መንግስት የግለሰቦችን ክስ አቋርጦ እንዲፈቱ የወሰነው፤ “ኢትዮጵያን በዘላቂነት ለማቆየት እና ለማጽናት” መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ መንግስት በእስር ላይ የሚገኙ ግለሰቦችን ክስ አቋርጦ እንዲፈቱ ውሳኔ ያሳለፈው “ኢትዮጵያን በጠንካራ አለት ላይ ለማኖር፣ ጠላቶቿን ለመቀነስ እና ጉልበት ለመሰብሰብ” መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። “ጉዳዩን እኛም መጀመሪያ ስንሰማው” አስደንግጦናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሆኖም ውሳኔው “ለኢትዮጵያ የሚበጅ፣ ዘላቂ ጥቅም የሚያግዝ፣ በአውደ ውጊያ የተገኘውን ድል በሰላሙ መድረክ እንዲደገም የሚያደርግ” በመሆኑ “እየመረረን የዋጥነው እውነት ነው” ብለዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ እሁድ ጥር 1፤ 2014 በተካሄደው የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት ምረቃ እና ለጦር ጀግኖች የሜዳሊያ ሽልማት አሰጣጥ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚሁ ንግግራቸው “የተሸነፉ” ሲሉ የጠሯቸው ኃይሎች ክስ ተቋርጦ ከእስር ቤት እንዲወጡ ሲደረግ “በሁለት ቡድኖች” ዘንድ “ከፍተኛ ቁጣ” መቀስቀሱን ገልጸዋል። 

የመጀመሪያው ቡድን “ኢትዮጵያ ውስጥ ጭር ሲል የማይወድ” እና “ሁልጊዜ እያጋጨ በሰበር ዜና ብር የሚሰበስብ” እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አንስተዋል። ይህ ቡድን “የት እንዳለ እንደማይታወቅ” የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሆኖም “ካለበት ሆኖ ስንዋጋ ‘ጦርነት አቁሙ’ የሚል፣ ስናቆም ‘ተዋጉ’ የሚል ነው” ብለዋል። ቡድኑን “አጓጉል ብልጣብልጥነት የሚያጠቃው” ሲሉ የገለጹት አብይ፤ ለዚህም መንግስታቸው “እምብዛም ጆሮ” እንደማይሰጠው አስረድተዋል።

“ሁለተኛው ቡድን ግን በዜናው ድንገተኝነት የደነገጠ፣ በነበረው ተጋድሎ እና ሁኔታ ጊዜውን፣ ገንዘቡን እና ህይወቱን ለመስጠት የወሰነ፣ ከያለበት ሀገር እና ክልል ተምሞ ከሀገር እና ከህዝብ ጋር የዘመተ፣ ይህንን እኩይ ጠላጥ አምርሮ የሚጠላ እና ከዚህ እኩይ ጠላት ጋር የሚደረግ ማንኛውም ንግግር ኢትዮጵያን ይጎዳል ብሎ የሚያምን ቅን ተቆጭ ነው” ብለዋል። የዚህን ቡድን ሀሳብ “መንግስት ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳ እና እንደሚያደምጥ” የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ያለውን እውነታ ለማስገንዘብም ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። 

“እነዚህ ቅን ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፣ በውስጥም፣ በውጭም የሚገኙ፣ የአንዳንዶችን ‘ከእኛ ይቅር ማለት’ አምርረው የጠሉ እና የደነገጡ ወንድምና እህቶቻችን እንዲገነዘቡልን የምንፈልገው ይህ ጉዳይ እኛም መጀመሪያ ስንሰማው ያስደነገጠን መሆኑን ነው። ነገር ግን ደጋግመን ስናመነዥገው፣ ግራ ቀኙን ስንፈትሽ፤ ለኢትዮጵያ የሚበጅ፣ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም የሚያግዝ፣ የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ ጠላቶች የሚቀንስ፣ በአውደ ውጊያ ያገኘነውን ድል በሰላሙ መድረክ እንድንደግም የሚያደርግ፣ የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን የሚያረጋግጥ በመሆኑ እየመረርን የዋጥነው እውነት ነውና እናንተም ለሀገራችሁ ዘላቂ ድል ስትሉ፣ ለሀገራችሁ ክብር እና አሸናፊነት ስትሉ ደጋግማችሁ በማሰብ ይህንን ውሳኔ እንድትቀበሉ በትህትና እጠይቃችኋለሁ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ።

