በሃሚድ አወል
የመከላከያ ሰራዊት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ከህወሓት ኃይሎች ነጻ ባወጣቸው አካባቢዎች ጸንቶ እንዲቆይ ትዕዛዝ ማስተላለፉን የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ። በህወሓት ኃይሎች የተያዙ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የሚገኙ አካባቢዎችን ለማስለቀቅ የተካሔደው “ዘመቻ ህብረ ብሔራዊ አንድነት” መጠናቀቁም ዛሬ ይፋ ተደርጓል።
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ዛሬ ሐሙስ ታህሳስ 14 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የመከላከያ ሰራዊት ከህወሓት ባስለቀቃቸው አካባቢዎች እንዲቆይ የተወሰነባቸውን ሶስት ምክንያቶች አብራርተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ከትግራይ ክልል “ወታደራዊ ትጥቆች እና ሠራዊቱን ለማንቀሳቀስ” ያደረገውን ጥረት በተማጽኖ ያስቀየሩ “የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች” በሰሜን ዕዝ ላይ “ጥቃት እና አጽያፊ ድርጊት ሲፈጸም መከላከል ቀርቶ ድርጊቱን ያላወገዙ ሆነው ተገኝተዋል” ያሉት ዶ/ር ለገሰ፤ መንግስት ለደረሰበት ውሳኔ ይህ አንድ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

መከላከያ ሰራዊቱ በትግራይ ክልል “ሕግ ለማስከበር እንቅስቃሴ ባደረገበት ጊዜ በመጀመሪያ አካባቢ የተባባሪነት መንፈስ ከህብረተሰቡ ቢታይም የኋላ ኋላ ግን በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደገና ከኋላ ተወግቷል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ “ተመሳሳይ ችግሮች ዳግም እንዳያጋጥሙ” መንግስት ይህን ውሳኔ እንዳስተላለፈ አስረድተዋል። መንግስት ውሳኔውን እንዲወስድ ካደረጉት ምክንያቶች ሁለተኛው፤ የኢትዮጵያ መንግስትን እና መከላከያ ሰራዊቱን ከ“እኩይ ሴራ እና ወጥመድ ለመከላከል” እንደሆነ በዛሬው መግለጫ ተጠቅሷል።
ህወሓት “በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የረገፉበትን በብዙ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሬሳዎች ጭኖ በመውሰድ በጅምላ በመቅበር በትግራይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል” የሚል ክስ ለማቅረብ እንደተዘጋጀ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። “ይህንን በማስተጋባት ኢትዮጵያ ላይ ቀጣይነት ያለው ፍርደ ገምድል ጫና ለማሳረፍ የተዘጋጁ አንዳንድ ዓለም አቀፍ አካላት” መኖራቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ለገሰ፤ “በሽብር ቡድኑ ሴራ እና ወጥመድ [ውስጥ] ላለመግባት” ጦሩ ባለበት እንዲቆይ መወሰኑን አስረድተዋል።
የመከላከያ ሰራዊት የሀገርን የግዛት አንድነት እና ሰላምን ለአደጋ የሚዳርግ ሁኔታ ተፈጥሯል ብሎ በሚታሰብበት በማንኛውም የትግራይ ክልል ቦታ በመግባት ህገ መንግስታዊ መብት ያለው መሆኑ ለውሳኔው በሶስተኛ ምክንያትነት ተጠቅሷል።

ሚኒስትሩ በዛሬው መግለጫቸው ከመከላከያ ሠራዊት በተጨማሪ የአማራ እና የአፋር ክልሎች የጸጥታ ኃይሎች የተሳተፉበት ዘመቻ፤ “በምስራቅ አማራ እና በአፋር አካባቢዎች በአሸባሪው ኃይል የተወረሩ አካባቢዎችን ነጻ በማውጣት የመጀመሪያውን ግብ” እንዳሳካ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት የመከላከያ ሰራዊት “ተልዕኮውን አጠናቆ አሁን የያዛቸውን አካባቢዎች አጽንቶ እንዲቆይ ታዟል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት፤ የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በሚዋሰኑበት አካባቢ የሚገኘውን የዋግ ኸምራ ዞን እና የዞኑ ዋና ከተማ የሆነችውን ሰቆጣ ከህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር መውጣታቸውን ይፋ ያደረገው ትላንት ረቡዕ ታህሳስ 13፤ 2014 ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ፤ ረዘም ላለ ጊዜ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር የቆዩት ወልዲያ እና ቆቦን ጨምሮ በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙ ከተሞች እና አካባቢዎች በመንግስት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ተመልሰው መግባታቸው በዚሁ ሳምንት ተገልጿል።
በአማጽያኑ ላይ ተመሳሳይ ድሎችን መቀዳጀቱን ሲገልጽ የሰነበተው የፌደራል መንግስት፤ እያካሄደ ያለው ወታደራዊ ዘመቻ ወደ ትግራይ ክልል እንደማይዘልቅ ይፋ አድርጓል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴን መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከትላንት በስቲያ በሰጡት ማብራሪያ “ህወሓት የጦር መሳሪያ የማግኘት ዕድል ኖሮት ይህቺን አገር ዳግም እንዳይዘርፍ ማረጋገጥ እንጂ ወታደራዊ ዘመቻውን በትግራይ የመቀጠል ፍላጎት የለውም” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)