ከህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ነጻ በወጡ አካባቢዎች የሰዓት እላፊ ታወጀ

ከህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ነጻ በወጡ አካባቢዎች ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 12 ሰዓት ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ የሰዓት እላፊ መታወጁን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ መምሪያ አስታወቀ። የሰዓት እላፊው የታወጀው በአካባቢዎቹ ሰላምንና ጸጥታን ለማስፈን እንዲሁም የሕዝብንና የንብረትን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል እንደሆነም ገልጿል። 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ መምሪያው ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፤ ዛሬ ረቡዕ ማምሻውን ካደረገው ስብሰባ በኋላ ነው ተብሏል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም ለመገምገም በተደረገው በዚህ ስብሰባ፤ ዕዙ ከሰዓት እላፊው በተጨማሪ ሶስት ትዕዛዞችን ማስተላለፉ ተነግሯል።

ትዕዛዞቹ የመንግስት ኃይሎች ያስመዘገቧቸውን ድሎች “ጠብቆ ለማስቀጠል እንዲቻል” የሚያግዙ መሆናቸውን ዕዙ በዛሬ መግለጫው ጠቅሷል። በዚህም መሰረት ዕዙ፤ ከህወሓት ኃይሎች እጅ ነጻ በወጡ አካባቢዎች የታወጀውን የሰዓት እላፊ የማስፈጸም ስልጣን የሰጠው ወደ አካባቢዎቹ ለገቡ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ነው።

የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በአማራ ክልል መንግስት ከሚመደብ የሲቪል አስተዳደር ጋር በመሆን “ጥምር ኮሚቴ” “በአስቸኳይ” እንዲያቋቁሙም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ መምሪያው ትዕዛዝ ሰጥቷል። ጥምር ኮሚቴው በአማጽያኑ ኃይሎች አማካኝነት ተፈጽመዋል የተባሉ “ሰብአዊና ቁሳዊ  ውድመትን የሚያሳዩ ማስረጃዎች”፤ “እንዳይጠፉ፣ እንዲጠበቁ፣ በተገቢው መንገድ እንዲመዘገቡ እና ማስረጃዎችም እንዲሰነዱ” የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎበታል። 

በየአካባቢው የሚቋቋሙት እነዚህ ጥምር ኮሚቴዎች የሚያሰባስቧቸውን ማስረጃዎች፤  ለፍትሕ አካላት እንዲሰጡ ትዕዛዝ  ተላልፎላቸዋል።  የፍትሕ አካላት የሚቀበሏቸውን ማስረጃዎች አደራጅተው “ለሚመለከተው አካል” እንዲያስረክቡም  ታዝዘዋል።  (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)