የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን “በኢትዮጵያ በአፋጣኝ ግጭት የማቆም አስፈላጊነት” ላይ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ። አሁሩ እና ብሊንከን ከዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት፤ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ሁኔታን ጨምሮ በክፍለ አህጉሩ የጸጥታ ጉዳይ ላይ ትላንት ማክሰኞ በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ነው ተብሏል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትላንት ማክሰኞ ምሽት ባወጡት መግለጫ፤ ኡሁሩ እና ብሊንከን በኢትዮጵያ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ሊኖር፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሊቆም እንደሚገባ ከስምምነት መድረሳቸውን ገልጸዋል።
ኡሁሩ እና ብሊንከን በውይይታቸው ተስማሙባቸው ከተባሉ ጉዳዮች መካከል አንድ አመት ላስቆጠረው የኢትዮጵያ ግጭት “በድርድር” መፍትሔ የማበጀት አስፈላጊነት ይገኝበታል። ለዚህም አንቶኒ ብሊንከን የአፍሪካ ህብረት ልዩ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እና የኬንያው ፕሬዝዳንት ለሚያደርጉት “የማሸማገል ጥረት” ሀገራቸው “ጠንካራ ድጋፍ እንደምታደርግ” መናገራቸውን ኔድ ፕራይስ አስታውቀዋል።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለፈው ህዳር ወር ወደ ናይሮቢ አቅንተው ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል። ከውይይቱ በኋላ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኬንያ አቻቸው ራቼል ኦማሞ “የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ከተኩስ አቁም ስምምነት ይደርሳሉ” የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)