ተመድ በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የመብት ጥሰቶችን የሚመረምር የባለሙያዎች ኮሚሽን አቋቋመ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚመረምር ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ኮሚሽን አቋቋመ። ኮሚሽኑን የሚያቋቋመውን የውሳኔ ሃሳብ ከአርባ ሰባቱ የምክር ቤቱ አባል ሀገራት ሃያ አንዱ ሲደግፉት፤ አስራ አምስቱ ተቃውመውታል። 

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፤ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ኮሚሽን እንዲቋቋም ድምጽ የሰጠው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በጠራው እና ዛሬ አርብ ታህሳስ 8 በጄኔቫ በተካሄደው ልዩ ስብሰባ ላይ ነው። አፍሪካን ወክለው የምክር ቤቱ አባል ከሆኑ አገሮች መካከል አንዳቸውም ኮሚሽኑ እንዲቋቋም የሚጠይቀውን የውሳኔ ሃሳብ ደግፈው ድምጽ አልሰጡም።

የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆኑት ኤርትራ እና ሶማሊያን ጨምሮ ቡርኪና ፋሶ፣ ካሜሩን፣ ኮትዲቯር፣ ጋቦን እና ናሚቢያ የውሳኔ ሃሳቡን ተቃውመዋል። ቻይና፣ ሩሲያ እና ህንድም የኮሚሽኑን ማቋቋም ጨምሮ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እና በደሎችን የሚያወግዘውን የውሳኔ ሃሳብ ከተቃወሙት መካከል  ይገኙበታል።

ሌላዋ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሱዳን ድምጽ ከመስጠት የታቀበች ሲሆን ቶጎ፣ ማላዊ፣ ሊቢያ፣ ሞሪታኒያ እና ሴኔጋልም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል። ጽምጽ ከመስጠት የታቀቡ የምክር ቤቱ አባል ሀገራት ብዛት 11 ነው። 

በዛሬው የውሳኔ ሃሳብ መሰረት የሚቋቋመው መርማሪ ኮሚሽን፤ በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የሚሾሙ ሶስት ባለሙያዎችን የሚያካትት ነው። የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽኑ ያሰራጨው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ እንደሚለው፤ መርማሪ ኮሚሽኑ የአንድ ዓመት የስራ ዘመን የሚኖረው ሲሆን የጊዜ ቆይታው እንዳስፈላጊነቱ ሊራዘም ይችላል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጸሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና በደሎችን የሚመረምረው ዓለም አቀፍ ኮሚሽን አምስት ኃላፊነቶች ተሰጥተውታል። ኮሚሽኑ በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ወገኖች ተፈጽመዋል የሚባሉ የዓለም አቀፍ ሕጋግት ጥሰቶችን የመመርመር ኃላፊነት ተጥሎበታል።

ኮሚሽኑ ተፈጽመዋል በሚባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና በደሎች ላይ በሚያደርገው ምርመራ የደረሰባቸውን ሃቆች እና ሁኔታዊ ማስረጃዎች የመሰነድ ሚና አለው። የሰነዳቸውን ማስረጃዎች አጥፊዎችን በመለየት ተጠያቂ ለማድረግ በሚካሄድ ላይ ላሉ እና ወደፊትም ሊደረጉ ለሚችሉ ጥረቶች ግብዓት እንዲሆኑ እንደሚያደርግም ተገልጿል። ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ይካተቱበታል የተባለው ኮሚሽኑ፤ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እና ዕርቅ ማውረድን ጨምሮ እንደ አስፈላጊነቱ ስለ ሽግግር ፍትህ ለኢትዮጵያ መንግስት ቴክኒካዊ ድጋፍ እንደሚሰጥ የውሳኔ ሃሳቡ ያትታል። 

የኢትዮጵያ መንግስት ምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳቡን ካስተላለፈ በኋላ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በይፋ ያለው ነገር የለም። ሆኖም በሀገሪቱ ላይ ያተኮረውን የልዩ ስብሰባ መካሄድ ግን ከጅምሩ አንስቶ አጥብቆ ተቃውሟል። የምክር ቤቱ አባል ሀገራትም የተዘጋጀውን የሰነድ ረቂቅ በመቃወም ድምጽ እንዲሰጡ ሲያሳስብ ቆይቷል።    

መቀመጫቸውን በስዊዘርላንድ ጄነቫ ባደረጉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ቋሚ የኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑት አምባሳደር ዘነበ ከበደ በዛሬው ስብሰባ ላይ ባሰሙት ንግግር፤ ምክር ቤቱ “የፖለቲካ ግፊት መጠቀሚያ መሳሪያ” ሆኗል ሲሉ ወንጅለዋል። ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር “የማያወላውል ቁርጠኝነት” እንዳላት የጠቀሱት አምባሳደሩ፤ ሆኖም ሀገራቸው በምክር ቤቱ በኩል የሚደረግን “ፖለቲካዊ ዓላማ ያነገበ ጣልቃ ገብነት” እንደማትቀበል አስታውቀዋል።

“መንግስታችን [በምክር ቤቱ] ከሚጫንበት ማንኛውም አይነት አሰራር ጋር አይተባበርም። ምክንያቱም ይህ ሆን ተብሎ ያለመረጋጋትን ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ነው” ብለዋል።  

አምባሳደር ዘነበ ምክር ቤቱ በአማጽያኑ የህወሓት ኃይሎች የተፈጸሙ “የንብረት ውድመት፣ አስገድዶ መድፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ ህጻናትን በወታደርነት የማሰማራት” የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችን አለማውገዙን ተችተዋል። አማጽያኑ የምግብ አቅርቦት የተከማቹባቸው መጋዘኖችን፣ የጤና ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማውደማቸውን የገለጹት አምባሳደሩ፤ “ይህንን ልዩ ስብሰባ የጠሩት ግን ለዚህ ግድ የላቸውም” ሲሉ ነቅፈዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)