የደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ዋሉ

የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ኃይሎች ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በአማጽያን ቁጥጥር ስር የነበሩትን የደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን መልሰው መቆጣጠራቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ። የኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤቱ ዛሬ ሰኞ ምሽት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን የምትገኘው የባቲ ከተማም ከአማጽያኑ ነጻ ወጥታለች። 

የባቲ ከተማ በምትገኝበት የምሥራቅ ግንባር ስር ያሉት የቀርሳ፣ ገርባ እና ደጋን አካባቢዎች የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እንደተቆጣጠሯቸው በምሽቱ መግለጫ ተነግሯል። በሐርቡ ግንባር የተሰማሩት የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ቃሉ ወረዳን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውንም የኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤቱ አክሎ ገልጿል።   

“ስትራቴጂካዊ” እንደሆነች የሚነገርላት የደሴ ከተማ፤ የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር መቀመጫ ነች። ከደሴ በቅርበት ርቀት የምትገኘው ኮምቦልቻ በውስጧ በየያዘቻቸው ኢንዱስትሪዎች ይበልጥ የምትታወቅ ሲሆን ለአካባቢው አገልግሎት የሚሰጥ የአየር ማረፊያም በከተማዋ ይገኛል። የኮምቦልቻ ከተማ የወሎ አካባቢን ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኝ አውራ ጎዳና የሚያልፍባት እና የደረቅ ወደብ አገልግሎት የሚሰጥባት ከተማም ናት። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)