የመንግስት ኃይሎች 11 ከተሞችን መልሰው መቆጣጠራቸው ተነገረ

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራው የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት ከሚሴ እና ተንታን ጨምሮ በአማጽያን ቁጥጥር ስር የነበሩ 11 ከተሞችን ነጻ ማውጣቱን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ። ጥምር ጦሩ ኮምቦልቻን ለመያዝ “በመገስገስ ላይ” እንደሚገኝም ገልጿል። 

በመንግስት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው የተነገረላቸው ከተሞች በሶስት የጦር ግንባሮች የሚገኙ ናቸው። ለአዲስ አበባ ቅርበት ባለው ግንባር፤ ከመዲናዋ 325 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ከሚሴን ጨምሮ ስድስት ከተሞች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸውን የመንግሥት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ቅዳሜ ህዳር 25 ምሽት ይፋ አድርጓል። 

በዚህ ግንባር ከአማጽያን እጅ ነጻ የወጡት ሌሎች ከተሞች ጭረቲ፣ ርቄ፣ ወለዲ እና አልቡኮ ከተሞች መሆናቸውን የኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤቱ አስታውቋል። ከከተሞቹ በተጨማሪ የቃሉ ወረዳ አብዛኛው ክፍል በጥምር ጦሩ መያዙንም አክሏል። የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት ቀጣይ መዳረሻ የኢንዱስትሪ ከተማ የሆነችው ኮምቦልቻ እንደሆነችም ጠቁሟል።  

በወረኢሉ ግንባር በተደረገው ወታደራዊ ዘመቻ አጅባር፣ ተንታ፣ ዶባ ከተሞች እና አካባቢያቸውን የመንግስት ኃይሎች ከአማጽያን ማስለቀቃቸውን የመንግሥት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል። ባለፈው ረቡዕ የመከላከያ ሰራዊት “ከፍተኛ ድል” ማስመዘገቡ በተገለጸበት በጋሸና ግንባርም፤ ተጨማሪ ቦታዎች ከአማጽያን ኃይሎች ነጻ መደረጋቸውን በዛሬው መግለጫ ተጠቅሷል። 

በጋሸና ግንባር የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ዛሬ እንደተቆጣጠሯቸው የተገለጹ ቦታዎች ቀውዝባ እና ጭላ ከተሞች እንዲሁም በዙሪያቸው ያሉ አካባቢያዎችን ነው። ዛሬ እና ትላንት በተደረጉት ከፍተኛ የማጥቃት ኦፕሬሽኖች አብዛኛው የአማጽያኑ ኃይል “ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲበተን ተደርጓል” ያለው የመንግሥት የኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤት፤ ጥምር ጦሩ በአሁኑ ወቅት የተበተነውን ኃይል “በመልቀም ላይ” እንደሚገኝ አብራርቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)