በሃሚድ አወል
ከሃዋሳ ከተማ እምብርት ራቅ ብሎ በስተምስራቅ አቅጣጫ በሚገኝ የተንጣለለ ቅጽር ግቢ ውስጥ የተንሰራፋው የደቡብ ክልል ምክር ቤት በባንዲራ እና መፈክሮች በተጻፉባቸው ባነሮች አሸብርቋል። የክልሉ ምክር ቤት የምስረታ ጉባኤውን ባካሄደ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ለጠራው አስቸኳይ ስብሰባ፤ አባላት እና እንግዶች ወደ ግቢው በመግባት ላይ ናቸው። አብዛኞቹ የምክር ቤቱ አባላት በባህላዊ አልባሳት ተውበዋል።
ከሶስት መቶ ሰዎች በላይ የማስተናገድ አቅም ያለው የደቡብ ክልል ምክር ቤት አዳራሽም፤ በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ፊኛዎች እንዲሁም በፌደራሉ እና የክልሉ ባንዲራዎች አጊጧል። ምክር ቤቱ በዚያን ቀን አስቸኳይ ጉባኤ እንዲጠራ ያስደረገው ጉዳይ፤ በምክር ቤቱ ታሪክ ከዚህ ቀደም የተከናወነው አንድ ጊዜ ብቻ መሆኑ ነው ዕለቱን እንዲህ ልዩ ያደረገው።
የምክር ቤቱ የዕለቱ ዋነኛ አጀንዳ፤ በደቡብ ክልል እና በስሩ የሚገኙ አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ ባቋቋሙት አዲስ ክልል መካከል፤ የስልጣን ርክክብ ማድረግ ነው። ከዚህ ቀደም ይህን አካሄድ ተከትሎ የራሱን ክልል የመሰረተው፤ እስከ ሰኔ 2012 ድረስ በደቡብ ክልል ስር የነበረው የሲዳማ ዞን ብቻ ነው። የያኔውን የሲዳማ ዞን በመወከል የስልጣን ርክክቡን ያደረጉት የዞኑ አፈ ጉባኤ ነበሩ።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ጥቅምት 24፤ 2014 በተካሄደው የደቡብ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ላይ አዲሱን ክልል በመወከል የስልጣን ርክክቡን የሚያደርገው አካል ግን እስከ ስብሰባው ዕለት በግልጽ አልታወቀም ነበር። የዚህ ጥያቄ ምላሽ በመድረክ የታየው የጉባኤው መገባደጃ ሲቃረብ ነው። የደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ የስልጣን ርክክብ የሚያደርጉትን ሰዎች ሲጠሩ፤ በአዳራሹ ጀርባ የተቀመጡ አራት ሴቶች እና ሁለት ወንዶች ከመቀመጫቸው ተነሱ።
ስድስቱም አፈ ጉባኤዎች ናቸው። አፈ ጉባኤዎቹ አስራ አንደኛውን የኢትዮጵያ ክልል የመሰረቱት የካፋ፣ ቤንች ሸኮ፣ ሸካ፣ ዳውሮ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳዎች ምክር ቤቶችን የሚመሩ ናቸው። ደመቅ ባለ ጭብጨባ ታጅበው ወደ መድረክ የወጡት አፈ ጉባኤዎቹ፤ የመጡባቸው አካባቢዎች ከደቡብ ክልል በይፋ ተለያይተው፤ የአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አካል መሆናቸውን የሚያበስረውን ሰነድ በጋራ ተረክበዋል።
የሁለቱ ክልሎች ፍቺ እንዴት ይካሄዳል?
