የአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ክልል ምክር ቤት፤ የኮንታ ልዩ ወረዳ በዞን ደረጃ እንዲደራጅ ወሰነ

በሃሚድ አወል

አዲሱን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከመሰረቱት አስተዳደራዊ መዋቅሮች አንዱ የሆነው የኮንታ ልዩ ወረዳ በዞን ደረጃ እንዲደራጅ የክልሉ ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ ወሰነ። የክልሉ ምክር ቤት የልዩ ወረዳውን በዞን የመደራጀት ጥያቄን በሙሉ ድምጽ ያጸደቀው ዛሬ ባካሄደው ጉባኤ ላይ ነው። 

የምስረታ ጉባኤውን በትላንትናው ዕለት ያደረገው የክልሉ ምክር ቤት፤ ዛሬ ረቡዕ ህዳር 15፤ 2014 በነበረው የሁለተኛ ቀን ውሎው የአደረጃጀት ጥያቄን ጨምሮ ሌሎችንም ጉዳዮች ተመልክቶ ውሳኔ አሳልፏል። የክልሉ ምክር ቤት አባላት የኮንታ ልዩ ወረዳ በዞን እንዲደራጅ በቀረበላቸው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ከሌሎች ጉዳዮች በበለጠ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ውይይት አድርገውበታል።  

በደቡብ ክልል ስር ከነበሩ እና አስራ አንደኛውን ክልል ከመሰረቱት የአስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ አምስቱ በዞን ደረጃ የተዋቀሩ ናቸው። ቀሪው የኮንታ አካባቢ በነባሩ የደቡብ ክልል የነበረው የልዩ ወረዳነት ደረጃ ነበር። 

የኮንታ ልዩ ወረዳን ጨምሮ በአዲሱ ክልል ሌሎችም የአደረጃጀት ጥያቄዎች መኖራቸውን ያነሱት አንድ የምክር ቤት አባል፤ የእነዚህ የአደረጃጀት ጥያቄዎች ምላሽ የማያገኙ ከሆነ በቀጣይ ክልሉን ሊፈትኑት ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። የምክር ቤት አባሉ ለስጋታቸው ማሳያነት ያነሱት በምዕራብ ኦሞ እና በቤንች ሸኮ ዞን ያሉ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ነው።

ሌላ የምክር ቤት አባል፤ በአዲሱ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ የአደረጃጀት ጥያቄው ምላሽ ያገኘለት የኮንታ ዞን “ምን ያህል የወረዳዎች አደረጃጀቶች ይኖሩታል?” ሲሉ ጠይቀዋል። በጉባኤው ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ፤ የኮንታ ልዩ ወረዳ በዞን የመደራጀት ጥያቄ ለዓመታት የቆየ እንደነበር አስታውሰዋል።  

ልዩ ወረዳው በዞን የመደራጀት ጥያቄውን በምክር ቤቱ አጽድቆ ለነባሩ የደቡብ ክልል የላከው፤ ከሶስት ዓመት በፊት በ2011 ህዳር ወር ላይ ነበር። በወቅቱ የአደረጃጀት ጥያቄው የቀረበለት የነባሩ የደቡብ ክልል፤ በጥያቄው ላይ ጥናት እንዳደረገበት ዶ/ር ነጋሽ ጠቅሰዋል። ነባሩ የደቡብ ክልል፤ የዞንነት ጥያቄው ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምስረታ በኋላ በአዲሱ ክልል ምላሽ እንዲያገኝ ውሳኔ አሳልፎ እንደነበርም ለዛሬው ጉባኤ በቀረበ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ተመልክቷል።

