• ኮሚሽኑ በክልሉ የተፈጸሙ ጥሰቶች የጦር ወንጀሎች ስለመሆናቸው አመላካች ሁኔታዎች አሉ ብሏል
በሃሚድ አወል
በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሳቢያ በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ 184 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። የሕወሓት ታጣቂዎች በቁጥጥራቸው ስር በገቡ የክልሉ ከተሞች እና ገጠራማ አካባቢዎች ሲቪል ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውን እና ማቁሰላቸውን ማረጋገጡን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ኢሰመኮ ይህን ያለው የሕወሓት ኃይሎች ፈጽመዋቸዋል በተባሉ የሰብአዊ መብት እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶችን በተመለከተ ያደረገውን ምርመራ ሪፖርት ዛሬ ቅዳሜ ህዳር 4፤ 2014 ይፋ ሲያደርግ ነው። ኮሚሽኑ በሪፖርቱ እንደገለጸው በአማራ ክልል የተፈጸሙ ጥሰቶች “የጦር ወንጀሎች ስለመሆናቸው አመላካች ሁኔታዎች አሉ”።
ከሰኔ 21፤ 2013 እስከ ነሐሴ 22፤ 2013 ያለውን ጊዜ የሚሸፍነው የኮሚሽኑ ምርመራ፤ በአማራ ክልል የሚገኙትን የደቡብ ጎንደር እና የሰሜን ወሎ ዞኖችን እንዳካተተ ሪፖርቱ አመልክቷል። ምርመራው ደብረ ታቦር፣ ሃራ፣ ወልድያ፣ ቆቦ፣ ራያ ቆቦ፣ ራያ አላማጣ እና ማይጨው ከተሞችን አዳርሷል ተብሏል።
የምርመራ ቡድኑ ጦርነት በነበረባቸው ሁሉም አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ መረጃ ማሰባሰብ አለመቻሉን ኢሰመኮ ገልጿል። መረጃው በተሰበሰበበት ወቅት፤ በሰሜን ጎንደር እና በዋግ ኽምራ ዞኖች እንዲሁም በሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ ከደብረ ዘቢጥ እስከ ጋሸና ባለው መስመር ያሉ ከተሞች የጦርነት ቀጠና የነበሩ በመሆኑ በእነዚህ አካባቢዎች ምርመራ ለማከናወን አለመቻሉን አስታውቋል።
በዚህም ምክንያት “የሟቾች እና የተጎጂዎች ቁጥር በዚህ ምርመራ ከተገለጸው በእጅጉ ከፍ ሊል እንደሚችል ይገመታል” ሲል በጦርነቱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከዚህም ሊያሻቅብ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል። ኮሚሽኑ ከሰው ህይወት መጥፋት በተጨማሪ “በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት እና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል” ብሏል።
የመብት ተሟጋቹ ተቋም ለደረሰው የሰው ህይወት መጥፋት እንዲሁም ለአካል እና የስነ ልቦና ጉዳት የህወሓት ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርጓል። ወደ ከተሞች ከባድ መሳሪያ ተኩሰዋል ሲል አማጽያኑን የሚከስሰው ኮሚሽኑ፤ “በሲቪል ሰዎች መኖሪያ ቤቶች እና ቅጥር ግቢዎች ውስጥ ምሽግ በመቆፈር እና ከባድ መሳሪያዎችን በመተኮስ ሲቪል ዜጎችን በአፀፋ ለሚተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች ጥቃት አጋልጠዋል” ሲል በሪፖርቱ ዘርዝሯል።
የመከላከያ ሰራዊት በከባድ መሳሪያዎች ያደርጋቸው የነበሩ የአጸፋ ምላሾች በሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ኢሰመኮ በሪፖርቱ ጠቅሷል። የሕወሓት ታጣቂዎች፤ ሲቪል ሰዎች የሚኖሩባቸው መንደሮች ውስጥ ሆነው የሚፈፅሙበትን ጥቃት ለመከላከል እና ለማጥቃት፤ የመከላከያ ሰራዊት “ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀሙ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞትና አካል ጉዳት ደርሷል” ሲል ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ አካላት የተተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች የሰው ህይወት እና አካል ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን እንዲሁም በሲቪል መሰረተ ልማቶች፣ በመኖሪያ ቤቶች፣ በሆስፒታሎች፣ በእምነት ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሳቸው መረጋገጡን ኢሰመኮ በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። ለዚህም በደቡብ ጎንደር ዞን ስር ባሉት የደብረ ታቦር ከተማ እንዲሁም በፋርጣ ወረዳ ጋሳይ ከተማ እና ሳህርና ቀበሌ ላይ የደረሱ ጉዳቶችን በፎቶግራፍ አስደግፎ አሳይቷል።
ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ፤ የሕወሓት ኃይሎች በቁጥጥር ስራቸው በነበሩ የአማራ ክልል ከተሞች እና የገጠር ስፍራዎች ሁሉ ሰፊ የሆነ ዘረፋ እና የንብረት ውድመት “ሆን ብለው” መፈጸማቸው መረጋገጡንም አትቷል። ኮሚሽኑ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የደረሱ የንብረት ውድመቶችን የሚያሳዩ በርከት ያሉ ፎቶግራፎችንም በሪፖርቱ አያይዞ አቅርቧል።
በአማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ በተሰራጨው የኮሚሽኑ ሪፖርት፤ በጦርነቱ የተፈናቀሉ ሰዎች ጉዳይም ትኩረት አግኝቷል። “ጦርነቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሁሉ ከፍተኛ የሰዎች መፈናቀል ተከስቷል” የሚለው ሪፖርቱ፤ ኮሚሽኑ ምርመራውን ባደረገበት ወቅት እንኳ ከሰሜን ወሎ፣ ደቡባዊ ትግራይ እና ከአፋር ክልል የተፈናቀሉ 183,404 ሰዎች በደቡብ ወሎ ዞን ከተሞች እንደነበር ጠቅሷል። ኮሚሽኑ ከተፈናቃዮች እና የመንግስት አካላት ባሰባሰበው መረጃ፤ ከንጽህና መስጫ እና የመመገቢያ ቁሳቁሶች በተጨማሪ “በዓለም አቀፍ የሰብአዊ ድጋፍ አቅራቢ ድርጅቶች የተደረገ ድጋፍ አልነበረም” ብሏል።
ኢሰመኮ በሪፖርቱ ማጠቃለያ ለሶስት አካላት የምክረ ሃሳቦችን ለግሷል። በጦርነቱ ተሳታፊ ለሆኑ ኃይሎች ባቀረበው ምክረ ሃሳብ፤ ሰብአዊ መብቶችን እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግን በማክበር ሲቪል ሰዎችን፣ የሲቪል መሰረተ ልማቶችን ሁሉ ከጉዳት እና ከዘረፋ እንዲጠብቁ አሳስቧል። የፌደራል እና የአማራ ክልል መንግስታት በበኩላቸው በጦርነቱ የተጎዱ ሰዎችን የማቋቋም ስራ እንዲከናወን፣ ለተፈናቃዮች አስፈላጊው የሰብዓዊ ድጋፎች እንዲያቀርቡ እና በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ አስፈላጊ አገልግሎቶች እንዲሟሉ ጥሪ አቅርቧል።
በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ አካላት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት እና የሰብዓዊነት ህግ ጥሰቶችንን በተመለከተ ወንጀል ምርመራ እንዲደረግ እና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በደቡብ ጎንደር እና በሰሜን ወሎ ዞኖች በሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊዎች የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተመለከተ የተደረገው ምርመራ ሪፖርት ግኝቶች፤ በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በአፋጣኝ ማስቆም እንደሚገባ የሚያመላክት ነው” ብለዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ፤ በአማራ እና አፋር ክልሎች ተጨማሪ ምርመራዎችን እያካሄደ መሆኑን በዛሬው ሪፖርት ላይ ጠቁሟል። ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሰፊ የጾታዊ ጥቃት መፈጻማቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች መኖራቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)