በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሸካ ዞን ስር በምትገኘው ቴፒ ከተማ በትላንትናው ዕለት በተሰነዘረ ጥቃት አራት የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የዞኑ የሰላም እና የጸጥታ መምሪያ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ጥቃቱን የሰነዘሩት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ “ጸረ ሰላም ኃይሎች” መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የሸካ ዞን የሰላም እና የጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አለማየሁ አለሙ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንዳሉት፤ ጥቃቱ የደረሰው በቴፒ ከተማ ስር ባለው የኪ ወረዳ ሰላም በር ቀበሌ በገቢ ማሰባሰብ ላይ ተሰማርተው በተሽከርካሪ እየተመለሱ በነበሩ የመንግስት ሰራተኞች ላይ በተከፈተ ተኩስ ነው። በጥቃቱም የመንግስት ሰራተኞቹን አጅበው የነበሩ ሶስት የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል አባላት እና አንድ የፌደራል ፖሊስ መገደላቸውን አስረድተዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ የአንዱ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ ረቡዕ ህዳር 15 መፈጸሙን የዞኑ የሰላም እና የጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አክለዋል። በጥቃቱ ከቆሰሉት ስድስት ሰዎች መካከል የየኪ ወረዳ የገቢዎች ጽህፈት ቤት ባለሙያ እንደሚገኙበት የሸካ ዞን ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ አድራሮ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከቆሰሉት ሰዎች መካከል አራቱ ለህክምና ወደ ጅማ እና አዲስ አበባ መላካቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
በቴፒ ከተማ እና አካባቢው ለሶስት አመት ተኩል የዘለቀ የሰላም ችግር መኖሩን የሚጠቅሱት አቶ አለማየሁ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ “ታጥቀው ጫካ የገቡ ሰዎች” እንዳሉ ጠቁመዋል። የትላንቱን ጥቃት የፈጸሙት ኃይሎች በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ “ሽፍቶች” መሆናቸውን አመልክተዋል። ከትላንቱ ጥቃት ጀርባ “የጁንታው ኃይል እጅ እንዳለበት ምንም ጥርጥር የለንም” ያሉት ኃላፊው፤ የጥቃቱን አድራሾች ለመያዝ ከትላንት ማታ ጀምሮ የጸጥታ አካላት በአሰሳ ላይ እንዳሉ አስታውቀዋል።
ትላንት ህዳር 14 በይፋ በተመሰረተው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስር ከሚገኙ ዞኖች አንዱ በሆነው የሸካ ዞን፤ አካባቢው ላለፉት ሶስት ዓመታት በኮማንድ ፖስት ስር ሲተዳደር ቆይቷል። በአካባቢው ያለው የጸጥታ ችግር መንስኤ “ከመዋቅር ጥያቄ” ጋር የተያያዘ እንደሆነ የአካባቢው ባለስልጣናት ይናገራሉ።
ከነባሩ የጸጥታ ችግር በተጨማሪ፤ በቅርቡ በዞኑ ዋና ከተማ ላይ የተደረገው ለውጥ በተወሰኑ ወገኖች ዘንድ ቅሬታ ማስነሳቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። የሸካ ዞን አስተዳደር የመቀመጫ ከተማውን ከማሻ ወደ ቴፒ የለወጠው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር። የትላንቱ ጥቃት ከዚህ ለውጥ ጋር ይገናኝ እንደው የተጠየቁት የዞኑ የሰላም እና የጸጥታ መምሪያ ኃላፊ፤ “በከተማው [ቅያሬ] ያኮረፉ ቢኖሩም፤ የትላንቱ ጥቃት ግን ከዚህ ጋር የሚገናኝ አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)