የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ይደርሳሉ የሚል እምነት እንዳላቸው የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ራይቼል ኦማሞ ይህን እምነታቸውን የገለጹት፤ ከአሜሪካ አቻቸው አንቶኒ ብሊንከን ጋር ዛሬ ረቡዕ ህዳር 8 በናይሮቢ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
በሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መግለጫ የታደሙ ጋዜጠኞች ያነሷቸው ጥያቄዎች በዋናነት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ነበሩ። ጋዜጠኞቹ ካቀረቧቸው ጥያቄዎች ውስጥ “በኢትዮጵያ ያሉ ተፈላሚ ወገኖች ከተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ከዲፕሎማሲያዊ ግፊት ባሻገር ምን ሊደረግ ይችላል?” የሚለው ይገኝበታል። የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ወደ አዲስ አበባ ባቀኑበት ወቅት “እንደ ኢትዮጵያ ጓደኛ እና ጎረቤት” የተኩስ ማቆም ጉዳይን እንዳነሱ ጠቅሰዋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ “ለዚህ ቀውስ መፍትሔ ለማግኘት ኢትዮጵያ ባላት አቅም እናምናለን። ተኩስ ማቆም ይቻላል ብለን እናምናለን። ሰብዓዊ እርዳታን አስመልክቶ ያሉ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች ሊሳኩ የሚችሉ ናቸው ብለን እናምናለን” ሲሉ ተደምጠዋል። “በኢትዮጵያ ሕዝብ ጥንካሬ እና ብልኃት (wisdom) እምነት ሊኖረን ይገባል። ምክንያቱም በስተመጨረሻ መፍትሔው የሚመጣው ከእነሱ ነው” ሲሉም ሚኒስትሯ አክለዋል።
“ይህ ቀውስ ያበቃል ብለን እናምናለን” ያሉት ራይቼል ኦማሞ፤ ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ “ጠንካራ ሀገር፤ ጠንካራ አጋር እንደገና በቀጠናችን ሰላምን የምታረጋግጥ ሆና እንድትቀጥል” ሊደረግ ይገባል ያሉትን ጠቁመዋል። “እንደ ጎረቤት ማድረግ ያለብን መደገፍ፣ ማጽናናት እና ትክክለኛውን አቅጣጫ መጠቆም ነው” ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ “በኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋ አንቁረጥ፤ በዚህ ቀውስ አዎንታዊ ሆነን በጽናት መቆም አለብን” የሚል ጥሪ አቅርበዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው የኢትዮጵያ ጉዳይ፤ ኬንያ እና ሀገራቸውን እኩል በጥልቅ የሚያሳስብ እንደሆነ ተናግረዋል። ብሊንከን ውጊያው ባለፈው አመት በትግራይ ኋላም በአማራ ክልል ሲስፋፋ በአገሪቱ ዜጎች ለችግር መዳረጋቸውን በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
ግጭቱ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ጸጥታ ጭምር ስጋት እንደሆነ የገለጹት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ሁሉም ወገኖች ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ ጥሪ አቅርበዋል። ብሊንከን፤ ህወሓት እና የኦሮሞ ነጻነት ጦር ወደ አዲስ አበባ ያደርጉታል ያሉትን ግስጋሴ እንዲያቆሙ አገራቸው እንደምትፈልግ ተናግረዋል። “ጦርነቱ እንዲቆም [ተፈላሚ] ወገኖች በጠረጴዛ ዙሪያ ሲሰበሰቡ፣ የሰብአዊ እርዳታ በነጻነት ሲሰራጭ፤ የታሰሩ ሰዎች ሲፈቱ፣ ሁሉም ወገኖች ልዩነቶቻቸውን በሰላም እና ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ሲረባረብ ማየት እንፈልጋለን” ሲሉም የሀገራቸውን አቋም አስተጋብተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስትን ጨምሮ “ቅሬታ እና ስጋት ያላቸው ሁሉ”፤ በአገሪቱ ህገ መንግስት መሠረት በሚያደርጉት ንግግር፣ ውይይት እና ድርድር ልዩነቶች እና ግጭቶችን መፍታት እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ብሊንከን ገልጸዋል። “እንዳለመታደል ሆኖ በሚያሳዝን ሁኔታ ሁሉም ከፖለቲካዊ ሂደት ይልቅ ወታደራዊ መንገድን መርጧል” ሲሉ ተችተዋል።
በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል የዘር ማጥፋት (genocide) ተፈጽሟል ብለው ያምኑ እንደሆነ የተጠየቁት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “በሐቆች እና በሕግ ላይ አተኩረናል። ሐቆቹን እና የህጉን ትንታኔ ከተመለከትን በኋላ እንወስናለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ብሊንከን “ግፍ ሲፈጸም እና ሰዎች ሲሰቃዩ ተመልክተናል፤ አሁንም መመልከታችንን ቀጥለናል። ምንም እንበለው ምን መቆም አለበት። ተጠያቂነት መኖር አለበት። ተጠያቂነት እንዲኖር ቁርጠኞች ነን” ሲሉ በጋዜጣዊ መግለጫው ተደምጠዋል።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይህን መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት ከኬንያው ፕሬዝዳንት አሁሩ ኬንያታ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። ብሊንከን በጋዜጣዊ መግለጫው፤ ኡሁሩ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በኢትዮጵያ በአካል በመገኘት አድርገውታል ያሉትን ጥረት አመስግነዋል። የኬንያው ፕሬዝዳንት ባለፈው እሁድ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር መምከራቸው ይታወሳል።
አሁሩ እና ብሊንከን ዛሬ በነበራቸው ውይይት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የከባቢ አየር ለውጥ እንዲሁም የቀጠናውን ሰላም እና ጸጥታ የተመለከቱ ጉዳዮች እንደተዳሰሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። የኬንያው ፕሬዝዳንት እና የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዚሁ ውይይታቸው፤ “የቀጠናውን ግጭቶች ለመፍታት እና በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም በማምጣት ረገድ” ሊተባበሩ የሚችሉባቸውን ዕድሎች እንደፈተሹ መግለጫው ይጠቁማል።
ብሊንከን ከውይይቱ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸውም ይህንኑ አስተጋብተዋል። “ከኬንያ፣ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እንዲሁም ሌሎች አጋሮች ጋር በቅርበት እየሰራን ነው” ሲሉ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ብሊንከን የአፍሪካ ህብረት ልዩ ልዑክ እና የአሜሪካው አቻቸው ጄፍሪ ፌልትማን፤ ውጊያ የገጠሙ “ወገኖች ያለቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ ግጭት እንዲያቆሙ ለመጫን” እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
ብሊንከን እንዳሉት የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን ማስቆም እና በሰሜን ኢትዮጵያ የነፍስ አድን አቅርቦት በአፋጣኝ ለሚያስፈልጋቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እርዳታ የሚቀርብበትን መንገድ ማመቻቸት ልዩ ልዑካኑ ከሚያደርጉት ጥረት መካከል ይገኙበታል። “ምንም እንኳ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሰራተኞቻችን ቁጥር ለመቀነስ ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ ብንወስድም፤ ኤምባሲያችን በእነዚህ ጥረቶች ሙሉ በሙሉ ተሳትፎ እያደረገ ነው” ብለዋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ቢሉም፤ የአሜሪካ ዜጎች ከኢትዮጵያ ለቅቀው እንዲወጡ አገራቸው ያስተላለፈችውን ጥሪ በናይሮቢም ደግመውታል። የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስከ ቅዳሜ በአፍሪካ በሚያደርጉት ጉብኝት ከኬንያ በተጨማሪ ወደ ናይጄሪያ እና ሴኔጋል ይጓዛሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ዘግየት ብሎ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለዋል]