አከራዮች፤ የተከራዮቻቸውን ማንነት በሳምንት ውስጥ ለፖሊስ እንዲያስመዝግቡ ታዘዘ

ማንኛውም ቤት አከራይ የተከራይን ማንነት የሚገልጽ ሙሉ መረጃ፤ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በአቅራቢያው በሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ እንዲያስመዘገብ የአስቸኳይ ጊዜ ዕዝ ትዕዛዝ ሰጠ። በትዕዛዙ መሰረት ምዝገባውን የማያከናውኑ አካላት ላይ አስፈላጊው ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ አስተላልፏል። 

ዕዙ ዛሬ ረቡዕ ህዳር 1 ምሽት ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው ትዕዛዙ የተላለፈው “የጸጥታ ኃይሎች ለሕዝቡ ደኅንነት ሥጋት የሚሆኑትን ለመመንጠር ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲያግዝ” ነው። “የጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ እንቅስቃሴ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌዎችን በማስፈጸም ባለፉት ቀናት አኩሪ ውጤቶችን አስመዝግቧል” ያለው ዕዙ፤ ይህንን ተከትሎ “ሕገ ወጦች” ያላቸው አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች መያዛቸውን አስታውቋል።

“ይህ ያስደነገጠው  ጠላት የጸጥታ አካላትን መልካም ስም ለማጥፋት፣ ለማሸማቀቅና ሥራቸውን በሙሉ አቅም እንዳይሠሩ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ  ይገኛል” ሲልም ዕዙ በዛሬው መግለጫው አመልክቷል። ከዚህ ጎን ለጎን “በአጋጣሚው ለመጠቀም የሚፈልጉ ጥቂት የጸጥታ አካላት መኖራቸውን” አረጋግጬያለሁ ብሏል። በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የሚመራው ዕዙ “በእነዚህ አካላት ላይ፤ በጠራ መረጃ ላይ በመመሥረት የማያዳግም ርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ተሰጥቷል” ሲልም በመግለጫው ጠቅሷል። 

አስቸኳይ ጊዜ ዕዙ በዛሬ መግለጫው ከዘረዘራቸው ሶስት ትዕዛዛት ውስጥ የመጨረሻው የገንዘብ ዝውውርን የተመለከተ ነው። “ሕገወጥ ግለሰቦች ብሔራዊ ባንክ ካወጣቸው ደንቦችና የአፈጻጸም መመሪያዎች እንዲሁም ከባንኮች ሕጋዊ አሠራር ውጭ፤ በተጭበረበረ መንገድ የገንዘብ ዝውውር እያካሄዱ መሆኑ ተደርሶበታል” ያለው ዕዙ፤ ለዚህም በጊዜው ተገቢው እርምጃ እንደተወሰደ ጠቁሟል። 

ቀደም ብለው ከወጡ ሕጎችና መመሪያዎች ውጭ ሲሰሩ በሚገኙት ባንኮች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ መታዘዙንም ዕዙ ገልጿል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሠረት በማድረግ እርምጃውን የሚወስደው አካል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደሚሆንም በመግለጫው አመልክቷል። እርምጃው የሚወሰደውም ከሕግ አስፈጻሚ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሆነም ጠቅሷል። ማንኛውም የተጭበረበረ የገንዘብ ማዘዋወሪያ ሰነድ ይዘው በተገኙ ላይ፤ “ከወትሮው በተለየ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ” ትዕዛዙን መተላለፉንም ዕዙ ጨምሮ ገልጿል። 

የአስቸኳይ ጊዜ ዕዙ ሶስቱን ትዕዛዞች ያስተላለፈው፤ አዋጁ ከወጣበት ጀምሮ ያለውን ሀገራዊ ሁኔታና የአዋጁን አፈጻጸም ከገመገመ በኋላ መሆኑን አስታውቋል። ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጥቅምት 23፤ 2014 በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት፤ የአዋጁን አፈጻጸም የመከታተል እና በበላይነት የመምራት ስልጣን የተሰጠው ለዕዙ ነው። ዕዙ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)