ተከታታይ የመንግስት ተግባራት ጋር በመደራረቡ መሆኑን” ጣና ፎረም ባለፈው ዓመት ጷጉሜ መጨረሻ ላይ በድረ ገጹ አስታውቆ ነበር።

ፎረሙ ወደ ህዳር ተሸጋግሮ የነበረው በባህርዳር ከተማ “የካቢኔ ስብሰባ ይካሄድ ስለነበር ነው” ሲሉ አቶ ዮናስ ለመራዘሙ ምክንያት ነው ያሉትን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የህዳሩ ጉባኤ በሳምንቱ መጨረሻ በታተሙ ጋዜጦች ላይ ጭምር ማስታወቂያው የተነገረ ቢሆንም፤ በተባለው ጊዜ እንደማይካሄድ አዘጋጆቹ አረጋግጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)