– የክልሉ አደራጅ ኮሚቴ ምስረታው በታቀደለት ጊዜ ይካሄዳል ብሏል
በሃሚድ አወል
የቤንች ሸኮ ዞን ምክር ቤት ከአራት ቀናት በኋላ የሚከናወነው የአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መስራች ጉባኤ እንዲራዘም ጥያቄ አቀረበ። የዞኑ ምክር ቤት ጥያቄውን ያቀረበው፤ ለአዲሱ ክልል ጊዜያዊ ዋና ከተማ መሰየሙን በመቃወም ነው። የአዲሱ ክልል አደራጅ ኮሚቴ በበኩሉ “የሚራዘም ጉባኤ የለም” ሲል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ምክር ቤት የክልል ምስረታ ስነ ስርዓቱ እንዲራዘም የጠየቀው፤ በትላንትናው ዕለት ረቡዕ ህዳር 8፤ 2014 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ነው። የዞኑ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ እንዲጠራ ካደረጉት ሁለት አጀንዳዎች መካከል የመጀመሪያው የአዲሱ ክልል ምስረታ ጉዳይ መሆኑን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወርቅነሽ ባድንስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የክልሉ አደራጅ ኮሚቴ “ቦንጋ ከተማን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ አድርገው መወሰናቸው” በዞኑ ምክር ቤት አባላት ቅሬታ ማስነሳቱን አፈ ጉባኤዋ ገልጸዋል። አዲሱ ክልል በማዕከልነት የሚጠቀምበት ከተማ ጉዳይ በምክር ቤቱ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ በወጣው የአቋም መግለጫ ላይም በጉልህ ተንጸባርቋል።
“የማዕከል ጉዳይ በይደር ያለና ጊዜው ሲደርስ በአለም አቀፍ መመዘኛዎችና በገለልተኛ ወገን ተሰርቶ እንደሚወሰን ተስማምተን እየጠበቅን ባለንበት ወቅት፤ ህጋዊ ስልጣን ባልተሰጣቸው አካላት ከመርህና ከአቅጣጫ ውጭ መወሰኑ ላይ እንደ ቤንች ሸኮ ዞን ህዝቦች ቅሬታ እያቀረብን ስለሆነ ለህዝባዊ ቅሬታችን ህጋዊና ፍትሃዊ ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ የአዲሱ ክልል መስራች ጉባኤ እንዲራዘምልን እንጠይቃለን” ሲሉ የዞኑ ምክር ቤት አባላት በአቋም መግለጫቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት “ከመርህ እና ከህግ ውጭ” ተወስኗል ባሉት የማዕከል ምርጫ ላይ የፌደራል መንግስቱ ጣልቃ እንዲገባ እና የዞኑ አመራሮች ቅሬታቸውን እንዲያቀርቡ በተጨማሪነት ጥያቄ አቅርበዋል። የዞኑ ምክር ቤትም “ቅሬታውን ህጋዊ መንገድ ተከትሎ” እንዲያስፈጽም በመግለጫው ኃላፊነት ተጥሎበታል።
የዞኑን ጥያቄ በተመለከተ የአዲሱ ክልል አደራጅ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጸጋዬ ማሞ በሰጡት ምላሽ “የሚራዘም ጉባኤ የለም፤ ውይይቱም አብቅቷል” ሲሉ የክልል ምስረታው እንደማይራዘም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የህዝበ ውሳኔ አስተባባሪ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጁ አቶ ምትኩ በድሩም “ሁሉም ዝግጅት አልቋል፤ እንግዶችም ተጋብዘዋል” ሲሉ ከአቶ ጸጋዬ ማሞ ጋር ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።
የዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ግን “አንዱ መስራች ወገን ቅሬታ ውስጥ እያለ ወደ ምስረታ ከተገባ በምስረታው ላይ ላንገኝ እንችላለን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። አፈ ጉባኤዋ “በምስረታው ላይ አንገኝም” ቢሉም ግን አቶ ምትኩ አለመግባባቱ በውይይት ይፈታል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የቤንች ሸኮ ዞንን እና የአስራ አንደኛውን ክልል አደራጅ ኮሚቴ እያከራከረ የሚገኘው የከተማ ማዕከል ጉዳይ ማነጋገር የጀመረው አሁን አይደለም። የክልሉ የህገ መንግስት ረቂቅ ክልሉ “ብዝሃ ማዕከል ይኖሩታል” ከማለት ውጭ የማዕከሎቹን ብዛት እና የታጩትን ከተሞችን በዝርዝር አለመጥቀሱ ጥያቄዎችን አስነስቶ ነበር።
