በሃሚድ አወል
ከሳዑዲ አረቢያ የሚመለሱ የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ሂዩማን ራይትስ ዎች በትላንትናው ዕለት ያወጣው ሪፖርት “ድርሰት ነው” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አጣጣለ። የሚኒስቴሩ ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ ዛሬ ሐሙስ በሰጡት መግለጫ፤ የተቋሙ ሪፖርት “በኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ያሉ ጫናዎች አካል ነው” ብለዋል።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ትላንት ረቡዕ ታህሳስ 27 ባወጣው ሪፖርት፤ ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ የመብት ጥሰት መፈጸሙን ገልጾ ነበር። ተቋሙ በዚሁ ሪፖርቱ፤ ከስደት ተመላሾቹ ላይ “የዘፈቀደ እስር እና እንግልት ደርሶባቸዋል፤ ደብዛቸውም ጠፍቷል” ሲል ወንጅሏል።
የሂዩማን ራይትስ ዎች የስደተኞች እና የስደተኛ መብት ተመራማሪ ናዲያ ሃርድማን “በሳዑዲ እስር ቤት አሰቃቂ በደል የደረሰባቸው የትግራይ ተወላጆች፤ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ በማቆያ እስር ቤቶች እየተቆለፉ ይገኛሉ” ማለታቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል። በአዲስ አበባ በሚገኙ መቀበያ ማዕከላት “ከህግ ውጭ እንዲቆዩ ተደርገዋል” ከተባሉ ከስደት ተመላሾች በተጨማሪ ወደ ትግራይ ክልል የተጓዙትም ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ እንደገጠማቸው ሪፖርቱ አመልክቷል።
እንደ ሪፖርቱ ገለጻ ወደ ትግራይ ክልል የተጓዙ ከስደት ተመላሾች፤ ከኬላዎች ወይም ከሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ ተይዘው በአፋር እና ደቡብ ክልል ወደሚገኙ እስር ቤቶች ተወስደዋል። ከስደት ተመላሾቹ ከእነዚህ ቦታዎች በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ማዕከላት ታስረው እንደሚገኙ ሪፖርቱ ጠቁሟል።
ለሂዩማን ራይትስ ዎች ውንጀላ የኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ ምን እንደሆነ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ፤ “በሰፈር፣ በማንነት የተለየ እና የተጎዳ ሰው አልነበረም። እንደዚያ አይነት አሰራርም አልነበረም” ሲሉ የተቋሙን ሪፖርት አስተባብለዋል።
“ሂዩማን ራይትስ ዎች ኢትዮጵያን በሚመለከት መዓት ድርሰቶች አሉት” ሲሉ በሳምንታዊ መግለጫቸው ላይ የተናገሩት ቃል አቃባዩ፤ “ይሄም ከድርሰቶቹ አንዱ ነው” ሲሉ የተቋሙን የትላንት ሪፖርት አጣጥለውታል። በጉዳዩ ላይ ከዚህ በላይ ማብራሪያ የሚሰጠበት እንዳልሆነም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)