በሃሚድ አወል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ለማቋቋም የቀረበውን አዋጅ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ። ምክር ቤቱ አዋጁን ያጸደቀው ዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 20፤ 2014 ባካሄደው ሁለተኛ ልዩ ስብሰባው ነው።
በዛሬው ልዩ ስብሰባ ከተገኙ 301 የምክር ቤቱ አባላት መካከል አስራ ሶስቱ አዋጁን ተቃውመው ድምጽ ሰጥተዋል። አንድ የምክር ቤት አባል ደግሞ ድምጻቸውን ከመስጠት ታቅበዋል። አዋጁ በአብላጫ ድምጽ የጸደቀው፤ የኮሚሽኑ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ያስነሱ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ በማድረግ ነው።
ማሻሻያ የተደረገበት የመጀመሪያው ጉዳይ የኮሚሽነሮች አሰያያም ነው። በማሻሻያው መሰረት የኮሚሽነሮችን ጥቆማ የሚቀበለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መሆኑ ቀርቶ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት እንዲሆን ተወስኗል። የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን 11 ኮሚሽነሮች እንደሚኖሩት በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ተቀምጧል።
በአዋጁ ረቂቅ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሰጥተው የነበሩ ኃላፊነቶችም የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ኃላፊነቶች ሆነዋል። አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ደንቦችን የማውጣቱ ኃላፊነትም ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ወደ ተወካዮች ምክር ቤት ተሸጋግሯል። ኮሚሽኑ የምክክር አጀንዳዎችን፣ የምክከሮቹን ሂደት እና ምክረ ሃሳቦች ሪፖርት የሚያቀርበው ለመንግስት ብቻ መሆኑ ቀርቶ፤ ለተወካዮች ምክር ቤት እና ለአስፈጻሚ አካላትም እንዲሆን ተሻሽሏል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ለማቋቋም የቀረበው አዋጅ በረቂቅ ደረጃ ከነበረው ሁለት አንቀጾች እንዲጨመሩበትም ተደርጓል። በአዋጁ ላይ የተጨመረው አንደኛው አንቀጽ የኮሚሽኑን ኮሚሽነሮች የሚመለከት ነው። የተጨመረው አንቀጽ “ከኃላፊነት የተነሳ ወይም ኃላፊነቱን በገዛ ፈቃዱ የለቀቀ ኮሚሽነር ለሁለት ዓመት ለሌላ መንግስታዊ ኃላፊነት አይታጭም” ሲል ይደነግጋል።
ሁለተኛው አንቀጽ ከኮሚሽኑ ሰነዶች ጋር የተያያዘ ነው። ኮሚሽኑ የስራ ጊዜው ሲያበቃ በኮሚሽኑ የስራ ዘመን የተዘጋጁ ሰነዶች እና የተያዙ ሰነዶችን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት እና ለብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻህፍት አገልግሎት የማስረከብ ኃላፊነት እንዳለበት በዚህ አንቀጽ ላይ ተቀምጧል። የብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻህፍት አገልግሎት ሰነዶቹን ማየት እና መጠቀም ለሚፈልጉ ሰዎች መጠቀም እንዲችሉ ማመቻቸት እንዳለበት የሚደነገግ ንዑስ አንቀጽም ተካቶበታል።
የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ማሻሻያዎች ተካተውበት ከመጽደቁ በፊት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሁለት ሰዓታትን የፈጀ ውይይት አድርገውበታል። የህግ፣ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ አዋጁን በተመለከተ ሪፖርት እና ውሳኔ ሃሳብ በንባብ ካቀረቡ በኋላ 17 የምክር ቤት አባላት ጥያቄ እና አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።
አዋጁ የተዘጋጀበትን እና እንዲጸድቅ የተፈለገበትን ጊዜ እንዲሁም በምክክሩ የሚሳተፉ አካላትን በተመለከተ የተነሱት ጥያቄዎች ጎልተው ተደምጠዋል። አንድ የምክር ቤት አባል ወቅታዊ የሀገሪቱን ሁኔታ በማንሳት “[አሁን] በተረጋጋ መንገድ ምክክሩን ማካሄድ ይቻላል ወይ?” የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
