የኢትዮጵያ መንግስት፤ አሜሪካ ለህወሓት ቡድን የመወገን “ግልጽ ጦርነት” በኢትዮጵያ ላይ ከፍታለች አለ። የአሜሪካ መንግስትም ሆነ በአዲስ አበባ የሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ ኢትዮጵያን በሚመለከት ከሚያወጧቸው “አሸባሪ፣ አሳፋሪ እና ኃላፊነት የጎደላቸው” መግለጫዎች እንዲቆጠቡም አስጠንቅቋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ዛሬ ሐሙስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የአሜሪካ ኤምባሲ እና አንዳንድ የአሜሪካ መንግስት ተወካዮች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያሉት ጫና “እጅግ አሳፋሪ በሆነ መንገድ” እና “በማይገባ መስመር ቀጥሏል” ብለዋል። ሚኒስትር ዲኤታው ለዚህ በማሳያነት የጠቀሱት በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል በአሜሪካ ኤምባሲ የወጣውን ማስጠንቀቂያ ነው።
ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ጀምሮ አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እና በአሜሪካ መንግስት ተቋማት የተሰራጨው መልዕክት፤ በኢትዮጵያ አሸባሪዎች ያለ ምንም ቅደመ ማስጠንቀቂያ የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ ስለሚችሉ የአሜሪካ ዜጎች ራሳቸውን ከአደጋ እንዲጠብቁ የሚያሳስብ ነው። ኤምባሲው በዚሁ መልዕክቱ አሸባሪዎች በኢትዮጵያ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ተቋማትን፣ የቱሪስት ቦታዎችን፣ የትራንስፖርት ማዕከላትን፣ የመገበያያ ስፍራዎችን፣ በምዕራባዊያን ባለቤትነት የተያዙ የንግድ ድርጅቶችን፣ ምግብ ቤቶችን፣ ሪዞርቶችን፣ የመንግሥት ተቋማትን እንዲሁም ሌሎች ህዝብ የሚበዛባቸውን ቦታዎችን ኢላማቸው ሊያደርጉ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።
ይህንን የአሜሪካ ኤምባሲን ማስጠንቀቂያ “ማስፈራሪያ እና ሽብር የሚፈጥር መግለጫ” ሲሉ ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸውታል። መግለጫው “ኢትዮጵያውያንን የማስፈራራት እና የዓለም ማህብረሰብ ኢትዮጵያ ሰላም የላትም እንዲል” ለማድረግ ያለመ እንደሆነም ተናግረዋል። የአሜሪካ ማስጠንቀቂያ “ ‘አዲስ አበባ ለሽብር ጥቃት የተጋለጠች ነች’ በማለት ባለሃብቶች፣ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ለማድረግ እና የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለማበላሸት ያለመ መግለጫ መሆኑን እንገልጻለን” ብለዋል።
“እንደዚህ አይነት ተግባራት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ህጎች እና ልማዶችን የሚጥሱ፤ የሁለቱን ሀገራት የቆየ ታሪካዊ፣ ሰላማዊ ግንኙነትን የሚንዱ እና የሚያበላሹ መሆኑን እየገለጽን፤ በዚህ አጋጣሚ የአሜሪካ መንግስትም ሆነ አዲስ አበባ ውስጥ ተቀማጭነቱን ያደረገው የአሜሪካ ኤምባሲ ከእንደዚህ አይነቱ አሸባሪ፣ አሳፋሪ እና ኃላፊነት የጎደለው መግለጫዎች ራሱን እንዲቆጥብ እናስጠንቅቃለን” ሲሉ አቶ ከበደ የኢትዮጵያን መንግስት አቋም አስታውቀዋል።
የአሜሪካ ኤምባሲ እና ተቋማት ጥንቃቄ እንዲደረግ ብለው በሚያወጧቸው “ከእውነት የራቁ” መግለጫዎች እና ማሳሰቢያዎች ብቻ ሳይወሰኑ፤ በተለያዩ ሌሎች መንገዶችም ጭምር “ጫናዎችን በማሳደር” ላይ እንደሚገኙ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል። የአሜሪካ መንግስት ተወካዮች እና አንዳንድ ግለሰቦች በተለያዩ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች ላይ “ጫና በማድረግ ላይ ይገኛሉ” ያሉት አቶ ከበደ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማትም መቀመጫቸውን እንዲቀይሩ ግፊት ያደርጋሉ ሲሉ ከስሰዋል።
“የዓለም ትላልቅ ድርጅቶች፣ የአፍሪካ ህብረት ዋና ጽህፈት ቤት እዚህ መሆኑ ይታወቃል። የተለያዩ የተባበሩት መንግስታት ተቀማጭነታቸውን እዚህ ያደረጉ ተቋማት አሉ። እነዚህ ኢትዮጵያን ለቅቀው እንዲወጡ እና ወደሌላ ሀገራት እንዲሄዱ፣ relocate እንዲያደርጉ ጫናዎችን ሲያሳድሩ ቆይተዋል” ብለዋል።
ይህንን ዓላማቸውን ለማሳካት ይረዳቸው ዘንድም፤ በኢትዮጵያ ላይ በተለይም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ሰበብ “ቅሬታ ያላቸውን ሀገራት በማሰባሰብ እና በማስተባበር” ተቋማቱ መቀመጫቸውን ከአዲስ አበባ እንዲቀይሩ “ጉትጎታቸውን ቀጥለዋል” ሲሉ አብራርተዋል። ጉዳዩን “ተገቢ ያልሆነ፣ ኃላፊነት ከሚሰማው ግለሰብ እና ተቋም የማይጠበቅ” ሲሉ የነቀፉት አቶ ከበደ፤ ይህን የሚያደርጉ ወገኖች “ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እናሳስባለን” ብለዋል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ዘግየት ብሎ ተጨማሪ መረጃ ታክሏል]