ተመድ ከሸዋሮቢት፣ ወልዲያ፣ ላሊበላ እና ምዕራባዊ ትግራይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል አለ

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ በአማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች አሁንም ነዋሪዎች እየተፈናቀሉ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ። የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪች እንደተናገሩት፤ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ስር ከምትገኘው የሸዋሮቢት ከተማ የተፈናቀሉ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ አፋር ክልል ገብተዋል።

ዱጃሪች ይህን ያሉት ትላንት ሐሙስ ህዳር 30፤ 2014 በሰጡት ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮን የጠቀሱት ዱጃሪች፤ በአማራ ክልል ከሚገኙት ከወልዲያ እና ከላሊበላ ከተሞችም በርካታ ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውን አስረድተዋል። 

ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በአማጽያን ተይዛ የቆየችው ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ፤ በመንግስት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መልሳ የገባቸው ባለፈው ሳምንት ነበር። ከአዲስ አበባ 516 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው እና የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር መቀመጫ የሆነችው ወልዲያ፤ እስከ ዛሬ አርብ ድረስ በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከሚገኙ የአማራ ክልል ከተሞች አንዷ ናት።

በትላንቱ የተመድ ቃል አቃባይ መግለጫ በተጠቀሱት ሶስት የአማራ ክልል ከተሞች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ቁጥር አስር ሺህዎች መሆናቸው ቢነገርም የኢትዮጵያ መንግስት ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በክልሉ በአጠቃላይ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፤ በአማራ ክልል 1.4 ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸውን ተናግረው ነበር።

የተፈናቃዮቹ ቁጥር ባለፈው ሳምንት በፕሬስ ሴክሬታሪዋ ተመሳሳይ መግለጫ ይፋ ከተደረገው በ300 ሺህ ከፍ ያለ ነው። በአፋር ክልል በጦርነቱ ምክንያት 400 ሺህ ገደማ ሰዎች መፈናቀላቸውንም ቢልለኔ አስታውቀዋል።  

የተመድ ቃል አቃባይ በትላንቱ መግለጫቸው በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታም አንስተዋል። እንደ ዱጃሪች ገለጻ ከምዕራብ ትግራይ ዞን የተፈናቀሉ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በክልሉ ስር ወዳለው ሰሜን ምዕራብ ዞን ሸሽተዋል። ወደ ትግራይ ክልል በቅርቡ የገቡትን እነዚህን ተፈናቃዮች ጨምሮ 43 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች የረድኤት ድርጅቶች ከህዳር 16 እስከ ህዳር 22 ባሉት ቀናት የምግብ እርዳታ ማከፋፈላቸውንም ጠቅሰዋል።    

ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ህዳር 22 ጀምሮ ባለው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ፤ ምግብ፣ ውሃ እና የንጽህና መጠበቂያዎችን የጫኑ 44 ተሽከርካሪዎች በአፋር ክልል በኩል ወደ መቀሌ መግባታቸውንም ገልጸዋል። የዚህ ሳምንቱ የተሽከርካሪዎች ቁጥር፤ ባለፈው ሳምንት ወደ ስፍራው ከተጓዙት 157 እርዳታ ጫኝ መኪናዎች እና በየቀኑ ወደ ክልሉ መጓጓዝ ነበረባቸው ከሚባሉት 100 ተሽከርካሪዎች ጋር ሲነጻጸር  “በጣሙኑ ያነሰ” መሆኑን ቃል አቃባዩ አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)