የአስራ አንደኛው ክልል የስልጣን ርክክብ ስነ ስርዓት በግማሽ ሰዓት ቢጠናቀቅም፤ በአዲሱ እና በነባሩ የደቡብ ክልል መካከል የሚኖረው አስተዳደራዊ እና ህጋዊ ጉዳዮች በተመለከተ በምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ የተነሱ ጉዳዮች ግን ለሁለት ሰዓት ያህል አነጋግረዋል። የምክር ቤቱ አባላት በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ሃሳቦች ከመሰንዘራቸው በፊት፤ የደቡብ ክልል ያቀረበውን ዝርዝር የውሳኔ ሃሳብ (ሞሽን) አድምጠዋል።
አራት ክፍሎች ያሉት ሞሽኑ በሁለቱ ክልሎች መካከል የሚኖረውን የሽግግር እና የስልጣን ርክክብ፣ የሃብት እና የዕዳ ክፍፍል ስርዓት፣ የሰው ኃይል ድልድል እንዲሁም ድርድር እና አለመግባባቶች ስለሚፈቱበት ስርዓት ያትታል። ሞሽኑ ካሉት 17 አንቀጾች መካከል የሃብት እና የዕዳ ክፍፍልን የሚመለከተው አንቀጽ ሰፊው እና በደቡብ ክልል ምክር ቤትም በርካታ ጥያቄ እና አስተያየቶች የቀረቡበት ነው።
አስራ ሁለት ንዑስ አንቀጾች ያሉት ይህ አንቀጽ፤ በሁለቱ ክልሎች መካከል የሚኖረው የሃብት እና ዕዳ ክፍፍል በመንግስት አሰራር የሚፈጸም እንደሚሆን ያስቀምጣል። የሃብት እና ዕዳ ክፍፍል ከመደረጉ በፊት በቅድሚያ በደቡብ ክልል መንግስት ባለቤትነት የሚገኙ የንብረቶች ምዝገባ፣ የሃብትና ንብረት ልየታ እና የዋጋ ትመና እንደሚከናወን ያስቀምጣል።
በውሳኔ ሃሳቡ መሰረት፤ በሁለቱ ክልሎች መካከል የሃብት ክፍፍል የሚከናወነው የህዝብ ቁጥርን ወይም ቀመርን ወይም አስተዳደራዊ ወሰንን መሰረት በማድረግ በድርድር ይሆናል። የዕዳ ክፍፍልን በተመለከተ በነባሩ የደቡብ ክልል የሚገኙ እዳዎች፤ አዲሱ ክልል ስራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በቀመር እንደሚከፋፈል በውሳኔ ሃሳቡ ሰፍሯል።
በሃብት ክፍፍል ወቅት ያልተገኘ ቋሚ ንብረት እና ዕዳ ጉዳይም በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ትኩረት ተሰጥቶታል። በሃብት ክፍፍል ወቅት ያልተገኙ ንብረቶች ከክፍፍሉ በኋላ መገኘታቸው ሲረጋገጥ፤ በውሳኔ ሃሳቡ መሰረት ክፍፍል እንደሚደረግ ተቀምጧል። በዚህም መሰረት በአዲሱ እና በነባሩ ክልሎች መካከል በ2014 በስራ ላይ ያሉ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በሁለቱ ክልሎች የጋራ ስምምነት እንደሚፈጸም ተቀምጧል።
ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ምን አይነት መልክ ይኖረዋል የሚለውን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው “በክፍፍሉ ቀመር መሰረት የሚከፋፈልበትን ቀመር አዘጋጅተናል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። በስራ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን ዕጣ ፈንታ የሚያትተው የውሳኔ ሃሳቡ አንቀጽ፤ “የጋራ የሆኑ ልዩ ልዩ ክልላዊ ፕሮግራሞች እስከ 2014 መጨረሻ ድረስ በጋራ ክንውናቸው የሚቀጥል ሆኖ አካባቢያዊ የሆኑ ፕሮግራሞች አዲሱ ክልል ከተደራጀበት ጊዜ ጀምሮ በአዲሱ ክልል ተጠቃሎ የሚከናወን ይሆናል” ሲል በተጨማሪነት ያብራራል ።
በአዲሱ እና በነባሩ የደቡብ ክልል መካከል የሚከናወነው የሃብት እና የዕዳ ክፍፍል “በምን ያህል ጊዜ ይጠናቀቃል?” የሚለው ከምክር ቤቱ አባላት ጎልቶ የተሰማው ጥያቄ ነው። “ብዙ ሂደቶችን የሚያልፍ ይሆናል። በዚህ ቀን ያልቃል ብለን መገደብ አንችልም” ያሉት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር “በፍጥነት እንዲካሄድ እንፈልጋለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የሲዳማ እና የደቡብ ክልሎች ተሞክሮ ምን ይመስላል?
