በሃሚድ አወል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ለሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አባልነት የሚሾሙ ስድስት የህግ ባለሙያዎችን ዕጩነት በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ። የህግ ባለሙያዎቹ በፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ አማካኝነት እንዲሾሙ ምክር ቤቱ የወሰነው፤ ዛሬ ሐሙስ ታህሳስ 7፤ 2014 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ነው።
ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ስልጣን ያለው ጉባኤ ካሉት 11 አባላት ውስጥ ስድስቱ የህግ ባለሙያዎች እንዲሆኑ የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ይደነግጋል። የህግ ባለሙያዎቹ “በሙያ ብቃታቸው እና ስነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው” መሆን እንዳለባቸው በሕገ መንግስቱ ተቀምጧል። የህግ ባለሙያዎቹን ለሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አቅርቦ የማስሾም ስልጣን በሕገ መንግስቱ የተሰጠው ለተወካዮች ምክር ቤት ነው።
በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ለጉባኤው አባልነት በዕጩነት መመረጣቸው ይፋ ከተደረጉ ስድስት የህግ ባለሙያዎች ውስጥ አምስቱ ለቦታው አዲስ ናቸው። ባለፈው ሐምሌ 2013 ዓ.ም. የስራ ዘመኑን ያጠናቀቀው የነባሩ ጉባኤ አባል የነበሩት ደስታ ገብሩ፤ በድጋሚ ለኃላፊነት ቦታው ታጭተዋል። የ61 ዓመቷ ደስታ በዕጩነት ከቀረቡት ውስጥ ብቸኛዋ ሴትም ናቸው።
በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ደስታ፤ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለአስራ ስድስት ዓመታት በዳኝነት አገልግለዋል። የህግ ባለሙያዋ በነባሩ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አባል ሆነው የተሾሙት በ2007 ዓ.ም ነበር።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አባል ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ በሻዳ ገመቹ ጉባኤውን ለመጀመሪያ ጊዜ ከተቀላቀሉት አንዱ ሆነዋል። የ68 ዓመቱ አቶ በሻዳ፤ በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፕሬዝዳንትነት እና በምክትል ፕሬዝዳንትነት ለሁለት ዓመታት አገልግለዋል። አዲሱ የጉባኤው አባል በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በአሁኑ ወቅት በጥብቅና እና በህግ ማማከር ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።
“ሀበጋር” የተሰኘው የክርክር መድረክ መስራች የሆኑት አቶ ደበበ ኃይለገብርኤል፤ ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት የጉባኤው አባል እንዲሆኑ ከታጩ የህግ ባለሙያዎች አንዱ ናቸው። ከደቡብ አፍሪካው ፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ በህግ ሁለተኛ ዲግሪቸውን ያገኙት አቶ ደበበ፤ ለስምንት ዓመታት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት አገልግለዋል።
በሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ዕጩዎች ዝርዝር የተካቱት ሌላው የህግ ባለሙያ አቶ ቸርነት ዎርዶፋ ናቸው። በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ለአምስት አመታት ያገለገሉት አቶ ቸርነት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ አስተምረዋል። በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በመማር ላይ ናቸው።
አምስተኛው የጉባኤው እጩ አባል አቶ ምትኩ ማዳ፤ ለሶስት አስርት አመታት ያህል በዩኒቨርሲቲ ህግ አስተምረዋል። የ49 ዓመቱ አቶ ምትኩ፤ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በፌደራል የፍትህ እና ህግ ኢንስቲትዩት የጥናት እና ምርምር ምክትል ዳይሬክተር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
አቶ አብደልአዚዝ አህመድ ሌላኛው ለጉባኤው አባልነት በፕሬዝዳንቷ እንዲሾሙ የቀረቡ ዕጩ ናቸው። ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ህግ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያዙት አቶ አብደልአዚዝ በሶማሌ ክልል በዳኝነት አገልግለዋል። የክልሉ ዐቃቤ ህግ እና ፍትህ ቢሮ ኃላፊም ሆነው ለሶስት ዓመታት ሰርተዋል።
ለሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በዕጩ አባልነት በቀረቡ በእነዚህ የህግ ባለሙያዎች ላይ ሁለት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዛሬው ስብሰባ ጠንከር ያለ ተቃውሟቸውን አቅርበዋል። ቅድስት አርአያ የተባሉ የምክር ቤት አባላት “አብዛኛዎቹ ዕጩዎች ከአንድ አካባቢ የተውጣጡ ናቸው” ሲሉ የአባላቱ ምርጫ ላይ ጥያቄ አንስተዋል። አንድ ሌላ የምክር ቤት አባልም የዕጩዎቹ ምርጫ “ብዝሃነት ይጎድለዋል” ሲሉ ተችተዋል። ከሴቶች ተሳትፎ ጋር በተያያዘም ከአንዲት የምክር ቤት አባል ጥያቄ ተነስቷል።
የምክር ቤቱ አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ዕጩዎች ለሹመት እንዲቀርቡ ሲታጩ “ስብጥር እንዲኖር ጥረት ተደርጓል” ሲሉ ለምክር ቤት አባላቱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። እርሳቸው ይህን ቢሉም፤ የህግ ባለሙያዎቹ ዕጩነት ከተቃውሞ አላመለጠም። የጉባኤው ዕጩ አባላት በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አማካኝነት እንዲሾሙ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አራት የፓርላማ አባላት የተቃወሙት ሲሆን አስራ ሁለቱ ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል።
በፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ አማካኝነት ይሾማሉ ተብለው የሚጠበቁት ስድስቱ የህግ ባለሙያዎች፤ የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ አባል ሆነው የሚቆዩት ለስድስት ዓመት ነው። የነባሩ ጉባኤ አባል የሆኑት የህግ ባለሙያዎች የተሾሙት ከስድስት ዓመት ከመንፈቅ በፊት ሰኔ 2007 ዓ.ም. ነበር።
ከጉባኤው አባላት መካከል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የህግ አማካሪ የነበሩት ዶ/ር ፋሲል ናሆም ይገኙበታል። የቀድሞው የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሐሺም ቶፊቅም የአጣሪ ጉባኤው አባል ሆነው በ2007 ዓ.ም ተሹመው ነበር።
ዶ/ር ሐሺም ቶፊቅ ከሶስት ዓመት በፊት ከአጣሪ ጉባኤው አባልነት መልቀቃቸውን የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዬሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እንደ አቶ ደሳለኝ ገለጻ ዶ/ር ሐሺም ከኃላፊነት የለቀቁት “ከለውጡ በኋላ” ነው። ዶ/ር ሐሺም በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ህዳር 2011 ላይ በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር።
ላለፉት ስድስት ዓመታት የጉባኤው አባል ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩት የህግ ባለሙያዎች ውስጥ በአንድ ወቅት የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ጠበቃ ሆነው ያገለገሉት አቶ ሚሊዩን አሰፋ ይገኙበታል። የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚንስትር የነበሩት ኡባህ መሐመድም የጉባኤው አባል ነበሩ።
ሌላኛው የጉባኤው አባል የነበሩት አቶ ክፍለጽዮን ማሞ ከአንድ ዓመት በፊት ህዳር 2013 ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የሆኑት አቶ ክፍለጽዮን፤ አሁን በስራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት ከማርቀቁ እስከ ማጽደቁ ባለው የሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙያዊ ድጋፍ ስለመስጠታቸው ይነገርላቸዋል።
የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ 11 አባላት ውስጥ ሶስቱ ከፌደሬሽን ምክር ቤት የሚወከሉ መሆናቸው በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ተደንጓል። ጉባኤውን በሰብሳቢ እና ምክትል ሰብሳቢነት የሚመሩት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት እንደሆኑ በሕገ መንግስቱ ተቀምጧል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ወክለው ጉባኤውን የሚቀላቀሉ አባላቸው የሚኖራቸው የጊዜ ቆይታ፤ ከፌደሬሽን ምክር ቤት የስራ ዘመን ጋር ተመሳሳይ መሆኑን የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አዋጅ ላይ ሰፍሯል። በነባሩ ጉባኤ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የወከሉ ሶስት አባላት ዶ/ር ቀነዓ ያደታ፣ አቶ መለሰ አለሙ እና አቶ ብርሃን ኃይሉ ናቸው።
የአዲስ አበባ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ መለሰ፤ ባለፈው መስከረም ወር የምስረታ ጉባኤውን ባካሄደው የአዲስ አበባ ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል። ዶ/ር ቀነዓ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ። አቶ ብርሃን ከ2001 እስከ 2005 ዓ.ም. ለአራት አመታት የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)