ምርጫ ቦርድ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የቀረቡ አቤቱታዎችን የሚያጣሩ ቡድኖችን ማሰማራቱን አስታወቀ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቧቸውን አቤቱታ እና ቅሬታዎች የሚያጣራ ኮሚቴ አዋቅሮ የማጣራት ስራ መጀመሩን አስታወቀ። ኮሚቴው ከምርጫ ቦርድ፣ ከገዢው ብልጽግና ፓርቲ እና ቅሬታ ካቀረቡ ፓርቲዎች የተውጣጡ አባላትን መያዙ ተገልጿል። 

በኮሚቴው የሚዋቀሩ አጣሪ ቡድኖች “ቅሬታ በቀረበባቸው ክልሎች ተገኝተው የማጣራት ስራውን እንደሚሰሩ” የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናግረዋል። የቦርድ ሰብሳቢዋ ዛሬ ሰኞ ታህሳስ 18 ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንዳሉት፤ አጣሪ ቡድኖቹ በሶስት ክልሎች ተሰማርተው ስራ ጀምረዋል። 

ከአጣሪ ቡድኖቹ አንዱ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በርካታ ቅሬታ ባቀረቡበት በአዲስ አበባ ከተማ ተመሳሳይ የማጣራት ስራ በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል። በከተማ አስተዳደሩ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ አቅርበዋል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ ህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ቅሬታ ያቀረቡ ፓርቲዎች ናቸው።

በደቡብ ክልል አራት ፖለቲካ ፓርቲዎች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ቅሬታቸውን ለቦርዱ አቅርበዋል። በክልሉ ቅሬታቸውን ያቀረቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የዶንጋ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ናቸው። 

የምርጫ ቦርድ፣ የገዢው ብልጽግና እና የቅሬታ አቅራቢዎቹን ተወካዮች ያቀፈው አጣሪ ቡድን ዛሬ ወደ ደቡብ ክልል ያቀናል። ቅሬታ ከቀረበባቸው ክልሎች አንዱ ወደ ሆነው ወደ ሲዳማ ክልል የሚላከው አጣሪ ቡድን ደግሞ ከነገ በስቲያ ረቡዕ ታህሳስ 20 ወደ ስፍራው ይጓዛል። በሲዳማ ክልል ቅሬታቸውን ለምርጫ ቦርድ ያቀረቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሲዳማ ሕዝብ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እና የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ናቸው። 

እያንዳንዳቸው አንዳንድ ቅሬታ ወደ ቀረበባቸው የአማራ ክልል እና አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልል፤ የአጣሪ ቡድኖች ወደ ቦታው ተልከው ስራ መጀመራቸው በዛሬው ስብሰባ ላይ ተገልጿል።  የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት በአማራ ክልል፤ ኢዜማ ደግሞ በአዲሱ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቅሬታ አቅርበዋል። 

እንደ ሁለቱ ክልሎች ሁሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም አንድ ቅሬታ ቀርቧል። ቅሬታውን ያቀረበው በክልሉ የሚወዳደረው የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጸነት ንቅናቄ ነው። የፓለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ቦርድ ቅሬታ እንዲያቀርቡ መነሾ የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኢትዮጵያ የተደነገገው ጥቅምት 23፤ 2014 ነው። አዋጁ ከተደነገገበት ቀን ጀምሮ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ ሆኖ ይቆያል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)