የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በይፋ ተመሰረተ

በሃሚድ አወል

አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አስራ አንደኛው የፌዴሬሽኑ አካል በመሆን በይፋ ተመሰረተ። ዛሬ ማክሰኞ ህዳር 14፤ 2014 የምስረታ ጉባኤውን ያካሄደው የአዲሱ ክልል ምክር ቤት፤ የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ አፈ ጉባኤ እና ምክትል አፈ ጉባኤ በአብላጫ ድምጽ መርጧል። 

አዲስ የተቋቋመው የክልሉ ምክር ቤት ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾን አዲሱን ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት እንዲመሩ መርጧል። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ ምክር ቤት ካሉት 52 አባላት መካከል የሃምሳ አንዱን ድምጽ አግኝተዋል። አንድ የምክር ቤት አባል ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል። 

የክልሉ ምክር ቤት አባል ባለመሆናቸው የርዕሰ መስተዳድርነት ማዕረግ ያላገኙት አዲሱ ተሿሚ፤ አስራ አንደኛው ክልልን የመምራት ኃላፊነት ከመረከባቸው አስቀድሞ ክልሉን ለማደራጀት የተቋቋመውን ኮሚቴ በዋና ሰብሳቢነት መርተዋል። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከ45 ቀናት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አማካኝነት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዲኤታ ሆነው ተሹመው ነበር። 

ዶ/ር ነጋሽ ወደ መንግስት ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት እና በተመራማሪነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ምክትል ርዕስ መስተዳድሩ ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን የያዙትም በውሃ ምንድስና የትምህርት ዘርፍ ነው።

በካፋ ዞን ምክር ቤት አቅራቢያ በሚገኘው የካፋ የባህል አዳራሽ በተካሄደው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የምስረታ ሥነ-ስርዓት ላይ ሌሎች አበይት መርሃ ግብሮችም ተከናውነዋል። ከመርሃ ግብሮቹ መካከል የሚመራበትን ህገ መንግስት ማጽደቅ አንዱ ነበር። በዛሬው ሥነ-ስርዓት የምስረታ ጉባኤውን ያካሄደው የክልሉ ምክር ቤት የክልሉን ህገ መንግስት ያጸደቀው በሙሉ ድምጽ ነው። 

የአዲሱ ክልል ህገ መንግስት 11 ምዕራፎች እና 123 አንቀጾች አሉት። ህገ መንግስቱ፤ በ13 ብሔሮች እና ስድስት የአስተዳደር መዋቅሮች የተመሰረተው የአዲሱ ክልል የስራ ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን ደንግጓል። ሆኖም በክልሉ የሚገኙት አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በየምክር ቤቶቻቸው “የራሳቸውን የስራ ቋንቋ ሊደነግጉ እንደሚችሉ” በህገ መንግስቱ ላይ ሰፍሯል።

የክልሉን መንግስት የስልጣን ክፍፍል መርህ የሚዳስሰው የህገ መንግስቱ አንቀጽ፤ በክልሉ ብዝሃነትን ያማከለ የስልጣን ክፍፍል እንደሚኖር ያመለክታል። በዚሁ አንቀጽ ስር የሚገኝ ንዑስ አንቀጽ፤ ከአንድ ብሔረሰብ ወይም የአስተዳደር መዋቅር በተመሳሳይ ጊዜ የመጡ ተወካዮች፤ በክልሉ ካሉ አምስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ከአንድ በላይ መያዝ እንደማይችሉ አስቀምጧል። አምስቱ የስራ ኃላፊነቶች የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፣ ምክትል ርዕስ መስተዳድር እና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ 

አዲሱን ክልል የመሰረቱት የካፋ፣ ዳውሮ፣ ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞ፣ ሸካ ዞኖች እና ኮንታ ልዩ ወረዳ ናቸው። ከእነዚህ የአስተዳደር መዋቅሮች የተውጣጡ 52 አባላት ናቸው የአዲሱን ምክር ቤት በአባልነት የተቀላቀሉት። በአዲሱ ክልል ህገ መንግስት ላይ “የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎች” በሚል ርእስ ስር የሰፈረው አንቀጽ “ህገ መንግስቱ ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት በህጉ መሰረት በክልል ምክር ቤት የተወከሉ አባላት ለዚህ [ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች] ክልል ምክር ቤት እንደተወከሉ ይቆጠራል” ሲል ይደነግጋል።

ከአዲሱ ክልል ምክር ቤት አባላት ውስጥ ሃያዎቹ፤ የምስረታ ጉባኤው የተካሄደበት የካፋ ዞንን የወከሉ ናቸው። የዳውሮ ዞን በዘጠኝ አባላት በመወከል በተወካይ ብዛት በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል። ምዕራብ ኦሞ እና የቤንች ሸኮ ዞኖች እያንዳንዳቸው ሰባት ተወካዮች በአዲሱ ክልል ምክር ቤት ውስጥ አሏቸው። የሸካ ዞን ስድስት፤ የኮንታ ልዩ ወረዳ ደግሞ ሶስት ክልል ምክር ቤት ተወካዮች አሏቸው።  

በደቡብ ክልል ስር የነበሩ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ የራሳቸውን የጋራ ክልል ለመመሰረት የሚያስችላቸውን ህዝበ ውሳኔ ያካሄዱት መስከረም 20፤ 2014 ነበር። በህዝበ ውሳኔው ላይ ድምጽ ከሰጡት የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል 96 በመቶው የአዲሱን ክልል መመስረት ደግፈዋል። ከህዝበ ውሳኔው መካሄድ አንድ ወር በኋላ አስቸኳይ ስብሰባውን ያደረገው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ ውጤትን አጽድቋል። የፌደሬሽን ምክር ቤት ውጤቱን ካጸደቀ ከአራት ቀናት በኋላ ጉባኤውን ያካሄደው የደቡብ ክልል ምክር ቤት፤ ለአዲሱ ክልል በይፋ ስልጣን ማስረከቡ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)