የኮንታ ልዩ ወረዳን የአደረጃጀት ጥያቄ የደቡብ ምዕራብ ክልል አደራጅ ዐብይ ኮሚቴ ሲመክርበት መቆየቱን ያነሱት የኮሚቴው የቀድሞው ሰብሳቢ ዶ/ር ነጋሽ፤ በስተመጨረሻ ኮንታ በዞን እንዲደራጅ ውሳኔ ላይ መድረሱን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። በዚህ መሰረትም የኮንታ ልዩ ወረዳን በዞን ለማደራጀት ያለመ የውሳኔ ሃሳብ ዛሬ ለተሰበሰበው ምክር ቤት መቅረቡን አብራርተዋል። 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ህገ መንግስት መሰረት አደረጃጀቶችን የማቋቋም ስልጣን ለክልሉ ምክር ቤት የተሰጠ ነው። የክልሉ ምክር ቤት ኮንታ በዞን እንዲደራጅ ይሁንታውን ቢሰጥ እንኳ ዝርዝር አደረጃጀቶችን ለማስፈጸም ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ነጋሽ ገልጸዋል። የአዲሱ ክልል ምክር ቤት በቅርብ ጊዜ ሊሰበሰብ ስለማይችል፤ የኮንታ ዞን ሙሉ አደረጃጀትን ተግባራዊ ለማድረግ ምክር ቤቱ ለክልሉ አስፈጻሚ አካላት ውክልና እንዲሰጥም ጠይቀዋል። 

ምክር ቤቱ በውክልናው ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ ውሳኔ ባያሳልፍም የኮንታን በዞንነት የመደራጀት ጥያቄ ግን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። የኮንታ ዞን በገበታ ለሀገር እንዲለሙ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከተመረጡት አካባቢዎች አንዱ የሆነው የኮይሻ ሐይቅ መገኛ ነው። 

ምክር ቤቱ ከኮንታ ልዩ ወረዳ የአደረጃጀት ጥያቄ በተጨማሪ ሶስት አዋጆችን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። በዞኑ ምክር ቤት የጸደቁት አዋጆች የደቡብ ምዕራብ ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የአስፈጻሚ አካላት ስልጣን እና ተግባር ለመወሰን የወጣ አዋጅ እና በነባሩ ደቡብ ክልል የወጡ አዋጆች ተፈጻሚነታቸው እንዲቀጥል የሚፈቅድ አዋጅ ናቸው። 

በነባሩ ደቡብ ክልል የወጡ አዋጆች ተፈጻሚነታቸው እንዲቀጥል በሚፈቀድው አዋጅ መሰረት፤ በደቡብ ክልል ምክር ቤት ጸድቀው በስራ ላይ ያሉ 25 አዋጆች በአዲሱም ክልል ተፈጻሚ ይሆናሉ። በዚህ አዋጅ ላይ የአዲሱ ክልል ምክር ቤት አባላት ጥያቄ እና አስተያየት ሰንዝረዋል። 

አንድ የምክር ቤት አባል ተፈጻሚነታቸው እንዲቀጥል ከተወሰኑት አዋጅ መካከል “የቆዩ አዋጆች ይገኙበታል” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። የምክር ቤት አባሉ አዲሱ ክልል በራሱ አውድ አዋጆችን ቢያወጣ የሚል ምክረ ሀሳብም ለግሰዋል። 

ተፈጻሚነታቸው እንዲቀጥል ከተወሰነላቸው አዋጆች መካከል፤ በነባሩ የደቡብ ክልል ከ18 ዓመታት በፊት የወጣው የቤተሰብ ህግ አዋጅ ይገኝበታል። በአጠቃላይ በአዲሱ ክልል ተፈጻሚ እንዲሆኑ በአዲሱ ክልል ምክር ቤት ከተፈቀደላቸው 25 አዋጆች መካከል አስራ ሰባቱ ከአስር ዓመት በፊት የወጡ ናቸው። 

የክልሉ ምክር ቤት ያጸደቀው ሌላኛው አዋጅ የአስፈጻሚ አካላት ስልጣን እና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ነው። በዚህ አዋጅ መሰረት ክልሉ 21 የአስፈጻሚ አካላት መስሪያ ቤቶች እና 17 ተጠሪ ተቋማት ይኖሩታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)