የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የስራ ዘመኑ እንዲራዘም ጥያቄ አቀረበ

በሃሚድ አወል

የስራ ዘመኑ በዚህ ዓመት የሚጠናቀቀው የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን፤ የስራ ጊዜው ለተጨማሪ ሶስት ዓመታት እንዲራዘም  ለሰላም ሚኒስቴር ጥያቄ አቀረበ። ኮሚሽኑ የስራ ዘመኑ እንዲራዘም ጥያቄ ያቀረበው፤ እያከናወናቸው ያላቸውን ጥናቶች “በጊዜ አጠናቅቆ መጨረስ ባለመቻሉ” መሆኑን የኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አወል ሁሴን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ከአስተዳደር ወሰኖች፣ ራስን በራስ ከማስተዳደር እና ከማንነት ጋር የተያያዙ ግጭቶችንና መንስኤዎቻቸውን በመተንተን የመፍትሔ ሃሳቦችን ለሚመለከታቸው አካላት እንዲያቀርብ በየካቲት 2011 የተቋቋመው ይህ ኮሚሽን፤ የስራ ዘመኑ ሶስት ዓመት እንደሚሆን በአዋጅ ተደንግጓል።  ሆኖም የኮሚሽኑ የስራ ዘመን “እንደ ሁኔታው” ታይቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊራዘም እንደሚችል በአዋጁ ላይ ተቀምጧል።

በማቋቋሚያ አዋጁ መሰረት የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የነበረ ቢሆንም፤ ከሶስት ወራት በፊት የጸደቀው የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣን እና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ግን ይህን በመቀየሩ የስራ ዘመን የማራዘም ጥያቄው የቀረበውም ይህንኑ ተከትሎ መሆኑን አቶ አወል ገልጸዋል። በአዲሱ አዋጁ መሰረት የኮሚሽኑን ተጠሪነት የተላለፈው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሰላም ሚኒስቴር ነው። 

ፎቶ፦ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ቪዲዮ የተወሰደ

ኮሚሽኑ የስራ ዘመኑን ለማራዘም ያስገደዱትን ሀገር አቀፍ ጥናቶች በጊዜ ማጠናቀቅ ያልቻለው “በችግሮቹ ስፋት እና ጥልቀት” ምክንያት መሆኑን አቶ አወል ይናገራሉ። በአስተዳደር ወሰን፣ ማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ያሉት ችግሮች ሰፊ በመሆናቸው ኮሚሽኑ በተሰጠው የሶስት ዓመት የስራ ዘመን ጥናቶቹን ማጠናቀቅ እንዳልቻለ አቶ አወል ያብራራሉ።  

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ኮሚሽኑ የጥናት ቡድኑን አለማሰማራቱ ሌላው ለጥናቶቹ አለመጠናቀቅ በምክንያትነት የተጠቀሰ ጉዳይ ነው። የትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ በኮሚሽኑ ጥናት አለመካተቱን የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በደቡብ፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስር ያሉ የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎችም እንዲሁ አጥኚዎች አለመሰማራታቸውን አስረድተዋል።   

“የትግራይ ክልል ‘ኮሚሽኑ ህጋዊ አይደለም፤ ህገ መንግስቱን ይጥሳል’ የሚል ክስ እና ወቀሳዎችን ሲያቀርብ ነበር” የሚሉት አቶ አወል፤ በዚህም ምክንያት “ከትግራይ ክልል ጋር በቅርበት መስራት አልቻልንም” ሲሉ ክልሉ በጥናቱ ያልተካተተበትን ምክንያት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል መንግስት እውቅና ከመነገፈጉ በተጨማሪ በክልሉ የተቀሰቀሰው ጦርነትም ጥናቱን በስፍራው እንዳያደርግ ያገደው ሌላው ምክንያት መሆኑንም አክለዋል።  

የትግራይ ክልል የኮሚሽኑን ምስረታ “ኢ-ህገ መንግስታዊ” ነው ሲል በተደጋጋሚ ተቃውሞውን ሲያሰማ መቆየቱ የሚታወስ ነው። የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበት ወቅትም፤ 33 የትግራይ ክልል የፓርላማ ተወካዮች ተቃውመውት እንደነበር አይዘነጋም። እነዚህ የፓርላማ አባላት የኮሚሽኑ መቋቋም “የክልል ምክር ቤቶችን እና የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ስልጣን ይጋፋል” በሚል ነበር ተቃውሟቸውን ያስመዘገቡት።

ኮሚሽኑ ከጅምሩ እንዲህ አይነት ተግዳሮቶች ቢገጥሙትም፤ ከሰኔ 2012 ጀምሮ ዋነኛ ስራው የሆነውን የአስተዳደር ወሰን፣ የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳዮች ላይ አገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ስራን ሲያከናውን መቆየቱን ባለፈው ሳምንት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። በመላው ኢትዮጵያ ባሉ 56 ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ላለፉት 18 ወራት ሲካሄድ የቆየው አገር አቀፍ ጥናት “መጨረሻ ደረጃ ላይ” መድረሱንም ኮሚሽኑ በዚሁ መግለጫው ጠቁሟል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለቤትነት በተመራው እና 28 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፈውበታል በተባለው በዚሁ ጥናትና ምርምር “በርካታ በምክረ-ሀሳብነት ደረጃ ሊቀርቡ የሚችሉ ግኝቶች” መለየታቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል። ከግኝቶቹም መካከል “ከመዋቅራዊ አደረጃጀት ጋር የተገናኙ እንዳሉበት” የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ በዚህ አገራዊ የጥናት ውጤት ላይ ተከታታይ የባለድርሻ አካላት ውይይት በማካሄድ ተጨማሪ ግብዓት ለመሰብሰብ መታቀዱን አመልክቷል። በውይይቶቹ የሚገኙ ግብዓቶቹን በማካተትና በማዳበርም የጥናቱን ውጤት ይፋ የሚደረግ ይደረጋል ተብሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)