የቀድሞ የፓርላማ አባላት በመንግስት ከተሰጣቸው ቤት እንዲወጡ የተላለፈው ትዕዛዝ በፍርድ ቤት ታገደ

በሃሚድ አወል

ተሰናባች የፓርላማ አባላት እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ በመንግስት ከተሰጣቸው ቤት እንዲወጡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተቀመጠው ቀነ ገደብ በፍርድ ቤት ታገደ።  የእግድ ትዕዛዙን ባለፈው ሐሙስ ታህሳስ 28፤ 2014 ያስተላለፈው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ነው። 

የከፍተኛው ፍርድ ቤት እግዱን ያስተላለፈው 163 የቀድሞ የፓርላማ አባላት ያቀረቡትን አቤቱታ ከመረመረ በኋላ ነው። ተሰናባች የፓርላማ አባላቱ አቤቱታውን ለማቅረብ ምክንያት የሆናቸው በምክር ቤት አባልነታቸው የተሰጣቸውን ቤት እስከ ታህሳስ 30 እንዲያስረክቡ በደብዳቤ መታዘዛቸውን ተከትሎ ነው። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ደብዳቤውን የጻፈው ባለፈው ሰኞ ታህሳስ 25 ነበር። የቀድሞ ፓርላማ አባላቱ ባቋቋሙት ኮሚቴ አማካኝነት ጉዳዩን ከአንድ ቀን በኋላ ወደ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ወስደውታል። አቤቱታው የቀረበለት የከፍተኛው ፍርድ ቤትም፤ ይግባኝ ባዮች ከቤት ለቅቀው እንዲወጡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተጻፈው ደብዳቤ “ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ” ታግዶ እንዲቆይ ትዕዛዝ ሰጥቷል። 

ተሰናባች የፓርላማ አባላቱ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያሉት፤ ጉዳያቸውን መጀመሪያ የተመለከተው የስር ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን ቅር በመሰኘት ነው። የፓርላማ አባላት ጉዳዩን ለስር ፍርድ ቤት ባስገቡት ማመልከቻ፤ በአዋጅ የተሰጣቸው መብት ሳይከበር በመንግስት ከተሰጣቸው ቤት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ልቀቁ መባላቸው አግባብ ባለመሆኑ ትዕዛዙን ያስተላለፈው የተወካዮች ምክር ቤት በፍርድ ቤት ቀርቦ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።   

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት “እኔ መልስ መስጠት አይጠበቅብኝም። ጉዳዩ የአስፈጻሚው አካል ነው” ብሎ መከራከሩን ጉዳዩን የተከታተሉ አንድ የቀድሞ የፓርላማ አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ተናግረዋል። የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ልዩ ልዩ ችሎት ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ በሰጠው ውሳኔም፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ “መልስ መስጠት አይጠበቅበትም” ሲል ውሳኔ አስተላልፎ እንደነበር ገልጸዋል። 

ተሰናባች የፓርላማ አባላት “ሊከበርልን ይገባል” በሚል በፍርድ ቤት ማመልከቻቸው የጠቀሱት መብት፤ ከኃላፊነት የተነሱ የሀገርና መንግስት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞችን መብት እና ጥቅም ለመወሰን በወጣው አዋጅ የተካተተው ነው። በአዋጁ መሰረት ሁለት የምርጫ ዘመን ወይም ከዚያ በላይ ላገለገሉ የፓርላማ አባላት ኪራይ እየከፈሉ የሚገለገሉበት መኖሪያ እንደሚሰጣቸው ተደንጓል። 

አዋጁን በማጣቀስ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱት 163 የቀድሞ የፓርላማ አባላትም፤ ለሁለት እና ከሁለት ዙር በላይ በተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ያገለገሉ ናቸው። ከእነዚህ አቤቱታ አቅራቢ የፓርላማ አባላት አንዱ የሆኑት የደቡብ ክልል ተወካይ፤ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት በኪራይ የሚሰጥ ቤት ባለመኖሩ ምክንያት፤ አባላቱ የ40/60 ኮንዶሚኒየም ቤቶች እንዲሰጣቸው በመንግስት ተወስኖ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ለፓርላማ አባላቱ “ሰልፍ ተስተካክሎ” ቤቱ እንዲሰጣቸው የተወሰነላቸው፤ የኮንዶሚኒየም ቤቶቹን ለማግኘት ገንዘብ ሲቆጥቡ ስለነበር መሆኑንም ገልጸዋል። 

የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለማግኘት ገንዘብ ሲቆጥቡ የነበሩ ሆኖም ለአንድ ዙር ብቻ በምክር ቤት አባልነት ላገለገሉ የምክር ቤት አባላት ደግሞ የ20/80 ኮንዶሚኒየም ቤቶች እንዲሰጣቸው ተወስኖ እንደነበር አስታውሰዋል። የገዢው ፓርቲ ተወካዮች የነበሩት እነዚህ የፓርላማ አባላት “የመንግስትን ጫና ለመቀነስ” በሃሳቡ ተስማምተው እንደነበርም አስረድተዋል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንደተናገሩት፤ ተሰናባች የፓርላማ አባላቱ በዕጣ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ቢሰጣቸውም “ለመኖሪያ ምቹ አይደሉም” በሚል ምክንያት ሊገቡባቸው አልቻሉም

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንደተናገሩት፤ ተሰናባች የፓርላማ አባላቱ በዕጣ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ቢሰጣቸውም “ለመኖሪያ ምቹ አይደሉም” በሚል ምክንያት ሊገቡባቸው አልቻሉም። ከተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ጋር የተካሰሱት 163ቱ የፓርላማ አባላት፤ መንግስት በአዋጁ መሰረት የሚጠበቅበትን ቤት እንዲያመቻች ወይም በዕጣ የደረሳቸውን ኮንዶሚኒየም እንዲያስጨርስ ሲሉ ጥያቄ ማቅረባቸውንም ገልጸዋል። 

ከኦሮሚያ ክልል ተወክለው ለሁለት ዙር ያገለገሉ አንዲት የፓርላማ አባል፤  “በጣም እየተከራከርን ነው። ቤትም የለንም። ሜዳ ላይ ልንወድቅ ነው” ሲሉ መንግስት ኃላፊነቱን ካልተወጣ አሁን የሚኖሩበትን ቤት እንደማያስረክቡ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሌላ አንድ የቀድሞው የተወካዮች ምክር ቤት አባልም በተመሳሳይ በአዋጁ ላይ የተደነገገው የጥቅም መብት ካልተከበረ፤ በመንግስት የተሰጣቸውን ቤት አላስረክብም ብለዋል።

የቀድሞ የፓርላማ አባላት ጥቅማ ጥቅም መከበር ጉዳይን በተመለከተ ስለሚነሱ ጥያቄዎች “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ከአንድ ወር በፊት በደብዳቤ ጥያቄ ብታቀርብም፤ እስካሁን ምላሽ አላገኘችም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)