የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ከመጽደቁ በፊት ሃሳብ እንዲሰጥበት ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ጠየቀ

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን የማቋቋሚያ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመጽደቁ በፊት “ባለድርሻ አካላት ሀሳባቸውን እንዲሰጡበት” ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ጠየቀ። “የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የሚዲያ ተቋማት እና ህዝቡ” የአዋጅ ረቂቁን ተመልክተው ሀሳባቸውን እንዲሰጡ ቢደረግ “ሂደቱ ገና ከጅምሩ አሳታፊ እንዲሆን እድል” እንደሚፈጥር ፓርቲው ያለውን እምነት ገልጿል።

ፓርቲው ትላንት ማክሰኞ ታህሳስ 5 ባወጣው መግለጫ፤ የኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅ በባለድርሻ አካላት ሀሳብ ከተሰጠበት የሚመሰረተውን “ኮሚሽን ቅቡልነት ለማሳደግ እና ሰፊ የህዝብ ይሁንታ እንዲያገኝ ይረዳል” ብሏል። በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት እንዲካሔድ ባለፉት ሁለት አመታት “ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ እና መንግስትም ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጥሪ ሲያቀርብ” መቆየቱን ያስታወሰው ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ “መንግስት ኃላፊነቱን ወስዶ ይህንን ስራ የሚያስተባብር ተቋም ለማቋቋም መወሰኑ አበረታች” ብሎታል። 

በኢትዮጵያ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ለማካሄድ የታቀደውን “አካታች አገራዊ ምክክር” በገለልተኝነት የመምራት እና የማስተባበር ኃላፊነት የተጣለበትን ኮሚሽን የሚያቋቁመው የአዋጅ ረቂቅ፤ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ባለፈው ሳምንት ታህሳስ 1፤ 2014 ነበር። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ካካሄደው ውይይት በኋላ ተጨማሪ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ተቋም እንዲቋቋም የተፈለገው “መሰረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ልሂቃንም ሆኑ ምልዓተ ህዝቡ ተቀራራቢ እና በአገራዊ አንድነት ገንቢ አቋም እንዲይዙ ለማድረግ” በማሰብ እንደሆነ ጽህፈት ቤቱ ጨምሮ ገልጿል። የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ በትላንት መግለጫው፤ አገራዊ ምክክርን አስመልክቶ መንግስት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊያደርጉባቸው ይገባል ያላቸውን ጉዳዮች ዘርዝሮ አቅርቧል።

አገራዊ ምክክሩ፤ ከዝግጅት እስከ አተገባበር “ከፍተኛ ጥንቃቄ፣ ግልጽነት እና ቁርጠኝነትን” ይጠይቃል ያለው ነእፓ፤ ለዚህም የመንግስት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጿል። ይሁንና “ሂደቱ ከመንግስት ጫና እና የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ” መሆኑን ለማረጋገጥ “ተሳታፊዎች እና አወያዮች በመምረጥ እና አጀንዳዎችን በመቅረጽ ሂደት ተቋሙ በነጻነት መስራት ይችል ዘንድ፤ ግልጽ የህግ ማዕቀፍ እና ከለላ ሊኖረው” እንደሚገባ ፓርቲው ጥቆማ አቅርቧል።

“የምክክር ሂደቱን ቅቡልነት ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ፣ በተሳታፊዎች መካከል መተማመንን ሊፈጥሩ የሚችሉ ህጋዊ እና ፖለቲካዊ መደላድሎችን መፍጠር [ላይ] ትኩረት” መስጠት እንደሚገባም ፓርቲው አሳስቧል። ምቹ ከባቢ ከሌለ አገራዊ ምክክር ማካሄድ ከባድ መሆኑን በመግለጫው የጠቀሰው ፓርቲው፤ ከዚህም ባሻገር “የሚጠበቀው ውጤት እንዳይገኝ እንቅፋት” ሊሆን እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል። 

አገራዊ የምክክር ሂደቱን ማካሄድ “ከፍተኛ እውቀት እና ልምድ፣ ሰፊ የንድፈ ሀሳብ እና የተግባር ተሞክሮ” ይጠይቃል ያለው ፓርቲው፤ ይህን ለማከናወን የሚደረገው የሥራ ኃላፊዎች እና የባለሙያዎች ምደባ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚሻ አመልክቷል። “በተለይም ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ ኮሚሽነሮች ገለልተኛ፣ ሙያዊ ብቃት እንዲሁም የህዝብ አመኔታ እና ተቀባይነት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል” ሲል ፓርቲው በባለሙያዎች ምደባ ላይ ያለውን አቋሙን አሳውቋል። የኮሚሽኑ የስራ ኃላፊዎች አሰያየም ከሙያዊ ብቃት ባሻገር የሀገሪቱን ህዝቦች ብዝሃነት ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ “የብሄር፣ የእምነት እና የጾታ ስብጥርን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን” እንደሚገባም አሳስቧል። 

ነእፓ በትላንት መግለጫው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ሶስት አመታት ያቋቋማቸው ሁለት ኮሚሽኖች “ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎባቸው” እንደነበር አስታውሷል። የእርቀ ሰላም ኮሚሽን እንዲሁም የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የተባሉት እነኚህ ሁለት ተቋማት “ከፍተኛ የሀገር ሀብትም ቢፈስባቸውም”፤ እንቅስቃሴዎቻቸው “ከተጠበቀው አንጻር ሲታይ ለብዙዎች አጥጋቢ አልነበረም” ሲል ተችቷል። አዲስ የሚቋቋመው ኮሚሽን “የተጣለበትን ከፍተኛ ታሪካዊ ኃላፊነት በአግባቡ ይወጣ ዘንድ ተገቢ ትኩረት እና ድጋፍ” እንደሚያስፈልገው ፓርቲው አጽንኦት ሰጥቷል።

በኢትዮጵያ ያሉ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት “ብሔራዊ ውይይት” እንዲካሄድ በተለያዩ ወገኖች ተደጋጋሚ ጥሪ ሲቀርብ ቆይቷል። ከአንድ ዓመት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በተለይ “የብሔራዊ ውይይት” ጥሪው ጎልቶ መደመጥ ቀጥሏል። በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ውጤት መሰረት ባለፈው መስከረም መንግስት የመሰረተው ገዢው የብልጽግና ፓርቲም ይህንኑ የውይይት ጉዳይ ትኩረት እንደሚሰጠው በተደጋጋሚ ሲገልጽ ሰንብቷል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው መስከረም 24 በተከናወነው በዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የፖለቲካ ልዩነቶችን ለማጥበብ “አካታች ብሔራዊ የውይይት መድረክ” እንደሚካሄድ ቃል ገብተው ነበር። ውይይቱ “ችግሮቻችን በጠረጴዛ ዙሪያ ይፈታሉ ብለው የሚያምኑትን የሚያካትት” እንደሚሆን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አጠቃላይ ሂደቱ “የሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎችን ተሳትፎ ያገናዘበ፤ አካታች እና አሳታፊ” እንደሚሆን በወቅቱ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)