አሜሪካ በኤርትራውያን ባለስልጣናት እና ተቋማት ላይ ማዕቀብ ጣለች

አሜሪካ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት፤ በኤርትራ አራት ተቋማት እና ሁለት ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ ጣለች። የአሜሪካ ግምጃ ቤት ዛሬ አርብ የወሰደው ይህ እርምጃ፤ “የኢትዮጵያን መረጋጋት እና አንድነትን ላናጋው ቀውስ እና ግጭት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ኤርትራውያን ተዋናዮች ላይ ያነጣጠረ“ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

በማዕቀቡ ከተካተቱት መካከል የኤርትራ ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ (PFDJ) እንዲሁም የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት ይገኙበታል። የኤርትራ ብሔራዊ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አብርሃ ካሳ ነማርያም እና የገዢው ፓርቲ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ሐጎስ ገብረሕይወት ወልደኪዳንም ማዕቀብ የተጣለባቸው ባለስልጣናት ሆነዋል።

ማዕቀብ ከተጣለባቸው የኤርትራ ባለስልጣናት ውስጥ የገዢው ፓርቲ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ሐጎስ ገብረሕይወት ወልደኪዳን ይገኙበታል

በአሜሪካ ግምጃ ቤት የውጭ ሃብት ቁጥጥር ቢሮ (OFAC) ዛሬ ይፋ በተደረገው መግለጫ መሠረት፤ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪው አቶ ሐጎስ በዋና ስራ አስፈጻሚነት በሚመሩት “ሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽን” [ፎቶ] ላይም የአሜሪካ መንግስት ማዕቀብ ጥሏል። ከ27 አመታት ገደማ በፊት የተመሠረተው እና የገዢው ፓርቲ የንግድ ተቋማትን በበላይነት የሚያስተዳድረው “ህድሪ ትረስት” የተባለው ድርጅትም የማዕቀቡ ሰለባ ሆኗል። ሁለቱ ተቋማት በአሜሪካ የሚገኝ ጥሪታቸውን ከማንቀሳቀስ እንደታገዱ የውጭ ሃብት ቁጥጥር ቢሮ አስታውቋል።

የዛሬው እርምጃ፤ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ማዕቀብ እንዲጣል ባለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ ባስተላለፉት ውሳኔ መሰረት ተግባራዊ መደረጉን የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ገልጸዋል። የሚጣለው ማዕቀብ ትኩረቱን የሚያደርገው “በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በማራዘም፤ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን በማስተጓጎል እንዲሁም የተኩስ አቁም እንዳይደረግ እንቅፋት በመፍጠር ተጠያቂ ወይም ተባባሪ” በሆኑ ወገኖች ላይ እንደሚሆን በወቅቱ ተገልጾ ነበር። የመስከረሙ የባይደን ውሳኔ “ከድርድር ይልቅ ግጭትን የመረጡትን” ወገኖች “ተጠያቂ” ለማድረግ የሚያስችል ስልጣን ለአገሪቱ ግምጃ ቤት የሰጠ ነው። 

በፕሬዝዳንታዊው ትዕዛዝ  መሰረት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት፣ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የአማራ ክልል መስተዳድር ማዕቀብ ሊጣልባቸው እንደሚችል ባለፈው መስከረም ተገልጿል። ብሊንከን በዛሬው መግለጫቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት የአፍሪካ ህብረት ልዩ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በጀመሩት የማሸማገል ጥረት ተጠቅመው፤ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ጦርነቱን ለማቆም እንዲደራደሩ ጥሪ አቅርበዋል። 

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “እነዚህ ውይይቶች መሻሻል የሚያሳዩ ከሆነ ጊዜ እና ቦታ ለመስጠት፤ አሁን ከኢትዮጵያ መንግስት እና ከህወሓት ጎን የተሰለፉ አካላት ላይ ማዕቀብ አልጣልንም” ብለዋል። በተጀመሩት ውይይቶች የሚሳተፉ ወገኖች ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ከተሳናቸው ግን ከማዕቀብ እንደማያመልጡ አስጠንቅቀዋል። አሜሪካ፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓትን ጨምሮ በሌሎችም አካላት ላይ “ተጨማሪ ማዕቀቦች ለመጣል ዝግጁ ነች” ሲሉ ብሊንከን ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ በሚገኘው ውጊያ ምክንያት አሜሪካ በኤርትራ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ ስትጥል የዛሬው የመጀመሪያው አይደለም። አሜሪካ በዓለም ዙሪያ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የምትከሳቸውን ተጠያቂ የምታደርግበትን “ግሎባል ማግኔትስኪ አክት” የተባለ ድንጋጌ ተጠቅማ፤ የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ ማዕቀብ መጣሏን ባለፈው ነሐሴ 2013 ዓ.ም አስታውቃለች።

ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ትሰጥ የነበረውን ዕርዳታ መከልከሏም ይታወሳል። ሀገሪቱ ስማቸው ባልተገለጸ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይም የቪዛ ዕቀባ መጣሏን ይፋ አድርጋ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)