ከአንድ አመት በፊት አስረኛ ክልል በመሆን ከወጣው የሲዳማ ክልል ተሞክሮ የሚታየው ግን የሃብት እና ዕዳ ክፍፍሉ ቀላል ስራ እንዳልሆነ ነው። በሰኔ 2012 ከደቡብ ክልል ጋር የስልጣን ርክክብ ያደረገው የሲዳማ ክልል፤ ከነባሩ የደቡብ ክልል ጋር ከተሸከርካሪዎች በስተቀር የሃብት ክፍፍል አላደረገም። አስረኛው የሲዳማ ክልል እና የደቡብ ክልል እስካሁን የንብረት ክፍፍል አለማድረጋቸው በምክር ቤቱ ጉባኤ ላይም ተነስቷል።
የሲዳማ ክልል ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፊሊጶስ ናሆም “የተለየ የሃብት ክፍፍል አልተደረገም” ሲሉ የጉዳዩን እውነትነት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። አቶ ፊሊጶስ አዲሱ የሲዳማ ክልል በሚዋቀርበት ጊዜ አንገብጋቢ የነበረው የተሸከርካሪ ጉዳይ በመሆኑ ምክንያት የተሸከርካሪዎች ክፍፍል በአፋጣኝ መከናወኑን ያስረዳሉ።
በሲዳማ እና በደቡብ ክልል መካከል የሃብት ክፍፍሉ አለመጠናቀቁ፤ ነባሩ የደቡብ ክልል አሁን ያለው ንብረት ለሶስት እንዲከፈል ያደርገዋል። በደቡብ ክልል ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ በጸደቀው የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 15/ 2014 መሰረት፤ ለሲዳማ ክልል ተጠናቀቅው ከተላለፉት ሃብት እና ዕዳዎች ውጭ ያሉ ያልተጠናቀቁ የጋራ ሀብት እና ዕዳ ክፍፍል የደቡብ፣ የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በጋራ በተገኙበት ይከናወናል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሃብት እና ዕዳ ክፍፍልን በተመለከተ በምስረታ አንድ ዓመት ከሚቀድመው የሲዳማ ክልል ተሞክሮ ወስዷል። የክልሉ አደራጅ ኮሚቴ ጸሃፊ አቶ ምትኩ ታምሩ ክልሉ ከተመሰረተ በኋላ “የወዲያው ስራ የሚሆነው የተሽከርካሪ እና የበጀት ክፍፍል ማድረግ ነው” ሲሉ የአዲሱ ክልል የመጀመሪያ የቤት ስራ ምን እንደሚሆን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
ቋሚ ንብረቶችን በተመለከተ፤ “የራሳችንን ቲም አደራጅተን መረጃዎች እየተሰበሰቡ ነበር” የሚሉት አቶ ምትኩ፤ በደቡብ ክልል መንግስት ባለቤትነት ስር ያሉ ቋሚ ንብረቶች የመለየት ስራ መጀመሩን ያብራራሉ። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከተደራጀ፤ የክልል መንግስትም ከተዋቀረ በኋላ የመጀመሪያው የሚሆነው ስራ ከነባሩ የደቡብ ክልል ጋር ያለውን የሃብት እና ዕዳ ክፍፍል ማድረግ ነው ሲሉም አጽንኦት ይሰጣሉ።
አዲሱን ክልል ማደራጀት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ከሲዳማ ክልል ጋር ሲነጻጸር በአጭር ጊዜ ወደ ምስረታ የገባው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ ከአደረጃጀት ጋር የተያያዙ ያልተጠናቀቁ የቤት ስራዎች አሉት። ክልሉን የማደራጀት ስራ በዋነኛነት ያረፈው በደቡብ ክልል በተዋቀረው አደራጅ ኮሚቴ ላይ ነው። በየካቲት 2013 የተቋቋመው አደራጅ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ ማስረሻ በላቸው የኮሚቴው ቀጣይ ስራ ክልሉን ማደራጀት እና የክልሉን መንግስት ማዋቀር እንደሆነ ይናገራሉ።
በአደራጅ ኮሚቴው ስር የተደራጀው የህዝበ ውሳኔ አስተባባሪ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት፤ አዲሱን ክልል እውን ያደረገው ህዝበ ውሳኔ ከመካሄዱ አስቀድሞም ቢሆን የዝግጅት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። ከእነዚህ ስራዎች መካከል ዋነኛው የክልሉን ህገ መንግስት እና ሌሎች የህግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ነው።
