የሽግግር መንግሥት እንመሰርታለን በሚሉ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ታዘዘ

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከሚፈቅደው ውጪ የሽግግር መንግሥት ወይም ሌላ ሕገ ወጥ ቅርጽ ያለው መንግሥት እንመሠርታለን ብለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ አካላት ላይ የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ታዘዘ። የጸጥታ አካላት እርምጃውን እንዲወስዱ ትዕዛዝ የሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ነው። 

ዕዙ ትዕዛዙን ያስተላለፈው ዛሬ ሐሙስ ህዳር 16 ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ በዛሬው ዕለት ባደረገው ስብሰባ አዋጁን የተመለከቱ ወቅታዊ ሁኔታዎችን መገምገሙን አስታውቋል። በግምገማው ላይ በመመስረትም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር እና “ዕንቅፋት ናቸው” ያላቸውን ችግሮች ለማስወገድ አራት ትዕዛዞችን ማስተላለፉን ገልጿል። 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ይፋ ካደረጋቸው ትዕዛዞች መካከል፤ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን፣ የጦር ሜዳ ውሎዎችን እና ውጤቶችን በተመለከተ መረጃ ማሰራጨትን የተመለከተው ይገኝበታል። ወታደራዊ እና የጦርነት መረጃዎችን በተመለከተ በዕዙ ሥልጣን ከተሰጠው አካል ውጪ በየትኛውም የመገናኛ አውታር መግለጫ መስጠት እና ማሰራጨት ክልክል መሆኑን ዕዙ አስታውቋል።  

“በየግንባሩ የሚገኙ የሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች ከተሰጣቸው ሥምሪትና ተልእኮ ውጭ፤ ማንኛውንም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን፣ የጦር ሜዳ ውሎዎችን እና ውጤቶችን የሚመለከቱ  መግለጫዎች መስጠት የተከለከለ ነው። የጸጥታ አካላትም ይሄን ተላልፈው በሚገኙት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ታዟል” ሲል ዕዙ በመግለጫው አስፍሯል።

በዛሬ መግለጫ የተላለፈው ሌላኛው ትዕዛዝ ከጸጥታ ኃይሎች የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ነው። “የመለዮ ለባሾች ዩኒፎርም የራሱ የሆነ የአለባበስ ሕግና ሥርዓት አለው” ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ፤ “ከዚህ ሕግና ሥርዓት ውጭ የመለዮ ለባሾችን ዩኒፎርም ለብሶ መገኘት የተልዕኮ አፈጻጸሙን እያወከ እንደሚገኝ ጠቅሷል።

በዚህም ምክንያት “በማንኛውም ሁኔታ፣ ቦታና ጊዜ የመከላከያ ሠራዊትን፣ የፌዴራል ፖሊስን፤ የክልል ልዩ ኃይሎችንና የመደበኛ ፖሊስን ዩኒፎርሞች፣ የጸጥታ አካላት አባል ያልሆነ ማንኛውም ሰው ለብሶ መገኘት ፈጽሞ የተከለከለ መሆኑን አስታውቋል። “የተቋማቱ አባል ሳይሆን እና የታደሰ መታወቂያ ሳይዝ ዩኒፎርሙን ለብሶ በተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ፤ የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ታዟል” ሲል ዕዙ በመግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል።

በዕዙ መግለጫ በአራተኝነት የተቀመጠው ትዕዛዝ፤ በሽብርተኛ ቡድንነት ለሚታወቅን አካል ድጋፍ መስጠትን የሚከለክል ነው። “የሃሳብ ነጻነትን ሰበብ በማድረግ ልዩ ልዩ የሚዲያ አውታሮችን በመጠቀም፣ የሽብር ቡድኑን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በመደገፍ በህልውና ዘመቻው ላይ ዕንቅፋት የሚፈጥሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ አስጠንቅቋል። ይህንን ማስጠንቀቂያ ተላልፈው ከድርጊታቸው በማይቆጠቡ አካላት ላይ የጸጥታ ኃይሎች “ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ” መታዘዙን ጨምሮ ገልጿል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም የመከታተል እና በበላይነት የመምራት ስልጣን የተሰጠው አካል ነው። ዕዙ በኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የሚመራ ሲሆን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው። (በተስፋለም ወልደየስ- ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)