ሌሎች የምክር ቤት አባላት ደግሞ ከአዋጁ መጽደቅ እና ሀገራዊ ምክክር ከማድረግም በፊት የሚቀድሙ “ሌሎች ተግባራት አሉ” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። ይህን መሰል አስተያየት ከሰጡ የፓርላማ አባላት መካከል የቀድሞው የደቡብ ወሎ አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሐመድ ይገኙበታል።
በሀገራዊ ምክክሩ “ሁሉም ኢትዮጵያዊ መሳተፍ አለበት” የሚሉት አቶ ሰይድ፤ “ለምክክሩ ዝግጁ ያልሆኑ” ቦታዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። የብልጽግና ፓርቲ የፓርላማ ተመራጩ አቶ ሰይድ፤ ሀገራዊ ምክክር ከማድረግ በፊት “ለምክክሩ ዝግጁ አይደሉም” ያሏቸውን ቦታዎች “ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ማድረግ ይቀድማል” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮችም በተመሳሳይ ከምክክሩ በፊት መቅደም ያለባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን በስብሰባው ላይ አንስተዋል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲን በመወከል ምክር ቤቱን የተቀላቀሉት አቶ ባርጠማ ፍቃዱ፤ “ቅድሚያ የሚሰጠው የጦርነቱ ጉዳይ ሆኖ ሳለ ለምን ወደዚህ አጀንዳ ተገባ?” ሲሉ ጠይቀዋል። የማቋቋሚያ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት “በህዝቡ ውይይት ሊደረግበት፤ በምሁራንም ሊገመገም ይገባ ነበር” ሲሉም ተደምጠዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔም “አዋጁን ለማጽደቅ እየተሄደበት ያለው የችኮላ ስሜት “ጥርጣሬ ይፈጥራል” ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየት ሰንዝረዋል። ዶ/ር ደሳለኝ ከምክከሩ በፊት “ጦርነቱ ማለቅ አለበት” ሲሉ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚሉትን ጉዳይ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎች ጉዳይም ከምክር ቤት አባላቱ ሰፋ ያለ ጥያቄ እና አስተያያት ተነስቶበታል። አብዛኛዎቹ የምክር ቤት አባላት በተወካዮች ምክር ቤት “በሽብርተኝነት” የተፈረጀው ህወሓት “በአገራዊ ምክክሩ መሳተፍ የለበትም” የሚል አቋም አራምደዋል።
ፕሮፌሰር መሐመድ አብዶ የተባሉ የምክር ቤት አባል “ምክክሩ [በምክር ቤቱ] በሽብርተኝነት የተፈረጁ አካላትን አያካትትም የሚል ሐረግ በአዋጁ ላይ መካተት አለበት” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ሌሎች የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው በምክከሩ ተሳታፊ ለመሆን ቅድመ ሁኔታዎች ሊቀመጡ እንደሚገባ ገልጸዋል። የተቃዋሚው አብን አመራር የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ “ኢትዮጵያን እንደ ሀገረ መንግስት ያልተቀበለ አካል በምክክሩ መሳተፍ የለበትም” ሲሉ ጠንከር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል።
የተወካዮች ምክር ቤት ህግ፣ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ፤ ለተነሱት ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ማብራሪያ አቅርበዋል። አገራዊ ምክክር በዚህ ጊዜ የማካሄድ ተገቢነት ላይ ጥያቄ ላነሱ የፓርላማ አባላት፤ “ምክክር ማካሄድም ሆነ፤ የምክክር ኮሚሽን የማቋቋሙ ስራ ዘግይቷል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። እርሳቸው የሚመሩት ቋሚ ኮሚቴ ከህዝብ ጋር ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይም “ይሄ ኮሚሽን ፈጥኖ ሊቋቋም ይገባ ነበር” የሚል አስተያየት መቀበሉንም ለምክር ቤት አባላቱ ገልጸዋል።
በምክከሩ የሚሳተፉ አካላትን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ በሰጡት ምላሽ “የአዋጁ አላማ ቡድኖች ይወያያሉ፤ አይወያዩም አይደለም። ህዝቡ እንዲወያይ ነው” ብለዋል። በምክከሩ የሚሳተፉ አካላት ማንነት የሚወሰነው የተወካዮች ምክር ቤት ወደፊት በሚያወጣቸው ደንቦች እንደሆነም አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)