ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ የታሰረበትን ቦታ ማወቅ እንዳልቻሉ ቤተሰቦቹ ገለጹ

በተስፋለም ወልደየስ

በትላንትናው ዕለት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ፤ የታሰረበትን ቦታ እስካሁንም ማወቅ አለመቻላቸውን ቤተሰቦቹ ገለጹ። የጋዜጠኛው ጉዳይ “ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን” ተዛውሯል ቢባልም፤ ከክልሉ ፖሊስ በኩል በቂ መረጃ የሚሰጣቸው አካል አለማግኘታቸውን ቤተሰቦቹ ተናግረዋል። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ግን ስለ ጉዳዩ እንደማያውቁ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምላሽ ሰጥተዋል።  

“ተራራ ኔትወርክ” የተባለው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ባለቤት እና ዋና አዘጋጅ የሆነው ታምራት፤ ትላንት አርብ ታህሳስ 1፤ 2014 ከመኖሪያ ቤቱ የተወሰደው “ለጥያቄ ትፈለጋለህ” በሚል እንደነበር ቤተሰቦቹ ተናግረዋል። ከረፋዱ አራት ሰዓት ተኩል ገደማ ጋዜጠኛውን በቁጥጥር ስር ያዋሉት የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ አምስት ፖሊሶች እንደነበሩ የሚናገሩት ባለቤቱ ሰላም በላይ፤ ሲቪል የለበሱ ስድስት ሰዎችም የመኖሪያ ቤቱ ሲፈተሽ አብረው እንደነበሩ ገልጸዋል። 

በታምራት መኖሪያ ቤት እና በ“ተራራ ኔትወርክ” ዝግጅት ክፍል ከተደረገ ፍተሻ በኋላ፤ ጋዜጠኛው የተወሰደው በተለምዶ ሶስተኛ ተብሎ ወደሚጠራው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ጽህፈት ቤት እንደነበር እንደተነገራቸው ባለቤቱ አብራርተዋል። ሆኖም ለጥየቃ ወደ ስፍራው ያመሩት ቤተሰቦቹ፤ ጋዜጠኛው በሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደሌለ እና ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ መዛወሩን መስማታቸውን አክለዋል። 

ጋዜጠኛው ያለበትን ለማወቅ በአዲስ አበባ ከተማ ስድስት ኪሎ አካባቢ ወደሚገኘው የኦሮሚያ ፖሊስ ካምፕ ትላንት አመሻሹን ያመሩት ቤተሰቦቹ፤ በዚያም እንደሌለ እንደተነገራቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ወደዚሁ ቦታ ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ቢሄዱም ተመሳሳይ ምላሽ ማግኘታቸውንም አስረድተዋል።

የታምራት ደብዛ መጥፋት ያሳሰባቸው ባለቤቱ ዛሬ ረፋዱን ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሄደው ጋዜጠኛው ያለበትን ቦታ ለማወቅ በድጋሚ ጥያቄ አቅርበዋል። የኮሚሽኑ ባልደረቦች ታምራት “መጀመሪያውኑ የተፈለገው በኦሮሚያ ፖሊስ መሆኑን”፤ እንዲሁም የተፈለገበትን ጉዳይ እንደማያውቁ ጭምር እንደገለጹላቸው ጠቅሰዋል። በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታን ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም፤ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም።

የታምራት ቤተሰቦች ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተጨማሪ ግሎባል ሆቴል አካባቢ ወደሚገኘው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት በዛሬው ዕለት የሄዱ ሲሆን በዚያም ጋዜጠኛው የታሰረበትን ቦታ የሚነግራቸው አካል ሳያገኙ ቀርተዋል። ጋዜጠኛው “በቡራዩ አሊያም ገላን ፖሊስ ጣቢያዎች ታስሮ ሊሆን ይችላል” በሚል የደረሳቸውን ጥቆማ ተከትለው ቤተሰቦቹ በአካባቢዎቹ በሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎች ቢያጠያይቁም ጋዜጠኛውን በዚያም ሊያገኙት አለመቻላቸውን ተናግረዋል። 

ጋዜጠኛው በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ቁጥጥር ስር ይኖር እንደው ለማጣራት ዛሬ ረፋዱን ሜክሲኮ አካባቢ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ያመሩት ወዳጆቹ በቢሮው በሚገኘው የእስረኞች ማቆያ እንደሌለ ተነግሯቸዋል። 

ጋዜጠኛው በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ቁጥጥር ስር እንዳለ የተጠየቁት ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ መርዳሳ፤ “ሰውየውንም አላውቀውም። አሁን ነው ከአንተ የሰማሁት” ሲሉ ጥያቄውን ላቀረበላቸው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ምላሽ ሰጥተዋል። “የኦሮሚያ ፖሊስ ራሱን የቻለ ኮሚሽን ነው” ያሉት ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ፤ ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በኩል “ሰው አሳስሯል” የሚለው ጥያቄ በራሱ ትክክል እንዳልሆነ ተናግረዋል። 

ታምራት ነገራ በመስራችነት ያቋቋመው “ተራራ ኔትወርክ” ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ፍቃድ ያገኘው በግንቦት 2013 ዓ.ም. ነው። ታምራት በህዳር 2002 ዓ.ም. የተዘጋው የ“አዲስ ነገር” ጋዜጣ መስራቾች መካከል አንዱ ነው። ጋዜጠኛው ከዘጠኝ ዓመታት ገደማ የአሜሪካ የስደት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገሩ ተመልሶ “ተራራ ኔትወርክ”ን የመሰረተው ከአንድ ዓመት በፊት በመስከረም 2013 ዓ.ም. ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)