አፈ ጉባኤ ወርቅነሽም “የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር መቀመጫ ጉዳይ ከጅምሩ አጨቃጫቂ ነበር” ሲሉ ጉዳዩ ብዙ እንዳሟገተ ያስታውሳሉ። የክልሉ ማዕከል ሆነው የሚመረጡትን ከተማዎች ጉዳይ ለፌደራል መንግስት የተሰጠ ኃላፊነት እንደነበርም ይገልጻሉ። ይህንን ገለጻ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አደራጅ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢም ይቀበላሉ።
ሆኖም የክልል ምስረታው ሲቃረብ ማዕከል የሚሆኑ ከተሞችን የመምረጡ ኃላፊነት ከፌደራል መንግስት ወደ ክልል አደራጅ ኮሚቴ ተዘዋውሯል። ይህ የኃላፊነት መለዋወጥ የቤንች ሸኮ ዞንን ቅር እንዳሰኘው የዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የህዝበ ውሳኔ አስተባባሪ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጁ ግን ይህ የሆነበት ምክንያት የፌደሬሽን ምክር ቤት “የቴክኒክ ድጋፎችን እናደርጋለን። አጥንታችሁ አቅርቡ በማለቱ ነው” ይላሉ።
በአደራጅ ኮሚቴው እየተከናወነ የነበረው የጥናት ሂደት ሳይጠናቀቅ የክልል ምስረታው በመድረሱ፤ ክልሉን በጊዜያዊ ማዕከል መመስረት ማስፈለጉን የኮሚቴው አባላት ያስረዳሉ። በዚህም ምክንያት በአደራጅ ኮሚቴው ስር የሚገኘውን እና 13 አባላት ያሉት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ “ጊዜያዊ ማዕከል መመረጥ አለበት” የሚል ውሳኔ አሳልፏል።
ይህ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውሳኔ ግን በተወሰኑ የአካባቢው የህብረተሰብ ክፍሎች ተቀባይነት አላገኘም። ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ለማዕከልነት የተመረጡ ከተሞች “ቁጥራቸው እና ስማቸው ሳይታወቅ፤ ጊዜያዊ ማዕከል የመምረጥ ሀሳብ መቅረብ አልነበረበትም” የሚል ተቃውሞ አንስተው እንደነበር አቶ ምትኩ በድሩ ያስረዳሉ። በዚህም መሰረት ለማዕከልነት የተመረጡ አራት ከተሞች በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ይፋ እንደተደረገ ጨምረው ይገልጻሉ።
ኮሚቴው ከዚህ በተጨማሪም ለማዕከልነት ከተመረጡ አራት ከተሞች አንዷ የሆነችው ቦንጋን፤ ለአዲሱ ክልል በጊዜያዊ ማዕከልነት እንድታገለግል መርጧል። የቦንጋ ከተማ በጊዜያዊ ማዕከልነት እና የምስረታ ጉባኤውን ለማካሄድ የተመረጠችው በሁለት መስፈርቶች መሆኑን አቶ ምትኩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የመጀመሪያው መስፈርት ከተማይቱ የምትገኝበት የካፋ ዞን “የህዝብ ብዛት ነው” ይላሉ። የክልል ምስረታው በቦንጋ ከተማ እንዲካሄድ የተወሰነበት ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ “ለሁነቱ አማካኝ ቦታ ላይ በመገኘቷ” መሆኑን ያብራራሉ። የምስረታ ጉባኤው በቦንጋ ከተማ እንዲካሄድ ሲወሰን በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ዘንድ የድምጽ ልዩነት ተመዝግቦ እንደነበር ግን አቶ ምትኩ አልሸሸጉም። ከኮሚቴው አባላት አስራ አንዱ ቦንጋ ከተማ የመስራች ጉባኤውን እንድታካሄድ ይሁንታቸውን የሰጡ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ሁለት አባላት “ተቃውመዋል” ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የምስረታ ጉባኤ እና በዓል የሚካሄደው በመጪው ሳምንት የመጀመሪያ ሁለት ቀናት ነው። የአዲሱ ክልል ምክር ቤት አባላት ሰኞ ህዳር 13፤ 2014 በክልሉ ህገ መንግስት ረቂቅ ላይ ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አዘጋጆቹ ገልጸዋል። በማግስቱ ማክሰኞ ህዳር 14 ደግሞ የክልሉ ምስረታ በዓል በይፋ የሚከናወን ይሆናል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)