ፖሊስ በአሃዱ ሬዲዮ ዜና አርታኢ ላይ የጠየቀው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ

10

በሃሚድ አወል

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ይግባኝ ሰሚ ችሎት፤ በአሃዱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ዜና አርታኢ ክብሮም ወርቁ ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። ችሎቱ በዛሬ ማክሰኞ ውሎው፤ የስር ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ አጽንቷል።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ባለፈው ሳምንት አርብ ህዳር 3 በዋለው ችሎት፤ ጋዜጠኛው በ15 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቅ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር። ለተጠርጣሪው የተጠየቀው የዋስትና ገንዘብ ክፍያ ውሳኔው በተላለፈበት ዕለት ቢከፈልም አርታኢው ሳይፈታ ቀርቷል። 

የጋዜጠኛው አባት አቶ ወርቁ አብርሃ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ ልጃቸው ባለፈው አርብ ያልተለቀቀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን “ይግባኝ ስለምንጠይቅ አንፈታውም” በማለቱ ነው። በዚህም ምክንያት፤ ፖሊስ ፍርድ ቤት የጻፈውን የመፈቻ ትዕዛዝም “አልቀበልም” እንዳለ አቶ ወርቁ ጨምረው ገልጸዋል። 

መርማሪ ፖሊስ በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር መሰኘቱን በመግለጽ የይግባኝ አቤቱታ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ያቀረበው፤ ከሁለት ቀን በኋላ ትላንት ሰኞ ህዳር 6፤ 2014 ነበር። ፖሊስ በትላንትናው ዕለት ተጠርጣሪውን ከያዘበት ቀን ጀምሮ አከናወንኩ ያላቸውን ተግባራት ለፍርድ ቤቱ በቃል አስረድቷል። በዚህም መሰረት ፖሊስ የተጠርጣሪውን የሂሳብ እንቅስቃሴ ለማወቅ ለ18 ባንኮች እንዲሁም ለብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ደብዳቤ መጻፉን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል። 

የይግባኝ ሰሚ ችሎቱም፤ መርማሪ ፖሊስ አከናወንኳቸው ያላቸው ተግባራት በትክክል መፈጸማቸውን ለማረጋገጥ የምርመራ መዝገቡ እንዲቀርብለት ለዛሬ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር። “የምርመራ መዝገቡን ማመሳከር ካልተቻለ፤ ውሳኔው ተመሳሳይ ነው የሚሆነው” ሲል ችሎቱ የምርመራ መዝገቡን መቅረብ አስፈላጊነትን  አጽንኦት ሰጥቷል። 

በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ዛሬ ማከሰኞ ህዳር 7፤ 2014 ለዋለው ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቧል። የምርመራ መዝገቡን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ “ምርመራው ከዚህ በፊት በነበረበት ደረጃ ላይ ነው ያለው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም ፖሊስ በይግባኝ አቤቱታው የጠየቀውን የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜን ጉዳይ ተመልክቷል። 

ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ባለ አንድ ገጽ የይግባኝ አቤቱታ ቀጣይ ቀጠሮ የሚጠይቅባቸውን ምክንያቶች አብራርቶ ነበር። መርማሪ ፖሊስ፤ ለ18 ባንኮች እንዲሁም ለብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የጻፋቸው ደብዳቤዎች ምላሽ እስከሚደርስ ለመጠባበቅ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በመጀመሪያ ምክንያትነት በአቤቱታው ጠቅሷል።  

በሁለተኛነት ምክንያትነት በፖሊስ የተነሳው “ያልተያዙ ግብረ አበሮችን ተከታትሎ ለመያዝ” ተጨማሪ ቀናት የሚያስፈልጉ መሆናቸው ነው። የምስክሮችን ቃል ለመቀበል እንዲሁም ተጨማሪ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች ለማሰባሰብ እንዲሁ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ፖሊስ በአቤቱታው አንስቷል። ተጠርጣሪው በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ በዋስትና ቢወጣ “ምስክሮችን በገንዘብ ሊደልልብኝ እና ማስረጃዎችን ሊያበላሽብኝ ይችላል” ያለው ፖሊስ፤ በዚህ ምክንያት የጋዜጠኛው የዋስትና መብት እንዳይጠበቅ በይግባኝ አቤቱታው ጠይቋል። 

ፖሊስ ይህንን አቤቱታውን በትላንትናው ዕለት ለይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ቢያስገባም፤ ሰነዱን ለክብሮምም ሆነ ለጠበቃው አስቀድሞ አለመስጠቱ አነጋግሯል። የጋዜጠኛው ጠበቃ የሆኑት አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ፤ አቤቱታው ለእርሳቸው እና ለደንበኛቸው ከተሰጠ በኋላ የመመካከሪያ ጊዜ እንዲፈቀድላቸው ለችሎቱ አመልክተዋል። በዚህ የፖሊስ ድርጊት ቁጣውን የገለጸው ችሎቱ፤ ሰነዱ ለተጠርጣሪ ወገን እንዲደርሳቸው ካደረገ በኋላ የትላንቱ የችሎቱ ውሎ ቀጥሏል።

የይግባኝ አቤቱታውን በተመለከተ ትላንት መከራከሪያቸውን ለችሎት ያቀረቡት የጋዜጠኛው ጠበቃ፤ በመጀመሪያ ያነሱት ጉዳይ ደንበኛቸው ስለ ተጠረጠረበት ወንጀል ፍሬ ነገር ነው። “ደንበኛዬ የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል አይደለም፤ ጋዜጠኛ ነው” ያሉት ጠበቃው፤ ፖሊስ “ከህወሓት የጥፋት ቡድን ተልዕኮ በመቀበል” ጠርጥሬዋለሁ ማለቱ “በበቂ ማስረጃ ላይ የተደገፈ አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል።  

ተጠርጣሪው “ማስረጃዎችን ሊያበላሽብኝ ይችላል” በሚል በዋስትና እንዳይለቀቅ ፖሊስ ላቀረበው መከራከሪያም ጠበቃው ሙግታቸውን ለችሎት አሰምተዋል። ጋዜጠኛው “ከባንኮች እና ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ሊኖረው አይችልም” ያሉት አቶ ጥጋቡ፤ ይህ የፖሊስ መከራከሪያ ውድቅ እንዲደረግም ለችሎቱ አመልክተዋል። 

ደንበኛቸው ላለፉት 22 ቀናት በማረፊያ ቤት መቆየቱን ያስታወሱት ጠበቃው፤ ክብሮም ያለበትን የጤና ዕክል በተጨማሪነት በመጥቀስም የዋስትና መብቱ እንዲከበርለት ጠይቀዋል። “ደንበኛዬ የልብ ህመም አለበት፤ ስለዚህም የዋስትና መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል” ብለዋል ጠበቃው። የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የተጠርጣሪው ዋስትና መብትን በተመለከተ ውሳኔ የሰጠው ዛሬ ነው። 

የይግባኝ ሰሚ ችሎቱ በዛሬው ውሎው የስር ፍርድ ቤት ብይን እንዲጸና ውሳኔ ያስተላለፈው፤ የፖሊስን የተጨማሪ ምርመራ ቀናት ውድቅ በማድረግ ነው። ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ የሚፈቀደው “ተጠርጣሪው በዋስትና ቢወጣ የምርመራ ሂደቱ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ ነው” ያለው ፍርድ ቤቱ፤ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለጋዜጠኛው የፈቀደውን የ15 ሺህ ብር ዋስትና አጽንቷል።  

የክብሮም ቤተሰቦች የከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠውን ትዕዛዝ በመያዝ፤ ጋዜጠኛው በእስር ላይ ወደሚገኝበት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቢሄዱም እስከ ቀኑ አስር ሰዓት ድረስ አለመፈታቱን ተናግረዋል። ጋዜጠኛ ክብሮም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ በተለምዶ ሶስተኛ ተብሎ ወደሚጠራው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት የተወሰደው ጥቅምት 16፤ 2014 ነበር። 

ጋዜጠኛውን ለእስር የተዳረገው በቁጥጥር ስር ከመዋሉ አራት ቀን በፊት በአሃዱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ በተላለፈ ዜና ምክንያት ነው። ሉዋም አታክልቲ በተባለች የጣቢያው ጋዜጠኛ አማካኝነት የተጠናቀረው ይህ ዜና፤ የደቡብ ወሎዋ ሐይቅ ከተማ በህወሓት ኃይሎች መያዟን የሚገልጽ ነበር። የተላለፈው ዜና የተሳሳተ እንደነበር ከተረጋገጠ በኋላ ጣቢያው የዚያኑ ዕለት “እርማት ማድረጉን እና ይቅርታ መጠየቁን” መግለጹ ይታወሳል።

ሉዋም ዜናው በተላለፈበት ዕለት ጥቅምት 12 አስር ሰዓት ገደማ ነበር በፖሊስ የተያዘችው። ጋዜጠኛዋ ከ21 ቀናት እስር በኋላ ባለፈው ሳምንት አርብ በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተፈታለች። ዜናው በተላለፈበት ዕለት አርታኢ የነበረው ክብሮም፤ ባለፈው አርብ ዋስትና ቢፈቀድለትም ፖሊስ ይግባኝ በመጠየቁ እስካሁንም በእስር ላይ ይገኛል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)