በሃሚድ አወል
ላለፉት 47 ቀናት መደበኛ የዳኝነት አገልግሎታቸውን በከፊል ገድበው የቆዩት በአማራ ክልል የሚገኙ ፍርድ ቤቶች፤ ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ ውሳኔ ተላለፈ። ፍርድ ቤቶቹ ከትላንት ሰኞ ታህሳስ 18፤ 2014 ጀምሮ ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲገቡ ውሳኔ ያስተላለፈው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህን ውሳኔውን ያሳወቀው በክልሉ ለሚገኙ 13 የዞን ፍርድ ቤቶች፣ ሶስት ምድብ ችሎቶች እና ሶስት የዳኝነት አገልግሎት የስራ ሂደቶች በትላንትናው ዕለት በጻፈው ደብዳቤ ነው። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔው በተዋረድ ለወረዳ ፍርድ ቤቶች እንዲተላለፍም ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በክልሉ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ካለፈው ህዳር 1፤ 2014 ጀምሮ የዳኝነት አገልግሎታቸውን በከፊል ሲሰጡ የቆዩት በክልሉ ሲካሄድ በቆየው ጦርነት ምክንያት ነው። ባለፈው አንድ ወር ከአስራ አምስት ቀናት ውስጥ በክልሉ ፍርድ ቤቶች ሲስተናገዱ የቆዩት፤ የፍትሐ ብሔር ክርክሮች እንዲሁም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና ከክልሉ ዝርዝር የዘመቻ አፈፃፀም መመሪያ ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ጉዳዮች ብቻ ነበሩ።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አብዬ ካሳሁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ የክልሉ ፍርድ ቤቶች መደበኛ አገልግሎታቸው እንዲገደብ ከተወሰነበት ምክንያት አንደኛው “ወረራውን ለመመከት እና የተጀመረውን ጦርነት በሰው ኃይል እና በገንዘብ በአግባቡ ለመደገፍ” የሚል ነበር። የአማራ ክልል በስሩ የሚገኙ ተቋማት ከጥቅምት 21 ጀምሮ መደበኛ ስራቸውን እንዲያቆሙ ያስተላለፈው ውሳኔም ለዳኝነት አገልግሎቱ መገደብ ሌላኛው ምክንያት እንደነበርም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ጥቅምት 21 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ “ማንኛውም የመንግስት ተቋም መደበኛ አገልግሎቱን አቋርጦ” ክልሉ የገጠመውን “የህልውና ዘመቻ ለመቀልበስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንዲረባረብ” የተላለፈውን ውሳኔ ማጽደቁ አይዘነጋም። በውሳኔው መሰረት የክልሉ ተቋማት በጀታቸውን እና ተሽከርካሪዎቻቸውን “ለህልውና ዘመቻው” የማዋል ግዴታ ተጥሎባቸው ነበር።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዚህ ውሳኔ አስር ቀናት በኋላ በክልሉ ያሉ ፍርድ ቤቶች ከመደበኛ ስራቸው እንዲገደቡ ውሳኔ አስተላልፏል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት “መመሪያ አውጥተን ነበር ስራ ያቆምነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ ለሚመለከታቸው ተቋማት ትላንት ባሰራጨው ደብዳቤ፤ ጥቅምት 30፤ 2014 ተላልፎ የነበረው ይህ መመሪያ “ቀሪ መሆኑን” አሳውቋል።

መመሪያው ተሽሮ ፍርድ ቤቶች ወደ መደበኛ አገልግሎታቸው እንዲመለሱ ከተወሰነባቸው ምክንያቶች አንዱ፤ የክልሉ መንግስት በስሩ ያሉ ተቋማት የመደበኛ አገልግሎታቸውን እንዲያቆሙ የወሰነውን ውሳኔ ማንሳቱ እንደሆነ አቶ አብዬ ገልጸዋል። የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የክልሉ “ተቋማት ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰው የተሰጣቸውን ህጋዊና ህዝባዊ ኃላፊነት እንዲወጡ” ውሳኔ ያሳለፈው ከአራት ቀናት በፊት ባለፈው ሐሙስ ነበር።
የክልሉ ፍርድ ቤቶች ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ የተወሰነበት ሌላኛው ምክንያት ከተገልጋዮች የሚቀርቡ አቤቱታዎች መብዛት እንደሆነ አቶ አብዬ ተናግረዋል። ፍርድ ቤቶች ዝግ በነበሩበት ወቅት “ንብረቴን ተዘርፍኩ” የሚሉ አቤቱታዎች ይቀርቡ እንደነበር የሚገልጹት አቶ አብዬ፤ የፍርድ ቤቶች ከመደበኛ ስራ ውጭ መሆናቸው “በተከራካሪዎች እና መብት ጠያቂዎች ላይ ችግር አስከትሏል” ይላሉ።
በክልሉ ጦርነት እየተካሄደም ቢሆን ፍርድ ቤቶች ስራቸውን ማከናወን ይችላሉ የሚል ስምምነት ላይ መደረሱ የዳኝነት አገልግሎቱ ወደ ነበረበት ለመመለስ በተጨማሪ ምክንያትነት ቀርቧል። ፍርድ ቤቶች የህልውና ዘመቻውን እየደገፉ “ስራቸውን መስራት የሚችሉ መሆኑን አረጋግጠናል” ብለዋል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)