የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለልተኝነት ጥያቄ አስነሳ

በሃሚድ አወል

አገራዊ ምክክሮችን ለማመቻቸት ይቋቋማል የተባለው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለልተኝነት ላይ ጥያቄዎች ተነሱበት። ጥያቄዎቹ የተነሱት በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ፤ የተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ትላንት ሰኞ ታህሳስ 11፤ 2014 ባካሄደው የሕዝብ ውይይት መድረክ ላይ ነው። 

የኮሚሽኑ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ያነሱት በወይይት መድረኩ ላይ የተገኙ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት እና የዲሞክራሲ ተቋማት ተወካዮች ናቸው። ለጥያቄዎቹ መነሳት ምክንያት የሆነው ዋነኛ ጉዳይ፤ ኮሚሽኑ ሲቋቋም በተቋሙ ላይ መንግስት የሚኖረው ሚና ነው።

የኮሚሽኑን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ከከተቱት ጉዳዮች መካከል አንደኛው የኮሚሽነሮች አሰያየም ነው። በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ መሰረት ኮሚሽነር ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን ጥቆማ የሚቀበለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ነው። 

ጽህፈት ቤቱ ጥቆማዎችን ከህዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶች እና ከሲቪል ማህበራት ከተቀበለ በኋላ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀርባል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በቀረቡ ዕጩዎች ላይ እንደገና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ከሲቪል ማህበራት እና ከኃይማኖት ተቋማት አመራሮች ጋር ምክክር ያደርጋሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ጽህፈት ቤታቸው በኮሚሽነሮች አሰያየም ላይ ያላቸው ሚና ገለልተኝነቱን ጥያቄ ውስጥ ይከትተዋል የሚል ስጋት ከውይይቱ ተሳታፊዎች ተነስቷል፡፡

በኮሚሽኑ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ካነሱ የውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶ/ር ራሄል ባፌ አንዷ ናቸው። “የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትንም፤ ብልጽግና ፓርቲንም ለመለየት ያስቸግራል” የሚሉት የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢዋ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በኮሚሽነሮች አሰያየም ላይ ይሳተፋል መባሉን ተቃውመዋል።  

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ቀደም ብሎም የኮሚሽነሮች አሰያይም የገለልተኝነት ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል የሚል ግምት እንደነበር ጠቁመዋል | ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፤ ቀደም ብሎም የኮሚሽነሮች አሰያይም የገለልተኝነት ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል የሚል ግምት እንደነበር ጠቁመዋል። በዚህም ምክንያት ለኮሚሽነርነት በዕጩ የሚቀርቡ ግለሰቦችን ጥቆማን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት እንዲቀበል በአማራጭነት መቅረቡን ለውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል። 

ዶ/ር ጌዲዮን በኮሚሽኑ ላይ የሚነሱ የገለልተኝነት ጥያቄዎችን ለማስቀረት ያስችላል ያሉት አማራጭ የውይይቱን ተሳታፊዎች አላሳመነም። ሚኒስትሩ ያቀረቡት አማራጭ “ገለልተኛ የአፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ቢኖረን ያስማማናል” የሚል እንደሆነ የጠቀሱት ዶ/ር ራሄል “እኛ ለእዛ አልታደልንም። ሁሉም ከአንድ [ፓርቲ] ስለሆነ” ሲሉ የአፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ገለልተኝነትም ላይ ተጨማሪ ጥያቄ አንስተዋል።

ሌሎች የውይይቱ ተሳታፊዎች የኮሚሽኑን ገለልተኝነት ለማረጋገጥ ያስችላል ያሉትን የየራሳቸውን አማራጭ አቅርበዋል። በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ሕጻናት መብቶች ኮሚሽነር የሆኑት መስከረም ገስጥ አማራጭ ካቀረቡ ተወያዮች መካከል አንዷ ናቸው። መስከረም አዲስ ለሚቋቋመው ኮሚሽን “ዕጩዎችን የሚቀበለው ገለልተኛ ተቋም ቢሆን” የሚል ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል። 

