የኢትዮጵያ መንግስት፤ አራት የአየርላንድ ዲፕሎማቶች በአንድ ሳምንት ውስጥ ከሀገሪቱ ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠቱን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ። በአዲስ አበባ በሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ እንዲቆዩ የተፈቀደላቸው በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር እና ሌላ አንድ ተጨማሪ ዲፕሎማት መሆናቸውን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃውን የወሰደው፤ አየርላንድ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ግጭት እና የሰብዓዊ ቀውስ በተመለከተ “በዓለም አቀፍ መድረኮች እያራመደችው ባለው አቋም ሳቢያ” መሆኑን በአዲስ አበባ ለሚገኘው ኤምባሲ መግለጹን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል። መግለጫው የዓለም አቀፍ መድረኮች በሚል በምሳሌነት የጠቀሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትን ነው።
አየርላንድ በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰ አንስቶ በጉዳዩ ላይ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት እንዲሰበሰብ እና እርምጃ እንዲወስድ ተደጋጋሚ ግፊት ስታደርግ የቆየች ሀገር ናት። የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፤ ባለፈው ጥቅምት 26 በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያወጣው መግለጫ በአየርላንድ እና በምክር ቤቱ ሶስት የአፍሪካ ተወካይ አባል ሀገራት የተመራ ነበር።
የአየርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው መግለጫው በአዲስ አበባ የሚገኘው ኤምባሲ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ገልጿል። ሆኖም በእርምጃው ሳቢያ በአዲስ አበባው ኤምባሲ ያሉ ዲፕሎማቶች በሁለተኛ ሶስተኛ እንዲቀነሱ መደረጉ፤ ኤምባሲው በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ጠቁሟል። በዚህም መሰረት የኤምባሲው ዋነኛ ትኩረት የቆንስላ አገልግሎቶች መስጠት ይሆናል ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን እርምጃ በተመለከተ የአየርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሞን ኮቪኔ “ውሳኔው ጊዜያዊ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ማለታቸውን መግለጫው ጠቅሷል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በውሳኔው “ጥልቅ ሀዘን” እንደተሰማቸው መግለጻቸውንም አክሏል። አየርላንድ በኢትዮጵያ ኤምባሲ የከፈተችው የዛሬ 27 ዓመት ገደማ ነበር። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)