የኢትዮጵያ መንግስት ከትላንት በስቲያ አርብ ታህሳስ 29፤ 2014 ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ስር ያሉ 20 ተከሳሾች እና በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ ስር ያሉ አራት ተከሳሾች ክሳቸው እንዲነሳ መደረጉን ማስታወቁ ይታወሳል። በተመሳሳይ ሁኔታ በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መዝገብ ክስ ከቀረበባቸው 62 ግለሰቦች እና ድርጅቶች ውስጥ የስድስት ግለሰቦች ክስ እንዲነሳ መደረጉ በወቅቱ ተገልጿል።

የጤና እና የዕድሜ ሁኔታቸውን ከግምት በማስገባት” ክሳቸው እንዲነሳላቸው የተደረጉት አቶ ስብሐት ነጋ፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ፣ አቶ ዓባይ ወልዱ፣ አቶ አባዲ ዘሙ፣ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር እና ወ/ሮ ኪሮስ ሐጎስ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬ ንግግራቸው የግለሰቦቹን ማንነት በስም ባይጠቅሱም የተጠቀሟቸው ገለጻዎች የህወሓት አመራሮችን የሚመለከቱ ነበሩ።

“ክስ አቋርጠን ከእስር ቤት እንዲፈቱ ያደረግናቸው ግለሰቦች ሁሉም በሚባል ደረጃ የመንግስት ስልጣን ይዘው በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተሳተፉ፣ በቀጥታ የሚወስኑ፣ በቀጥታ የሚያዝዙ አይደሉም። አንዳንዶች በታሪካቸው ምክንያት አግዝፈን የምናያቸው ቢሆንም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከሁሉም የውሳኔ ሰጪነት መድረክ በቀጥታ የማይሳተፉ ኃይሎች ናቸው። ከዚህም በላይ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን እና ጀግንነታችን ሽማግሌዎች በእስር ቤት እንዲሞቱ የሚፈልግ፣ የሚፈቅድ አይደለምና፤ ጀግኖች ስለሆንን አዛውንቶች ሲቻል ወደ ገዳም አሊያም ወደቤታቸው እንጂ በእስር ቤት እንዳይቆዩ ወስነናል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግለሰቦቹ የመፈታት ውሳኔ ጋር በተገናኘ ደጋግመው ሲጠቅሱት የተደመጠው ነገር “ኢትዮጵያን የማጽናት” ጉዳይ ነው። የእስረኞቹ መለቀቅ ጉዳይ “በድንገት ሲሰማ ለመቀበል የሚያስቸግር” መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ውሳኔው የተላለፈው “ኢትዮጵያን በዘላቂነት የሚያቆይ፣ የሚያጸና፣ የሚያስማማ ሆኖ” ስለተገኘ መሆኑን አስረድተዋል። “እያንዳንዱ ውሳኔ በመንግስት ሲወሰን “አርቆ በማሰብ እና ኢትዮጵያን በማጽናት ብቻ ላይ የሚመሰረት መሆኑንም” አስገዝበዋል። 

“በዚህ ጉዳይ ያዘኑ፣ የተቆጡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እንዲገነዘቡ የምፈልገው ነገር…ዋናው አላማ የምትወዷትን ሀገር ኢትዮጵያ አንድ አድርገን ለማጽናት ካለን ፍላጎት ብቻ የመነጨ መሆኑን እንድትገነዘቡ፤ ቢያንስ ቢያንስ ጉቦ በልተን እንዳለቀቅናቸው እንድታስቡ ላሳስባችሁ እፈልጋለሁ” ሲሉ ውሳኔው የተላለፈው የሀገርን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ መሆኑን አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[ይህ ዘገባ ዘግየት ብሎ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]