የደቡብ ምዕራብ ህዝበ ውሳኔ በተደጋጋሚ መራዘም ለአብይ ኮሚቴውም ሆነ ለህዝበ ውሳኔው ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የእፎይታ ጊዜ ሰጥቷል። ለአምስት ወራት ያህል እጅግ በተጓተተ መንገድ ሲከናወን የነበረው የህገ መንግስት እና ሌሎች የህግ ማዕቀፎች ዝግጅት አሁን ከሞላ ጎደል ተጠናቅቋል። መሰረታዊ የሚባሉት እና የክልሉን ስያሜ፣ ሰንደቅ ዓላማ፣ የስራ ቋንቋ የሚወስኑት የህገ መንግስቱ ክፍሎችም ተጠናቀው በህዝብ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ከህገ መንግስቱ ጋር በተያያዘ የቀረው ስራ በአብይ ኮሚቴው ታይቶ ለአዲሱ ክልል ምክር ቤት ለውይይት በሚቀርብበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የህዝበ ውሳኔ አስተባባሪ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ በድሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ቀጣዩ ሂደት የህገ መንግስቱ ረቂቅ፤ የክልሉ ህገ መንግስት ሆኖ እንዲጸድቅ አዲስ ለሚዋቀረው የክልሉ ምክር ቤት ማቅረብ መሆኑን የአደራጅ ኮሚቴው አባላት ያስረዳሉ።
የክልሉን ህገ መንግስት ከማርቀቅ ባለፈ በአዲሱ ክልል ስራ ላይ የሚውሉ ከሃያ በላይ አዋጆች በአደራጅ ኮሚቴው ተዘጋጅተዋል እንደ አቶ ማስረሻ ገለጻ። “[አዋጆቹ] ወደ ስራ ስንገባ ሳንገራገጭ ወዲያው መንግስት እንድንመሰርት የሚያስችሉ ናቸው” ሲሉ አዋጆቹ የሚኖራቸውን ፋይዳ ያብራራሉ።
የአደራጅ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጸጋዬ ማሞ በበኩላቸው፤ አዋጆቹ አዲሱ ክልል ሲመሰረት የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል አደረጃጀት እና የአሰራር ጥያቄዎችን የሚመልሱ ናቸው ይላሉ። ከአዋጆቹ መካከል “አዲስ የሚሰረተው ክልል ምክር ቤት ምን ያህል መቀመጫዎች ይኖሩታል?” የሚለውን የሚወስነው ይገኝበታል።
አዲሱን ክልል በጋራ የመሰረቱት የካፋ፣ ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ ምዕራብ ኦሞ እና ሸካ ዞኖችን እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳን በመወከል የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል የነበሩት 52 ተወካዮች ናቸው። እነዚህ የነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባላት፤ አዲሱ ክልል ሲደራጅ በቀጥታ የክልሉ ምክር ቤት አባላት እንደሚሆኑ የአብይ ኮሚቴ ጸሃፊው አቶ ምትኩ ያስረዳሉ።
ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ላለው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 52 የምክር ቤት መቀመጫ ቁጥር አነስተኛ መሆኑን የአብይ ኮሚቴው እንዲሁም የህዝበ ውሳኔ አስተባባሪ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አባላት ይስማማሉ። አቶ ጸጋዬ ማሞ የምክር ቤት አባላት ብዛትን በተመለከተ፤ በአዲሱ ህገ መንግስት መፍትሄ ለመስጠት እንደተሞከረ ይገልጻሉ።
የክልሉ አደራጅ ኮሚቴ ጸሃፊ አቶ ምትኩ ታምሩ በበኩላቸው፤ የክልሉን ምክር ቤት አባላት ቁጥር ለመጨመር የዞን ምክር ቤቶች አባላት ወደ ክልል ምክር ቤት እንዲገቡ ሊደረግ እንደሚችል ጠቁመዋል። “የምክር ቤቱ መቀመጫ ምን ያህል ይሆናል?” የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ “ከ150 እስከ 200 ሊሆን ይችላል” ሲሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።
የአዲሱ ክልል ተጨማሪ ፈተናዎች
