የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበር፤ የጋዜጠኞች እስር እየጨመረ መምጣቱ አሳስቦኛል አለ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጋዜጠኞች እስር እየጨመረ መሆኑ እንደሚያሳስበው ገለጸ። ማህበሩ ሀገር አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ባለድርሻዎች ውይይት ጉባኤ እንዲጀመርም ጠይቋል። 

የመገናኛ ብዙሃን ማህበሩ ይህን ያለው ሶስት ሰሞናዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 5፤ 2014 ባወጣው መግለጫ ነው። በኢትዮጵያ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና ሀገሪቱ ያለችበትን “ወቅታዊ ችግር” እንደሚገነዘብ የገለጸው ማህበሩ፤ ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ የመጣው የጋዜጠኞች እስር አሳሳቢ መሆኑን አስታውቋል።   

“ከሰሞኑ ጋዜጠኞች በትክክል ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ለእስር መዳረጋቸው፤ እየታየ የነበረውን የጋዜጠኝነት ትግበራ ነጻነት ወደፊት ጥላ እንዳያጠላበት ያሳስበናል” ብሏል የባለሙያዎች ማህበሩ። ማህበሩ በዚሁ መግለጫው በህግ ጥላ ስር ያሉ ጋዜጠኞች ያሉበት ሁኔታ በቤተሰቦቻቸው አለመታወቁንም አውግዟል።

ጋዜጠኞቹ ያሉበት ቦታ አለመታወቁ፤ “ተገቢው የህግ ከለላ እና ፍትህ” እንዳያገኙ እንደሚያደርጋቸውም ማህበሩ በመግለጫው ጠቅሷል። የሚመለከተው የመንግስት አካል፤ በጸጥታ አካላት የተያዙት ጋዜጠኞች የህግ ድጋፍ የማግኘት መብታቸው እንዲጠበቅ እና በቤተሰቦቻቸው የመጎብኘት መብታቸው እንዲከበር እንዲያደርግም ማህበሩ ጥሪ አቅርቧል።

የማህበሩ መግለጫ የወጣው በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሶስት የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚሰሩ ጋዜጠኞች በፖሊስ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ነው። ባለፈው ሳምንት በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉት ሶስት ጋዜጠኞች እያስፔድ ተስፋዬ፣ ታምራት ነገራ እና መዓዛ መሐመድ ናቸው። 

“ኡቡንቱ” የተሰኘው የዩቱዩብ ሚዲያ ባልደረባ የሆነው እያስፔድ ተስፋዬ ከወላጆቹ ቤት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው የዛሬ ሳምንት ማክሰኞ ህዳር 28 ነበር። እያስፔድ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ጽህፈት ቤት በሚገኝበት እና በተለምዶ ሶስተኛ ተብሎ በሚጠራው ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ እንደሚገኝ የቅርብ ወዳጆቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።   

ባለፈው አርብ ታህሳስ 1 ከመኖሪያ ቤቱ በፖሊስ የታየዘው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራም፤ መጀመሪያ የተወሰደው ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደነበር ለቤተሰቦቹ ተነግሯቸው ነበር። ሆኖም ጋዜጠኛው ከተያዘበት ቀን ጀምሮ እስከዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 5 ድረስ በየፖሊስ ጣቢያው ሲያፈላልጉት የቆዩት ቤተሰቦቹ፤ የት እንደታሰረ እንደማያውቁ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

ጋዜጠኛ ታምራት “ተራራ ኔትወርክ” የተባለው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ባለቤት እና ዋና አዘጋጅ ነው። ከባልደረቦቿ ጋር በመሆን “ሮሃ ቲቪ” የተሰኘ የዩቲዩብ ሚዲያ በቅርቡ ያቋቋመችው መዓዛ መሐመድ በሰሞኑ የጋዜጠኞች እስር ሰለባ ከሆኑት አንዷ ናት። ከሁለት ቀናት በፊት ቅዳሜ ታህሳስ 2 በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው መዓዛን፤ የዓይን እማኞች በሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ግቢ ውስጥ እንዳለች ተመልክተዋታል።

ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች የሆነው ሲፒጄ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ህዳር 30 ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ በኋላ ስድስት ጋዜጠኞች መታሰራቸውን አስታውቆ ነበር። በሪፖርቱ መሰረት እስከ ህዳር 22፤ 2014 ድረስ ብቻ በኢትዮጵያ ዘጠኝ ጋዜጠኞች በእስር ላይ የነበሩ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያን ጋዜጠኞችን በማሰር ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት በሁለተኝነት ደረጃ አስቀምጧታል። 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበር በዛሬ መግለጫው የዳሰሰው ሌላው ጉዳይ፤ ሀገር አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ባለድርሻዎች ውይይትን የተመለከተው ነው። ማህበሩ የዘርፉ ባለሙያዎች የውይይት ጉባኤ እንዲጀመር የጠየቀው፤ የጋዜጠኝነት ስነ ምግባርን ለማሳደግ እና ሙያተኞች የሚጠበቅባቸውን ሙያ በመርሁ መሰረት ለመተግበር ያበቃል በሚል እምነት እንደሆነ ገልጿል። 

የውይይት ጉባኤው ሁሉም የመገናኛ ብዙሃን ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የሚያደርጉበት እና በሁለንተናዊ የጋዜጠኝነት ትግበራ ጥንካሬዎች፣ ድክመቶችና መፍትሔዎቹ ላይ የሚያተኩር መሆን እንዳለበት ማህበሩ በመግለጫው አሳስቧል። ለዚህ መነሻ እንዲሆንም ወቅታዊ ሁኔታን ያገናዘበ “የቀውስ ወቅት የሚዲያ አዘጋገብ” ላይ የምክክር መድረክ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ቢደረግ “ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ” አጽንኦት ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)