የሰሞነኛው የኮሮና ታማሚዎች ብዛት፤ በኢትዮጵያ “አዲስ የኮቪድ 19 ወጀብ መከሰቱን ያሳያል” ተባለ

በሀሴት ሀይሉ 

በኢትዮጵያ ባለፉት 15 ቀናት በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ፤ በሀገሪቱ አዲስ የኮቪድ 19 ወጀብ መከሰቱን የሚያሳይ እንደሆነ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። በኮቪድ 19 የመያዝ ምጣኔ በትላንትናው ዕለት ብቻ በ36 በመቶ ማሻቀቡን ኢንስቲትዩቱ ገልጿል። 

ኢንስቲትዩቱ ይህን ያለው በኢትዮጵያ ከሰሞኑ የተከሰተውን “ጉንፋን መሰል” ወረርሽኝን አስመልክቶ ዛሬ አርብ ታህሳስ 22 ባወጣው መግለጫ ነው። ወረርሽኙን ተከትሎ ኢንስቲትዩቱ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ተቋማት የመስክ ቅኝት ማድረጉን እና የናሙና ምርመራ ማካሄዱን በዛሬው መግለጫው ጠቅሷል። 

በዚህም መሰረት የናሙና ምርመራ ከተደረገላቸው ዜጎች ውስጥ፤ ከ59 እስከ 86 በመቶ የሚሆኑት ኮቪድ እንደተገኘባቸው ተቋሙ አስታውቋል። በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ጤና ተቋማት ሄደው ምርመራ ከተደረገላቸው 55,562 ሰዎች ውስጥ፤ 25,191 ያህሉ የኮሮና ቫይረስ እንዳለባቸው መረጋገጡንም ጨምሮ ገልጿል። 

ካለፈው ሳምንት አርብ ታህሳስ 15 ጀምሮ እስከ ትላንትናው ዕለት ድረስ፤ የኮቪድ ምልክት ለታየባቸው 83,237 ሰዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ የላብራቶሪ ምርመራ መደረጉን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመግለጫው አመልክቷል። በእነዚህ ሰባት ቀናት ውስጥ ምርመራ ከተደረገላቸው ዜጎች መካከል 29,279 ያህሉ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል ተብሏል። በዚህ ጊዜ ውስጥ 260 ሰዎች በጽኑ መታመማቸውን እና 41 ሰዎችም ህይወታቸውን ማጣታቸውን ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው አስፍሯል።

በኢትዮጵያ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ በኮቪድ 19 የመያዝ ምጣኔ በተከታታይ ጭማሪ ማሳየቱ በዛሬው የኢንስቲትዩቱ መግለጫ ተነስቷል። ከሁለት ሳምንት በፊት የነበረው በኮቪድ 19 የመያዝ ምጣኔ አምስት በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን፤ ይህ አሃዝ በትላትናው ዕለት ብቻ ወደ 36 በመቶ ማደጉ ተገልጿል። 

“እየተስተዋለ ያለው የወረርሽኙ ጭማሪ፤ በሀገራችን አዲስ የኮቪድ 19 ወጀብ መከሰቱን ያሳያል” ያለው ኢንስቲትዩቱ፤ እያሻቀበ የመጣውን የኮሮና ስርጭትን ለመግታት ሕብረተሰቡ የኮቪድ መከላከያ መንገዶችን ያለመሰልቸት እንዲተገብርም አሳስቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)