የኢትዮጵያ መንግስት በመላ ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከደነገገ ወዲህ “የትግራይ ብሔር አባላትን በብዛት እያሰረ ነው” በሚል አሜሪካ እና ብሪታኒያን ጨምሮ በስድስት ሀገራት የቀረበበትን ውንጀላ አጣጣለ። ለሀገራቱ ውንጀላ ይፋዊ ምላሽ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ናቸው።
የፕሬስ ሴክሬታሪዋ ዛሬ ማክሰኞ ህዳር 28 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሀገሪቱ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ “የተወሰኑ ሰዎችን በብሔራቸውም ሆነ ጥበቃ በሚደረግለት እና አባል በሆኑበት አንዳች ቡድን ላይ ያነጣጠረ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል። አሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ እና ኔዘርላንድስ በትላንትናው ዕለት በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ “የኢትዮጵያ መንግስት ‘ብዛት ያላቸው የሀገሪቱን ዜጎች ብሔርን መሠረት በማድረግ ያለ ክስ እያሰረ ነው’ በሚል የወጡ ሪፖርቶች” እንደሚያሳስቧቸው ገልጸው ነበር።
ስድስቱ ሀገራት ለዚህ ስጋታቸው በአስረጂነት የጠቀሱት፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል በጉዳዩ ላይ ከዚህ ቀደም ያወጧቸውን ሪፖርቶች ነው። ሁለቱ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በተለያዩ ጊዜያት ባወጧቸው መግለጫዎች፤ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት፣ አዛውንቶች፣ ልጆች የያዙ እናቶችን ጨምሮ በርካታ የትግራይ ብሔር ተወላጆች መታሰራቸውን ይፋ አድርገው ነበር።
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኩል ትላንት የወጣው የስድስቱ ሀገራት መግለጫ፤ “የኢትዮጵያ መንግስት የደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተወሰኑ ብሔር አባላት የሆኑ ሰዎችን በጅምላ ለማሰር ምክንያት አይሆንም” ሲል ተቃውሟል። የኢትዮጵያ መንግስት “የሃገር ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል” በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገው ጥቅምት 23፤ 2014 ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ በዛሬው መግለጫቸው፤ በኢትዮጵያ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ “የአንድ ብሔር አባላት ላይ ያነጣጠረ ነው” ብሎ ማቅረብ የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን “አሉታዊ ትርክትን ማስፋፋት ነው” ሲሉ ተችተዋል። “በተጨባጭ ማስረጃ፣ ምስክርነት እና ለጸጥታ አስከባሪዎች የተሰጡ ጥቆማዎችን መሠረት በማድረግ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሰሩ በርካታ ሰዎች አሉ” ያሉት ቢልለኔ፤ የጸጥታ አስከባሪዎች ተገቢውን ምርመራ ካደረጉ በኋላ በቁጥጥር ስር ያዋሏቸውን ሰዎች መፍታታቸውንም አስረድተዋል።
“ይህ ህጋዊ መንግስት ነው። መንግስታዊ ሥርዓቱ በአግባቡ መጠበቁን ለማረጋገጥ ማናቸውም የጸጥታ እርምጃዎች ተግባራዊ ሲያደርግ በህገ-መንግሥታዊው ሂደት ስር የሚያልፍ መንግስት ነው” ያሉት የፕሬስ ሴክሬታሪዋ፤ “በዚህ ላይ የሚደረግ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እንደተጋፋ ይቆጠራል” ብለዋል።
ቢልለኔ ስዩም በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ከምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ ለተሰነዘረው ወቀሳ ምላሽ ከመስጠት ባሻገር ሌሎች ጉዳዮችንም አብራርተዋል። የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በአውደ ውጊያዎች ያገኟቸው ድሎች፣ በጦርነቱ ምክንያት በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት፣ በአማራ፣ በአፋር እና ትግራይ ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት፤ በፕሬስ ሴክሬታሪዋ ማብራሪያ የቀረበባቸው ጉዳዮች ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ የጦር ግንባሮች “ከፍተኛ ድሎች” በማስመዝገብ ላይ እንዳለ ከሰሞኑ ሲገልጽ ሰንብቷል። በትላንትናው ዕለትም የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር መቀመጫ የሆነችው ደሴ ከተማን፣ የኢንዱስትሪ እና የንግድ ኮሪዶር የሆነችውን ኮምቦልቻን ጨምሮ በአማራ ክልል የሚገኙ በርካታ አካባቢዎች ከትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ነጻ መውጣታቸውን አስታውቆ ነበር።
“የትላንቱ ሽንፈት በአሁኑ ጊዜ በችግር ውስጥ ለሚገኘው የአሸባሪው ቡድን ከባድ ጉዳት ነው” ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ፤ በህወሓት የሚመሩት የትግራይ ኃይሎች በጦር አውድማዎች ለገጠማቸው ሽንፈት “አስተዋጽኦ አበርክቷል” ያሉትንም ጉዳይ አያይዘው አንስተዋል። አማጽያኑ 12 ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦቻቸው በአውደ ውጊያ ተገድለውባቸዋል መባሉ በጦር ግንባሮች ለደረሰባቸው ሽንፈት በምክንያትነት ተጠቅሷል።
ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ትላንት ሰኞ በትዊተር ባሰፈሩት አጭር መልዕክት “ሰሜን ሸዋ፣ ኮምቦልቻ እና ደሴን የለቀቅነው በዕቅዳችን መሠረት ነው“ በማለት የኢትዮጵያ መንግስት በጦር ግንባሮች አገኘሁ ያለውን ድል አስተባብለውል። አቶ ጌታቸው “እነዚህን ከተሞች ነጻ የሚያወጣ የተደራጀ ኃይል የለም” ሲሉም በትዊተር መልዕክታቸው አስፍረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ግን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከአማራ እና አፋር ክልል አጋሮቻቸው ጋር ያደረጉት ግስጋሴ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል መንግስት ኃይሎች ላደረጉት ስልታዊ ዝግጅት “ምስክር ነው” ሲሉ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ተናግረዋል። ቢልለኔ “ባለፉት ሁለት ሣምንታት ውስጥ የተገኘው ውጤት ስለ ራሱ ይናገራል” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)