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ሕጻናት መብቶች ኮሚሽነር የሆኑት መስከረም ገስጥ አማራጭ ካቀረቡ ተወያዮች መካከል አንዷ ናቸው | ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

አራት ሰዓታትን በፈጀው የትላንቱ ውይይት፤ ኮሚሽነር ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ጥቆማ “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀበል” የሚል ምክረ ሃሳብ ከበርካታ አስተያየት ሰጪዎች ተሰምቷል። የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን 11 ኮሚሽነሮች እንደሚኖሩት በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ተቀምጧል። 

ኮሚሽነሮቹ የሚመረጡት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከሕዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶች እና ከሲቪል ማህበራት ጥቆማ ከሚቀበላቸው ዕጩዎች መካከል እንደሆነ በአዋጅ ረቂቁ ተገልጿል። የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን፤ ምክር ቤቱ የዕጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ ይቀበል የሚለው አስተያየት በአማራጭነት ሊቀርብ ይችላል ሲሉ ለውይይት ተሳታፊዎቹ ምላሽ ሰጥተዋል።  

“ሁሉን አቀፍ እና አካታች ምክክር ያካሂዳል” የተባለለትን ኮሚሽን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባው ሌላው ጉዳይ፤ የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ደንቦችን የማውጣት ስልጣን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መሰጠቱ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ “ደንብ እና መመሪያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊወጣ ይችላል መባሉ [የኮሚሽኑ] ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ይፈጥራል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ “ደንብ እና መመሪያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊወጣ ይችላል መባሉ [የኮሚሽኑ] ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ይፈጥራል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል | ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ይህን ስጋት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶ/ር ራሄልም ተጋርተውታል። አዋጁን በበቂ ሁኔታ የሚያስረዳው ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይወጣል መባሉ፤ በኮሚሽኑ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ እንደሚያስነሳ ዶ/ር ራሄል ተናግረዋል። የፍትህ ሚኒስትሩ ለእነዚህ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፤ ደንብ የማውጣት ስልጣን ወደ ተወካዮች ምክር ቤቱ ሊተላለፍ እንደሚችል ጠቁመዋል። ዶ/ር ጌዲዮን “ደንቦችን ማውጣት ያለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። [ረቂቅ አዋጁ ላይ] ማሻሻያ ይደረግበታል” ብለዋል።  

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ በኋላ የሚያደርጋቸውን የምክክሮች ሂደት፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን እና የምክረ ሃሳቦቹን አተገባበር የሚገልጽ ሪፖርት ለመንግስት ያቀርባል መባሉም ሌላው የገለልተኝነት ጥያቄ ያስነሳ ጉዳይ ሆኗል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች የተወሰኑት “ለመንግስት ሪፖርት መቅረቡ አግባብ አይደለም” ሲሉ ተደምጠዋል። “ሪፖርቱ ለመንግስት ለምን ማቅረብ አስፈለገ?” የሚል ጥያቄ ያነሱ ተወያዮችም ነበሩ። 

ተሳታፊዎቹ ጥያቄውን እንዲያነሱ ያደረጋቸው፤ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ራሱ በምክከሩ ከሚሳተፉ ባለድርሻዎች አንዱ መሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ፤ “ምክክሩ ወደ መንግስት እና ገዢው ፓርቲ የሚሰበሰብበት ነገር ቢቀር” ሲሉ መንግስት በምክከሩ ላይ የሚኖረው ሚና እንዲጤን ጠይቀዋል። አቶ የሺዋስ “እያንዳንዷ [የኮሚሽኑ] እርምጃ ላይ ገለልተኝነቱን ማረጋገጥ መልካም ይመስለኛል” ሲሉ የኮሚሽኑ ገለልተኝነት አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል።

የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ “ምክክሩ ወደ መንግስት እና ገዢው ፓርቲ የሚሰበሰብበት ነገር ቢቀር” ሲሉ መንግስት በምክከሩ ላይ የሚኖረው ሚና እንዲጤን ጠይቀዋል | ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የምክክር ኮሚሽኑ ለመንግስት ሪፖርት እንዲያቀርብ በአዋጅ ረቂቁ ላይ የተደነገገበትን ምክንያት የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን አብራርተዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ለመንግስት የሚያቀርበው “ምክረ ሃሳቦቹን የማስፈጸም የፖለቲካ እና የሞራል ኃላፊነት በመንግስት ላይ ስለሚወድቅ ነው”። ዶ/ር ጌዲዮን ኮሚሽኑ የሚያቀርበው ሪፖርት “ከመደበኛ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በተለየ መታየት አለበት” ሲሉም ተደምጠዋል።  

በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ የአዋጅ ረቂቅ መሰረት፤ ኮሚሽኑ ለመንግስት የሚያቀርበው ሪፖርት የሚያካትተው የምክከሮቹን ሂደት፤ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሃሳቦች እና የምክረ ሃሳቦቹን የአተገባበር ስልት ነው። ኮሚሽኑ ለመንግስት ከሚያቀርበው ሪፖርት በተጨማሪ ሂደቱን እና ምክረ ሃሳቦቹን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ በአዋጅ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል። 

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ “የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ያገለለ ነው” የሚል ትችትም ከውይይቱ ተሳታፊዎች ቀርቧል። ለትችቱ መነሻ የሆነው የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአገራዊ ምክክሩ የሚኖራቸው ሚና በረቂቅ አዋጁ ላይ በግልጽ አለመቀመጡ ነው።

በምክክሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚኖራቸውን ተሳትፎ በተመለከተ በግልጽ ማመላከቱ አስፈላጊ መሆኑን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በአጽንኦት ተናግረዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ በግልጽ ከማመላከት ባለፈ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ምክክሩ “ከፍ ያለ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል” የሚል ምክረ ሃሳብም አቅርበዋል። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋር ምክር ቤት ሰብሳቢዋ ዶ/ር ራሄል በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያላካተተ እና ያልዳሰሰ መሆኑን በመግለጽ፤ አገራዊ ምክክሩ “ገና ከጅምሩ inclusive (አካታች) አለመሆኑን አይተናል” ሲሉ ተችተዋል። ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ላይ የሚኖራቸው ሚና በግልጽ አልሰፈረም የሚል አስተያየት ከውይይቱ ተሳታፊዎች ተነስቷል።

በአዋጅ ረቂቁ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሁለት ሚናዎች እንዳሏቸው ተጠቅሷል። ሁለቱም ሚናዎቻቸው ከኮሚሽኑ ኮሚሽሮች አሰያየም ጋር የተያያዙ ናቸው። የመጀመሪያው ሚናቸው ለኮሚሽነርነት የሚታጩ ግለሰቦችን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መጠቆም ነው። በቀረቡት ዕጩዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያደርጉት ምክክር መሳተፍ፤ ሌላኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ነው። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ሚና በተመለከተ ለተነሳው አስተያየት የፍትህ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፤ “ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ምን መልክ ይኖረዋል የሚለው በግልጽ ባልተመላከተበት ሁኔታ በዝርዝር ሚናቸውን መግለጽ ያስቸግራል” ብለዋል። 

በተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዕጸገነት መንግስቱ መሪነት በተካሄደው በትላንቱ የህዝብ ውይይት መድረክ ላይ፤ አብዛኛውን ጊዜ ወስዶ ያወያየው የኮሚሽኑ ገለልተኝነት ቢሆንም ሌሎች ጉዳዮችም ተነስተዋል። የኮሚሽነሮቹ አሰያየም፣ አካታችነት እና ብዝሃነት  እንዲሁም የምክከር አጀንዳዎች እና አወያዮች አመራረጥ ሂደት ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች ውስጥ ይገኙበታል።  

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ታህሳስ 7፤ 2014 ነበር።  በዕለቱ የምክር ቤት አባላት በቀረበው የአዋጅ ረቂቅ ላይ ቢካተቱ ያሏቸውን ጉዳዮች ያነሱ ሲሆን፤ ለዝርዝር እይታ ወደ ህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርተውታል።  አምስት ክፍሎች እና 30 አንቀጾች ያሉት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተወሰነው በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)