የኢትዮጵያ ሰራዊት ጭፍራ እና ቡርቃን ዛሬ እንደሚቆጣጠር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ሰራዊት በአፋር ግንባር የሚገኙትን ጭፍራ እና ቡርቃን በዛሬው ዕለት እንደሚይዝ ተናገሩ። ሰራዊቱ በዚያው ግንባር የሚገኘውን የካሳጊታን አካባቢ መቆጣጠሩን አስታውቀዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት፤ በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (OBN) ዛሬ አርብ ከሰዓት በሰበር ዜና በቀረበ መልዕክታቸው ነው። የወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሰው በቴሌቪዥን የታዩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አብረዋቸው የሚገኙት የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት “ከፍተኛ ድል” ማስመዘገባቸውን ተናግረዋል። 

“የምንፈልገው እኛ ሞተን የምትቆይ ኢትዮጵያን ማየት ነው። የምንፈልገው ወይም ኢትዮጵያዊ መሆን ነው፤ ወይም ኢትዮጵያ መሆን ነው። ይሄን ደግሞ በድል እንደምናሳካ እርግጠኛ [ነን]” ያሉት አብይ፤ ህዝቡ ከጎናቸው መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ወደ ጦር ሜዳ ለመሄድ መወሰናቸውን ያስታወቁት ባለፈው ሰኞ ህዳር 13፤ 2014 ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦር ግንባር መሄዳቸው ከተነገረ በኋላ በቴሌቪዥን ሲታዩ የዛሬው የመጀመሪያቸው ነው። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)