ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት “በሰላም መንገድ እንዲጠናቀቅ እናደርጋለን” አሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “አሁን የገጠምነውን ጦርነት በሰላም መንገድ እንዲጠናቀቅ እናደርጋለን” አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ አርብ ታህሳስ 29 ባወጡት መግለጫ፤ ለእርምትና ለይቅርታ ቦታ በመስጠት የምሕረትን መንገድ መከተል እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው መግለጫቸው በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በላይ ከዘለቀው ጦርነት ጋር በተገናኘ ስለ ድል፣ ይቅርታ እና ምህረት በሰፊው አውስተዋል። መንግስታቸው በጦርነቱ ካስመዘገበው ድል ማግስት የሚከተላቸውን አራት መርሆዎችንም አሳውቀዋል።

“ጦርነት ውስጥ የገባነው ሰላምን በሌላ በምንም መልኩ ለማምጣት ስላልቻልን ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሰላምን የማረጋገጫ የመጨረሻው አማራጭ እንደነበር ጠቁመዋል። ጦርነት “ወደ ሰላም ለመምጣት ያልቻሉ ኃይሎችን” ወደ ሰላም ጠረጴዛ ለማምጣት “የመጨረሻ ጉልበት” እንደነበርም በመግለጫቸው አንስተዋል። 

የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገር ውስጥ በህወሓት እና ሸኔ አማካኝነት፤ ከውጭ በኩል ደግሞ “ከቅርብ እና ከሩቅ” የኢትዮጵያ ጠላቶች “በሁለት አቅጣጫ ጥቃት እንደተሰነዘረበት” ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንንም “በብቃት እየመከተ” እንደሚገኝ ገልጸዋል። “ጀግና ህዝብ በቀኝ እጁ ድልን ጨብጦ በግራ እጁ ይቅርታ እና ምህረትን የሚቸር ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ ቀደም የነበረውን ይህን ዕሴት ዛሬም ተግባራዊ ሊያደርገው እንደሚገባ አሳስበዋል።  

“በባህላችን የግጭት መቋጫው ዕርቅ እና ይቅርታ ነው። ደም የተቃቡ ጠበኞችን ጭምር እስከማጋባት የሚደርስ የዕርቅና የሰላም ዕሴት ያለን ሕዝቦች ነን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ከ126 ዓመት በፊት የተካሄደው የአድዋ ጦርነትን በአስረጂነት በማንሳትም የምሕረትን አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተዋል። ኢትዮጵያውያን በአድዋ ጦርነት የማረኳቸውን የጣልያን ወታደሮች “በአሸናፊ ምሕረት” መማራቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዛሬም ተመሳሳዩን ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።  

“ዛሬም ኢትዮጵያ በአሸናፊነት ክብር ላይ ናት። ፍትሕ ያልተለየው ምሕረትን አብሮ በማስኬድ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ እናደርጋለን። በአንድ በኩል በደልና ጥፋትን በፍትሕ መንገድ እያየን፣ በሌላ በኩል ለእርምትና ለይቅርታ ቦታ በመስጠት የምሕረትን መንገድ መከተል አለብን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በኢትዮጵያ “እርቅ እና ሰላም” እንደሚያስፈልግ ሲገልጹ፤ በሁለት ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜያቸው ነው። በትላንትናው ዕለት ባስተላለፉት የገና በዓል መልዕክታቸው መደምደሚያ ላይም “በሀገራችን የተፈጸሙ መበዳደሎችን ለመሻር በዚህ ሰዓት ሀገራዊ እርቀ ሰላም ያስፈልገናል” ሲሉ የሰላምን ጉዳይ አንስተው ነበር። 

የዛሬው መግለጫቸው ደግሞ “ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ድሮም ልባችን ክፍት ነበር፤ ወደፊትም የሰላም እጃችን አይታጠፍም” ሲሉ በሀገሪቱ ያለውን ጦርነት በሰላም ለመፍታት ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዋል። ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ መፍታት የመንግስታቸው የመጀመሪያ ምርጫ መሆኑን በዛሬው መግለጫቸው ያሰመሩበት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ “ሰላማዊ መንገድ አድካሚና አታካች ቢመስልም ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳትን ይቀንሳል” ብለዋል።

መንግስታቸው “የሰላም፣ የይቅርታና የፍቅር መንገድ” የሚከተል ቢሆንም፤ ሊጣሱ የማይገቡ “ቀይ መሥመሮች” መኖራቸውን ግን አጽንኦት ሰጥተዋል። “ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የሚከፋፍል፣ የሀገራችንን ክብርና ሉዓላዊነት የሚጥስና የግዛት አንድነታችንን ለአደጋ የሚያጋልጥ ማንኛውም መፍትሔ ተቀባይነት የለውም። የክህደትና የክፍፍል መንገድን የሚከጅል ሁሉ፣ የኢትዮጵያውያን ክንድ መቅመሱ አይቀርም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው መግለጫቸው ማጠቃለያ የጠቀሷቸው መንግስታቸው ከድል ማግስት የሚከተላቸውን አራት መርሆዎች ነው። የመጀመሪያው መርህ “ድሉ እንዳይቀለበስ አድርገን በሁለንተናዊ መስክ መጠበቅ” ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “ድሉን በፖለቲካዊ እና ሰላማዊ መንገዶች እንዲቋጭ ማድረግ ነው”። 

ድሉን ለመጠበቅ እና ዘላቂ ለማድረግ እንዲቻል፤ ግጭቱ የፈጠረውን ውጥረት “በአሸናፊ ምሕረት ማርገብ” የሚለው የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለው ሶስተኛ መርህ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ከሚከተላቸው የመርሆዎች ዝርዝር ውስጥ በመጨረሻነት የተቀመጠው “ፍትሕ ማስፈን” ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ያጠፋ እንዲቀጣ፣ የበደለ እንዲክስ የሚያደርግ” ያሉትን ፍትሕ፤ ሃገራዊ ባህሎችን እና እሴቶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንደሚያሰፍኑ በዛሬው መግለጫቸው ቃል ገብተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)