ለመንግስት ባለስልጣናት ተብለው በ200 ሚሊዮን ብር የተገነቡት ቪላዎች፤ በድጋሚ ጨረታ ገዢ ሳያገኙ ቀሩ

በሃሚድ አወል

ለከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት መኖሪያነት የተገነቡ ስድስት ቪላ ቤቶችን ለመሸጥ፤ ለሁለት ጊዜ ያህል ጨረታ ቢወጣም ገዢ አለመገኘቱን የፌደራል መንግስት ህንጻ ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡት ቪላ ቤቶቹ፤ 200 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ ተደርጎባቸዋል ተብሏል። 

ገዢ ያጡት የመኖሪያ ቤቶች የተገነቡት “ከፍተኛ የሀገር መሪዎች አገልግሎታቸውን ጨርሰው በክብር ከመደበኛ ስራቸው ሲሸኙ፤ ለእነሱ መኖሪያ ይሆናሉ” ተብለው እንደነበር የፌደራል መንግስት ህንጻ ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ፈጠነ ጌታሁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። “ቤቶቹ ውስጥ ይገባሉ ተብሎ ታሳቢ የሚደረገው፤ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር [የነበሩ] ናቸው” ብለዋል። 

ግንባታቸው ከአራት ዓመት በፊት የተጠናቀቀው እነዚህ ቪላ ቤቶች፤ ለሽያጭ እንዲቀርቡ የተደረገው በሁለት ምክንያቶች መሆኑን ምክትል ስራ አስኪያጁ ይናገራሉ። አቶ ፈጠነ የሚያነሱት የመጀመሪያው ምክንያት መኖሪያ ቤቶቹ የሚገኙበት አካባቢ ከከተማ ወጣ ያለ መሆኑ ነው። ስድስቱ ቪላ ቤቶች የተገነቡት በየካ ክፍለ ከተማ፤ ሲኤምሲ አደባባይ አካባቢ ከጊፍት ሪል ስቴት መኖሪያ ቤቶች ጀርባ ነው። 

ሁለተኛው ምክንያት በመኖሪያ ቤቶቹ ይኖሩባቸዋል ተብለው ከነበሩት የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች እና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ደህንነት ጋር የተያያዘ ነው። ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶቹ ግንባታቸው በተከናወነበት አካባቢ፤ ሌሎች የመኖሪያ ቤቶች መገንባታቸው “የደህንነት ስጋት ፈጥሯል” ይላሉ አቶ ፈጠነ። 

“እኛ ግንባታውን በምንጀምርበት ወቅት አካባቢው ላይ ምንም አይነት የግንባታ እንቅስቃሴ አልነበረም” የሚሉት አቶ ፈጠነ፤ የቤቶቹ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ አካባቢው በጨረታ በመሸጡ ሌሎች ግንባታዎች ተጀምረዋል ሲሉ ያስረዳሉ። በዚህም ምክንያት “ከደህንነት ስጋት አንጻር ከፍተኛ መሪዎች ከሚኖሩባቸው ይልቅ ቤቶቹ ተሸጠው ገንዘቡ ለመንግስት ገቢ ቢደረግ ይሻላል” ተብሎ በመወሰኑ ቤቶቹ ለሽያጭ መቅረባቸውን ያብራራሉ።

የፌደራል መንግስት ቪላ ቤቶቹን ለመጀመሪያ ጊዜ ለጨረታ ያቀረበው በጷጉሜ 2012 ነበር። በወቅቱ ጨረታው ለአንድ ወር ያህል ክፍት ሆኖ የቆየ ሲሆን በተወዳዳሪዎች ጥያቄ መሰረት ለሁለት ሳምንት ያህል ተራዝሟል። በዚህ ጨረታ፤ 36 ተጫራቾች የጨረታ ሰነድ ቢገዙም “አንዳቸውም የወሰዱት የጨረታ ሰነድ ላይ የሚገዙበትን ዋጋ ሞልተው አልመለሱም” ሲሉ አቶ ፈጠነ ገልጸዋል። 

የመጀመሪያው ጨረታ ከወጣ አንድ ዓመት በኋላ፤ በመስከረም ወር መጨረሻ ቪላ ቤቶቹ በድጋሚ ለሽያጭ የቀረቡ ቢሆንም ተመሳሳይ ውጤት ተከስቷል። ስድስት ተጫራቾች የጨረታ ሰነድ ቢወስዱም፤ ቤቶቹን የሚገዙበትን ዋጋ አለማቅረባቸውን አቶ ፈጠነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። መስከረም 29፤ 2014 የወጣው ጨረታ የዋጋ ማስገቢያ ጊዜ የተጠናቀቀው ከሁለት ቀን በፊት ባለፈው ሰኞ ነበር።  

ቤቶቹን ገዢ እንዲያጡ ያደረጋቸው፤ የጨረታ መነሻ ዋጋቸው ከፍተኛነት ሳይሆን እንደማይቀር ምክትል ስራ አስኪያጁ ይገምታሉ። “ስድስቱም ቤቶች ዋጋቸው ከፍ ብሎ ሊሆን ይችላል” ይላሉ። ቪላ ቤቶቹ እያንዳንዳቸው እንዳረፉበት ቦታ ስፋት ከ271 ሚሊዮን እስከ 295 ሚሊዮን ብር የጨረታ መነሻ ዋጋ ወጥቶላቸዋል።

ግንባታቸው በ2007 የተጀመረው የስድስቱ ቪላዎች አጠቃላይ ወጪ 156 ብር ሚሊዮን ብር ገደማ ነበር። በአካባቢው ላሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፣ ለምድረ ግቢ እና አጥር ስራዎች ደግሞ መንግስት እስከ 50 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል። የቪላ ቤቶቹ ዋጋ የተተመነው “በተሰሩበት ሳይሆን አሁን ሪል ስቴቶች ሊሸጡ በሚችሉበት ዋጋ ነው” ያላሉ አቶ ፈጠነ። 

የዋጋ ትመናውን ለማድረግ ኮሚቴ ተቋቁሞ የገበያ ጥናት መደረጉን ምክትል ስራ አስኪያጁ ያስረዳሉ። የቤቶቹ አቀማመጥ፣ እያንዳንዳቸው ቤቶች የራሳቸው ግቢ ያላቸው መሆኑ እና አጠቃላይ ለቤቶቹ ግንባታ ስራ ላይ የዋሉ ግብዓቶች በዋጋ ትመናው ወቅት ከግምት ውስጥ መግባታቸውንም ያብራራሉ።  

በፌደራል መንግስት ህንጻ ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ባለቤትነት የተሰሩት እና በአንድ ቅጽር ግቢ የሚገኙት መኖሪያ ቤቶቹ ግንባታቸው የተከናወነው በተክለብርሃን አምባዬ የኮንስትራክሽን ድርጅት ነው። የግንባታዎቹ አማካሪ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን ድርጅት ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)