ከህዝበ ውሳኔው መካሄድ እና መጽደቅ፣ ከስልጣን ርክክቡ እንዲሁም ከህዝብ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት በኋላ አዲሱን ክልል ሊፈትኑት የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች አሉ። የክልሉ አደራጅ ኮሚቴዎች በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት የሚያዋቅሩትን ክልል የበጀት ጉዳይ ሊፈትነው እንደሚችል ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ። ክልሉ አዲስ እንደመሆኑ “ለምስረታ እና ለአጠቃላይ ስራ ከፍተኛ በጀት ያስፈልገዋል” የሚሉት አቶ ጸጋዬ ማሞ፤ “አሁን ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ይህን ፍላጎት ለማሟላት አስቻይ አይደለም” ሲሉ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት አዲሱን ክልል በተዘዋዋሪ እንደሚፈትነው ይገልጻሉ።
አዲሱን ክልል ከሚመሰርቱት ዞኖች አንዱ የሆነው የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማንም ይህንኑ ሀሳብ ይጋራሉ። “አዲስ የሚመሰረተው ክልል የኢትዮጵያ አንድ ክፍል ነው። ኢትዮጵያ ያላትን ችግሮች በሙሉ ይጋራል” ሲሉ በተመሳሳይ የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ለአዲሱ ክልልም ፈተና መሆኑ እንደማይቀር ይናገራሉ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስልጣን ርክክብ የተደረገው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተጀመረ በዓመቱ ነው። ርክክቡ በተደረገበት ዕለትም የጦርነቱ ድባብ በደቡብ ክልል ምክር ቤት ይስተዋል ነበር። የስልጣን ርክክቡ የሚደረግበት ጉባኤ ከመጀመሩ በፊት ዕለቱን በማስመልከት የጧፍ ማብራት ስነ ስርዓት ተከናውኗል። በምክር ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የህወሓት ኃይሎችን የሚያወግዙ ባነሮችም ተሰቅለው ታይተዋል። የምዕራብ ኦሞ ዞን አፈ ጉባኤ አቶ ቢልልኝ ወልደሰንበት ከርክክቡ በኋላ ባደረጉት ንግግርም የህወሓት ኃይሎች ጉዳይ ተደጋግሞ ተነስቷል።
በ13 ብሔሮች እና ስድስት አስተዳደራዊ መዋቅሮች የሚመሰረተውን ክልል፤ ከበጀት አኳያ የሚፈትነው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ብቻ አይደለም። ከክልሉ ምስረታ በኋላ ሊፈጠሩ የሚችሉ አዳዲስ የአደረጃጀት ጥያቄዎችም የአዲሱን ክልል በጀት ሊያዛቡት ይችላሉ የሚል ስጋት አለ። እነዚህን ጥያቄዎች ለመመመለስ የሚደረጉት ጥረቶች፤ “አስተዳደራዊ ወጪውን እየለጠጡት የህዝቦች የልማት ጥያቄ ተገቢውን ትኩረት ላያገኝ ይችላል” ይላሉ ስጋቱን የሚጋሩት አቶ ጸጋዬ።
የክልል ማዕከልነትም ሌላው ፈታኝ ሊሆን የሚችል ጉዳይ ነው። የክልሉ የህገ መንግስት ረቂቅ ለህዝብ ውይይት በቀረበበት ወቅት፤ “ክልሉ ከአንድ በላይ ማዕከላት ይኖሩታል” ከማለት ውጭ ማዕከላቱ ምን ያህል እንደሚሆኑ አሊያም ለማዕከልነት የታጩት ከተሞች የትኞቹ እንደሆኑ የገለጸው ነገር የለም። የህገ መንግስቱ ረቂቅ እነዚህን ጉዳዮች ችላ ማለቱ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ ፈጥሯል።
የክልል ማዕከልን በተመለከተ፤ በአዲሱ ክልል የሚገኙ ከተሞች ተለይተው ጥናት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ አደራጅ ኮሚቴ ጸሃፊ አቶ ምትኩ ይናገራሉ። ሆኖም ጥናቱ ከክልሉ መንግስት ምስረታ በፊት ላይጠናቀቅ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አልሸሸጉም። የክልል ማዕከል ለመምረጥ የሚደረገው ጥናት በመጓተቱ ምክንያትም የክልሉ የምስረታ ይፋዊ ስነ ስርዓት የሚከናወነው በጊዜያዊነት በሚመረጥ ከተማ እንደሚሆን አስታውቀዋል። የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ከተጠናቀቀ ከቀናት በኋላ የወጣ መረጃ እንዳመለከተው፤ የአዲሱን ክልል የምስረታ በዓል የምታስተናግደው የካፋ ዞን ዋና ከተማ ቦንጋ ናት። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)