ምርጫ ቦርድ 51 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ አለማድረጋቸውን አስታወቀ

በሃሚድ አወል

በህጋዊነት ከተመዘገቡ 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል፤ ከምርጫ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ ያደረጉት ሁለት ፓርቲዎች ብቻ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ጠቅላላ ጉባኤ ያላደረጉ ሁሉም ፓርቲዎች፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተጠናቀቀ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጉባኤያቸውን እንዲያከናውኑ ቦርዱ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ውሳኔ ማስተላለፉን ገልጿል።  

ምርጫ ቦርድ ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ባሳለፈው ውሳኔ፤ ከምርጫ ህግ መሻሻል በኋላ በአዲስ መልክ የተመዘገቡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያደርጉ ወስኖ ነበር። ሆኖም ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ በመቃረቡ፤ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄዱ ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለቦርዱ ጥያቄ አቅርበዋል።  

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለጥያቄያቸው ያቀረቡት ምክንያት “ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ በምርጫ እንቅስቃሴ ዝግጅት ላይ ጫና ይፈጥርብናል” የሚል ነበር። ፓርቲዎቹ ያቀረቡትን ጥያቄ በጥር 2013 ባካሄደው ስብስባ የመረመረው ምርጫ ቦርድ፤ የጥያቄውን ምክንያት ከግምት ውስጥ ማስገባቱን ጠቅሶ ፓርቲዎቹ ሀገራዊ ምርጫው በተጠናቀቀ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲያካሄዱ ቀነ ገደብ ሰጥቷል። 

ምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎቹ ተለዋጭ ጊዜ ቢሰጥም፤ በሰኔ 2013 የተካሄደው ምርጫ ከተጠናቀቀ ከሶስት ወራት በኋላም ገዢው ብልጽግና ፖርቲን ጨምሮ 51 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን አለማካሄዳቸውን ከቦርዱ የተገኘ መረጃ አመልክቷል። ቦርዱ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ህዳር 23፤ 2014 ከፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ባደረገው ምክር የጠቅላላ ጉባኤ ጉዳይ በዋነኛነት ተነስቷል። 

በስብሰባው የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንዳሉት፤ ፓርቲዎቹ ጠቅላላ ጉባኤ ላለማድረጋቸው በዋነኛነት የጠቀሷቸው ሁለት ምክንያቶችን ነው። በፓርቲዎቹ የተነሳው የመጀመሪያው ምክንያት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ አለመቻላቸውን እንደሆነ ስብሰባውን የተካፈሉት የኢዜማ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አንድነት ሽፈራው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ከአንድ ወር በፊት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ የአዋጁን አፈጻጸም ለመከታተል እና በበላይነት ለመምራት የተዋቀረው የመምሪያ ዕዝ በተዋረድ ውክልና ከሰጣቸው አካላት ፈቃድ ውጪ “ማንኛውንም የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የተከለከለ” መሆኑን ደንግጓል። የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የደነገገው “የሃገር ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል” እንደሆነ ማስታወቁ አይዘነጋም። 

በምርጫ ቦርድ ስብሰባ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሁለተኛ ምክንያትነት የጠቀሱት ጉዳይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለመደንገጉ ምክንያት ከሆነው “የሃገር ህልውና” ጋር የተያያዘ ነው። እንደ አቶ አንድነት ገለጻ፤ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ለመሳተፍ ወደ ጦር ግንባር በመሄዳቸው ጠቅላላ ጉባኤ አለመቻላቸውን በስብሰባው የገለጹ ፓርቲዎች ነበሩ። 

አባላቶቻቸው ወደ ጦር ግንባር ከሄዱባቸው ፓርቲዎች መካከል ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አንዱ ነው። የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዘቢባ ኢብራሂም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት የባልደራስ የተወሰኑ አባሎች “በገዛ ፍቃዳቸው ወደ ጦር ግንባር በመሄዳቸው” ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን እንዳቀደው ማድረግ አልቻለም። 

የፓለቲካ ፓርቲዎች በስብሰባው ላይ ያቀረቧቸውን ምክንያቶች ያደመጡት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ እና ምክትላቸው ውብሸት አየለ፤ ቦርዱ በጉዳዩ ላይ በቀናት ውስጥ ውሳኔ እንደሚሰጥ አስታውቀው ነበር። በዚህም መሰረት ቦርዱ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ህዳር 27 ባስተላለፈው ውሳኔ፤ ጠቅላላ ጉባኤ ያላደረጉ ሁሉም ፓርቲዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተጠናቀቀ በአንድ ወር ውስጥ ጉባኤያቸውን አከናውነው እንዲያሳወቁ” አሳስቧል። በጥቅምት 23፤ 2014 የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚ ሆኖ የሚቆየው ለስድስት ወራት መሆኑን በወቅቱ ተገልጿል። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ቢያንስ በሶስት ዓመት አንድ ጊዜ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ይደነግጋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከምዝገባ ከሚያሰርዙ ምክንያቶች መካከል ጠቅላላ ጉባኤያቸውን በተቀመጠው ጊዜ አለማድረግ አንደኛው ነው። 

በአዋጁ መሰረት “የፖለቲካ ፓርቲው የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ ከሚገባው በሶስት ወር የዘገየ እንደሆነ እና ከዚህ በኋላ ቦርዱ በሚሰጠው የጊዜ ገደብ ጉባኤውን ሳይካሂድ የቀረ እንደሆነ” ከምዝገባ ሊሰረዝ ይችላል። ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያካሄዱ ሰጥቶት የነበረው የሶስት ወራት የጊዜ ገደብ የተጠናቀቀው ባለፈው መስከረም ወር ነበር።   

የቦርዱ ኮሚዩኒኬሽን ክፍል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንዳስታወቀው፤ ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ ያደረጉት ሁለት ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (አብአፓ) ናቸው። አብአፓ ነሐሴ 27፣ 2013 ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤው የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻሉን፣ የጉባኤውን አባላት ቁጥር ከፍ ማድረጉን እና የአዲስ አመራሮች ምርጫ ማካሄዱን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሄር “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ጠቅላላ ጉባኤውን ባለፈው መስከረም ወር ያደረገው ኢዜማም የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ አሻሽሏል። ምርጫ ቦርድ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ባሳለፈው ውሳኔ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ከማካሄድ ባለፈ የመተዳደሪያ ደንባቸውን እንዲያስተካክሉ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። 

ኢዜማ በመስከረሙ ጠቅላላ ጉባኤው ተወያይቶ በአብላጫ ድምጽ ያጸደቀው ሌላው ጉዳይ፤ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ የአብረን እንስራ ጥያቄን ነበር። ይህን የፓርቲውን ውሳኔ ተከትሎ የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ን ጨምሮ የተወሰኑ የኢዜማ አመራሮች የተለያዩ መንግስት ተቋማትን የመምራት ኃላፊነት ተረክበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)