የአማራ ክልል፤ በህወሓት ኃይሎች ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች የደረሱ ጉዳቶችን የሚያጠና ቡድን አቋቋመ

በሃሚድ አወል

የአማራ ክልል በህወሓት ኃይሎች ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች የደረሱ ጉዳቶችን የሚያጠና ቡድን ባለፈው ሳምንት ማቋቋሙን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ አስታወቀ። ጥናቱ የሚከናወነው የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መልሰው በተቆጣጠሯቸው የክልሉ አምስት ዞኖች እና ሁለት ከተሞች ነው ተብሏል።  

የአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንሙት በለጠ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የሚደረገው ጥናት በሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። የመጀመሪያው በአካባቢዎቹ በንብረት ላይ የተፈጸሙ ውድመቶች ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ በነዋሪዎች ስነ ልቦና ላይ የደረሰው ጉዳት መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ቢሮ የሚያስተባበረው የጥናት ቡድን የተዋቀረው፤ በአማራ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከክልሉ የሴክተር መስሪያ ቤቶች መሆኑን አቶ አንሙት ኃላፊው አስረድተዋል። የፌደራሉ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲም በዚህ ጥናት ላይ ተሳትፎ እንደሚኖረው አክለዋል።

በጥናት ቡድኑ ውስጥ የክልሉ ግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ፍትህ እና የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮን ጨምሮ 16 የሴክተር መስሪያ ቤቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ አቶ አንሙት ተናግረዋል። የክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች 113 ባለሙያዎችን ለጥናት ቡድኑ መላካቸውንም ጨምረው ገልጸዋል። 

ቡድኑ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን እና በደቡብ ወሎ ዞን የደረሱ ጉዳቶችን ጥናት በተናጠል የሚያካሄድ ሲሆን፤ የዋግ ህምራ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖችን ግን በጋራ ያከናውናል ተብሏል። በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙት የደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች የደረሰው ጉዳት፤ “ከከተሞቹ ትልቅነት አንጻር” ተለይቶ እንደሚጠና አቶ አንሙት አብራርተዋል። 

በእነዚህ አካባቢዎች የሚደረገውን ጥናት በአማራ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ባለሙያዎችም እንደሚሳተፉበትም የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ጠቁመዋል። በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ በሚደረገው ጥናት ላይ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች እንደሚሳተፉ ከቢሮው የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

በደቡብ ጎንደር የደረሰውን ጉዳት በሚያጠናው ቡድን ውስጥ የባህርዳር እና ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ተካትተዋል። የደባርቅ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች በበኩላቸው በዋግ ኽምራ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች በሚደረገው ጥናት ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ። በደቡብ ወሎ እንዲሁም ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች በሚደረገው ጥናት ላይ ደግሞ የወሎ ዩኒቨርስቲ ባለሙያዎች የጥናት ቡድኑ አባላት ናቸው።     

በህወሓት ኃይሎች “ወረራ” ምክንያት በአማራ ክልል ከጥቅምት ወር አጋማሽ በፊት የደረሰው ጉዳት 279.5 ቢሊዮን ብር እንደሚገመት የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህ ጉዳት የህወሓት ኃይሎች በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎችን እንዲሁም የኦሮሞ ብሔረሰብ እና የሰሜን ሸዋ ዞኖችን ከመያዛቸው በፊት የተመዘገበ መሆኑንም ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)