የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ልዩ ስብሰባ ሊያካሂድ ነው

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፤ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብት ሁኔታ የሚገመግም ልዩ ስብሰባ በመጪው አርብ ሊያካሂድ ነው። ልዩ ስብሰባው እንዲካሄድ ጥያቄ ያቀረቡት የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ የምክር ቤቱ አባላት እና ታዛቢዎች ናቸው።

ምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባዎቹን በአብዛኛው በመጋቢት፣ ሰኔ እና መስከረም ወራት የሚያካሄድ ቢሆንም፤ በአሳሳቢ የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ ላይ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባዎች የመጥራት አካሄድን ይከተላል። በዚህ አካሄድ መሰረትም፤ በኢትዮጵያ “አስከፊ” ደረጃ ላይ ደርሷል የተባለውን የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ የሚገመግም ስብሰባ፤ ምክር ቤቱ እንዲያደርግ ጥያቄ መቅረቡን የአውሮፓ ህብረት አስታውቋል።

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትን በፕሬዝዳንትነት ለሚመሩት የፊጂ አምባሳደር ናዛት ሻሚም ኻን ጥያቄውን ያቀረቡት፤ 17 የምክር ቤቱ አባላት እና 35 ታዛቢዎች መሆናቸውን ህብረቱ ገልጿል። ጥያቄ አቅራቢዎቹ ለናዛት ሻሚም በጻፉት ደብዳቤ “በሁኔታው ጠቃሚነት እና አንገብጋቢነት ምክንያት ልዩ ስብሰባ ያስፈልጋል” ብለዋል።

በአውሮፓ ህብረት ልዑክ የተረጋገጠ የትዊተር ገጽ በኩል ይፋ በሆነው እና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው ደብዳቤ፤ 52ቱ ሀገራት ልዩ ስብሰባ እንዲደረግ የቀረበውን ጥያቄ ለምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት አሳውቀው አስፈላጊው ዝግጅት እንዲደረግ ሃሳብ አቅርበዋል። የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በመጪው አርብ ታህሳስ 8፤ 2014 ከቀኑ 12 ሰዓት ጀምሮ ልዩ ስብሰባው እንደሚካሔድ በይፋዊ የትዊተር ገጹ በኩል አረጋግጧል።

ዋና ጽህፈት ቤቱን በስዊትዘርላንድ ጄኔቫ ከተማ ያደረገው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፤ በጠቅላላ ጉባኤው አብላጫ ድምጽ የሚመረጡ 47 አባላት አሉት። ከእነዚህ አባል ሀገራት መካከል 13 መቀመጫዎች ለአፍሪካ አህጉር የተደለደሉ ናቸው።

አፍሪካን ወክለው የምክር ቤቱ አባል ከሆኑ አገራት መካከል የኢትዮጵያ ጎረቤቶች የሆኑት ኤርትራ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ይገኙበታል። የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ይዞታ ለመገምገም አስቸኳይ ስብሰባ እንዲካሔድ ጥሪ ካቀረቡ 52 አገራት አንዳቸውም የአፍሪካ ተወካዮች አይደሉም።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በትግራይ ክልል ጦርነት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚመለከት ምርመራ ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር አከናውኖ ሪፖርት ማቅረቡ አይዘነጋም። ባለፈው ጥቅምት 24 ይፋ የተደረገው የምርመራ ሪፖርት በትግራይ ግጭት ተሳታፊ በሆኑ አካላት የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መፈጸማቸውን ይፋ አድርጓል። የሁለቱ ተቋማት ሪፖርት ይፋ ካደረጋቸው መካከል የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት የተፈጸሙ ወንጀሎች ይገኙበታል።

በመጪው አርብ ሊካሄድ የታቀደው ስብሰባ  የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ ከኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሞታል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ሰኞ ምሽት ባወጣው መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መቀመጫ በሆነችው ጄኔቫ እየሆነ ባለው ነገር “ግራ መጋባቱን እና ማዘኑን” በመግለጽ ለአባል አገራት ጥሪ አቅርቧል። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በጥምረት ምርመራ ማድረጋቸውን እና የተሰጡ ምክረ ሀሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት ቁርጠኝነቱን መግለጹን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውሷል። ልዩ ስብሰባውን የጠሩት ለኢትዮጵያ መንግስት “ጥረቶች እና ስራዎች ቁብ የሌላቸው የተወሰኑ የምክር ቤቱ አባላት” መሆናቸውን በመግለጫ የጠቆመው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ስብሰባውንም “ፖለቲካዊ ውጤት ለማምጣት የታቀደ” ሲል ነቅፎታል። የምክር ቤቱ አባላትም የስብሰባውን ውጤት በመቃወም ድምጽ እንዲሰጡ ጠይቋል። 

ኢትዮጵያ “ፍትሐዊ እና ጠቃሚ ያልሆነ፡ ፖለቲካዊ ጫና ሲገጥማት የመጀመሪያው እንዳልሆነ የጠቀሰው መግለጫው፤ ከዚህ ቀደም በ47ኛው የምክር ቤቱ ስብሰባ የጸደቀው የውሳኔ ሀሳብ ጉዳዩ የሚመለከተውን አገር ያላካተተ እንዲሁም የውሳኔ ሀሳቡ እንዳይቀርብ ሌሎች ያቀረቡትን ጥሪ ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደነበር አስታውሷል። 

ምክር ቤቱ “በሽብርተኛው ህወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና አስከፊ ድርጊቶች መመርመር ቀዳሚ ስራው መሆን ነበረበት” ሲልም ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አመልክቷል። ከምክር ቤቱ አባላት “እንዲህ አይነት ጥሪ አለመቅረቡ” አሳዛኝ መሆኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ አካሄዱ በአፋጣኝ መስተካከል እንደሚኖርበት ማሳሰቢያ ሰጥቷል። 

የኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ ተቃውሞውን ባቀረበበት በዚሁ መግለጫ ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግንኙነቱን ገንቢ በሆነ አካሔድ ለመቀጠል እና በዓለም አቀፍ ህግጋት ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር እና ለመጠበቅ የተጣለበትን ግዴታ ለማሟላት ቁርጠኝነቱን ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ዘግይቶ ታክሎበታል]