በሃሚድ አወል
ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ “በአደጋ ላይ የሚገኝ ሰውን ባለመርዳት” ወንጀል ጥፋተኛ የተባለችው ላምሮት ከማል በሶስት ወር እስራት እንድትቀጣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወሰነ። ተከሳሿ ከተወሰነባት ቅጣት በላይ በእስር በመቆየቷ፤ ፍርድ ቤቱ በነጻ እንድትሰናበት አዝዟል።
የቅጣት ውሳኔውን ዛሬ አርብ ታህሳስ 15 ያስተላለፈው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ነው። ላምሮት ጥፋተኛ የተባለችበት የወንጀል አንቀጽ ከስድስት ወር የማይበልጥ ቀላል እስር ወይም መቀጮ የሚያስፈርድ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ ተከሳሿ ካቀረበቻቸው ሶስት የቅጣት ማቅለያዎች መካከል ሁለቱን በመቀበል የሶስት ወራት እስር ፈርዷል።
ተከሳሿ በተከላካይ ጠበቃዋ በኩል ያቀረበችው የመጀመሪያ የቅጣት ማቅለያ፤ ከዚህ በፊት በወንጀል ተከስሳም ሆነ ተቀጥታ የማታውቅ በመሆኗ ምንም አይነት የወንጀል ሪከርድ የሌለባት መሆኑን የሚገልጽ ነው። ተከሳሿ የልጅ እናት እና አሳዳጊ መሆኗን በሁለተኛ የቅጣት ማቅለያነት ለፍርድ ቤቱ አቅርባለች። በተከሳሿ የቀረበው ሁለተኛው የቅጣት ማቅለያ በሰነድ የተደገፈ በመሆኑ በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት አግኝቷል።
ሶስተኛው እና በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት ያላገኘው የተከሳሽ የቅጣት ማቅለያ ከተከሳሿ ማህበራዊ ህይወት ጋር የተያያዘ ነው። የቅጣት ማቅለያው ተከሳሿ በምትኖርበት “መቻሬ ኮንዶሚኒየም” በማህበራዊ ህይወቷ ንቁ ተሳታፊ መሆኗን የሚገልጽ ሲሆን ይህንንም የሚያስረዳ በአምስት የኮንዶሚኒየሙ ነዋሪዎች የተፈረመ ሰነድ የተያያዘበት ነው። ሆኖም ፍርድ ቤቱ በሰነዱ ላይ የፈረሙት ግለሰቦች የኮንዶሚኒየሙ ነዋሪዎች መሆናቸውን ማረጋጥ ስለማይቻል እና ሰነዱም ማህተም ያላረፈበት መሆኑን በምክንያትነት በመጥቀስ ሳይቀበለው ቀርቷል።
በከሳሽ ዐቃቤ ህግ በኩል ሁለት የቅጣት ማክበጃዎች ለፍርድ ቤቱ የቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ሁለቱንም ውድቅ አድርጓቸዋል። የመጀመሪያው የቅጣት ማክበጃ የወንጀል ድርጊቱ “መጥፎ ነገር ለመስራት ፍጹም ፍቃደኛ በመሆን የተፈጸመ ነው” የሚል ነው። “ተከሳሿ ወንጀሉን ለመፈጸም ፍጹም ፍቃደኛ መሆኗን የሚያስረዳ ማስረጃ አልቀረበም” ያለው ፍርድ ቤቱ፤ የዐቃቤ ህግ የቅጣት ማክበጃ “ምክንያታዊነት የሚጎድለው ነው” በሚል ሳይቀበለው ቀርቷል።
ዐቃቤ ህግ በሁለተኛነት ያቀረበው የቅጣት ማክበጃ፤ የወንጀል ድርጊቱ ሟች የተከሳሽን እርዳታ በሚፈልግበት፣ በሌሊት የተፈጸመ መሆኑን ነው፡፡ ችሎቱ የዐቃቤ ህግ የቅጣት አስተያያት “የወንጀል ህጉን ያላገናዘበ መሆኑን” በመጥቀስ ሁለተኛውንም ማክበጃ ውድቅ አድርጎታል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት፤ በተከሳሿ ላይ የቅጣት ውሳኔውን ካስተላለፈ በኋላ ሁለት ትዕዛዞችን ሰጥቷል። ተከሳሿ በዛሬው ዕለት ከተወሰነባት የእስራት ቅጣት በላይ የታሰረች በመሆኑ ከዛሬ ጀምሮ ከእስር እንድትፈታ ፍርድ ቤቱ አዝዟል።
ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ በተገደለበት ዕለት ድምጻዊው በሚያሽከረክረው መኪና ውስጥ አብራው የነበረችው ላምሮት ከማል፤ ከሰኔ 2012 ጀምሮ ለአንድ አመት ከአምስት ወር በማረሚያ ቤት ቆይታለች። ተከሳሿ ከአንድ ወር በፊት ህዳር 9፤ 2014 በአምስት ሺህ ብር ዋስትና በፍርድ ቤት ከተወሰነላት በኋላ ጉዳዩዋን በውጭ ሆና ስትከታተል ቆይታለች። የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዛሬው ውሎው፤ ተከሳሽ ለዋስትና ያስያዘችው ገንዘብ ወይም ንብረት ካለ እንዲመለስላት አዝዟል።
ተከሳሿ “በአደጋ ላይ የሚገኝ ሰውን ባለመርዳት” ወንጀል ጥፋተኛ የተባለችው ትላንት ሐሙስ ታህሳስ 14 ነበር። የላምሮትን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔውን ያስተላለፈው፤ ተከሳሿ የተከሰሰችበትን ወንጀል ሊከላከልላት የሚችል የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ ባለማቅረቧ መሆኑን ገልጾ ነበር።
የትላንቱን የፍርድ ቤት ውሎ በመንግስት ከተመደበላት ተከላካይ ጠበቃዋ ጋር በመሆን በችሎት ተገኝታ የተከታተለችው ላምሮት፤ የቅጣት ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማረፊያ ቤት እንድትቆይ ተደርጋለች። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የደንብ ልብስ በለበሱ ፖሊሶች ታጅባ ዛሬ ችሎት ፊት የቀረበችው ተከሳሿ፤ የቅጣት ውሳኔ በዳኛ ሲነበብ ስታለቅስ ታይታለች። ሁኔታዋን ያስተዋሉት የመሃል ዳኛ የፍርድ ቤት ሂደቱን ተቀምጣ እንድትከታተል የፈቀዱላት ቢሆንም ከችሎት እስክትወጣ ድረስ ግን ማልቀሷን አላቆመችም ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)