ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አብዛኛው የአማራ ክልል “ነጻ ወጥቷል” አሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አብዛኛው የአማራ ክልል ከአማጽያን ቁጥጥር ነጻ መሆኑን አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በክልሉ ስር ያሉት ሸዋ፣ ደቡብ ጎንደር እና የከሚሴ ልዩ ዞን ዛሬ “ሙሉ በሙሉ” እንዲሁም የወሎ አካባቢዎች ደግሞ “በከፊል” ነጻ ወጥተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን ያሉት ዛሬ ሰኞ ህዳር 27 ምሽት በብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈ መልዕክታቸው ነው። የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቀይ መለዮ ለባሽ በሆኑ ኮማንዶዎች ፊት ቆመው ባደረጉት ንግግር “የቀሩትን በጣም ጥቂት ቦታዎች በጥቂት ቀናት ነጻ እናወጣለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

አብዛኛው የደቡብ ወሎ አካባቢዎች ነጻ መውጣታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ “የቀሩ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች [ላይ] ኦፕሬሽኑ ይቀጥላል” ብለዋል። የመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ከሰሞኑ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና በከሚሴ ከፍተኛ ድል ማስመዝገባቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የተገኘው ድል ለማመን ይከብዳል” ሲሉ በኮምቦልቻ ከተማ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው መግለጫቸው የአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ነጻ መውጣቱንም ጨምረው ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦር ግንባር ከሄዱ በኋላ ህዳር 17፤ 2014 ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት መግለጫ ነበር በአፋር ክልል የሚገኘው የካሳጊታ አካባቢ ከአማጺያኑ ነጻ መውጣቱን ያስታወቁት። በክልሉ የሚገኙት የጭፍራ እና ቡርቃ ከተሞችም በተመሳሳይ ቀን በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጾ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)