ወደ ኮምቦልቻ እና ላሊበላ የእርዳታ በረራ ሊጀመር ነው

በአማራ ክልል ወደሚገኙት ኮምቦልቻ እና ላሊበላ የእርዳታ በረራ እንደሚጀመር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ ገለጹ። የኢትዮጵያ መንግስት  ወደ ሁለቱ አካቢዎች የሚደረገውን በረራ የፈቀደው የእርዳታ አቅርቦቶቹን ለማድረስ ነው። 

ቃል አቃባዩ በረራዎቹ እንደሚጀመሩ ጥቆማ የሰጡት ዛሬ ሐሙስ ህዳር 9 በሰጡት ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። የእርዳታ በረራዎች ወደ መቐለ ጭምር ይደረጉ እንደነበር በመግለጫቸው የጠቀሱት ቃል አቃባዩ፤ “በዚያ መሰረት ኮምቦልቻም፣ ላሊበላም እርዳታ ለማድረስ መንግስት ይፈቅዳል” ብለዋል። 

በአማጽያን ቁጥጥር ስር ወዳሉት ወደ እነዚህ አካባቢዎች የሚደረገው በረራ በምን መልኩ የሚከናወን እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ዲና፤  “በምን ቁጥጥር ስር እንዳለ መረጃ የለኝም” ሲሉ በደፈናው ምላሽ ሰጥተዋል። የህወሓት ኃይሎች ታሪካዊቷን የላሊበላ ከተማ መቆጣጠራቸው የተነገረው በሐምሌ ወር መጨረሻ ነበር። 

አማጽያኑ “ስትራቴጂካዊ” እንደሆነች የሚነገርላትን ደሴን ባለፈው ጥቅምት ወር ከተቆጣጠሩ በኋላ ከከተማይቱ አቅራቢያ የምትገኘውን ኮምቦልቻ ከተማ ይዘዋል። በርካታ ኢንዱስትሪዎችን በውስጧ የያዘችው ኮምቦልቻ፤ የአየር ማረፊያ ባለቤትም ናት። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ከተማይቱ የሚያደርገውን በረራ ያቋረጠው በጥቅምት ወር መጀመሪያ ነበር። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)