ከሶስት ቀናት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችን ክስ በማቋረጥ እንዲፈቱ ማድረጉ የሰሞኑ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል። ይህ የመንግስት እርምጃ ይፋ ከሆነበት ካለፈው አርብ ታህሳስ 29 እስከ ዛሬ ማክሰኞ ድረስ ባሉት ተከታታይ ቀናት፤ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሞ እና ድጋፋቸውን፣ ምክር እና ማሳሰቢያቸውን ለመንግስት እና ለደጋፊዎቻቸው አቅርበዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ባወጣቿው መግለጫዎች ከግለሰቦቹ ፍቺ በተጨማሪ በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተስፋ እና ስጋታቸውን ገልጸዋል። መግለጫዎቹ ከዳሰሷቸው ፖለቲካዊ ጉዳዮች መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት እና በአገሪቱ ሊካሄድ የታቀደው ሀገራዊ ምክክር ይገኙባቸዋል።
የህወሓት የቀድሞ መሪ አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ በጦር ምርኮ ተይዘው የታሰሩ ስድስት የፓርቲው የቀድሞ አመራሮች እንዲፈቱ መወሰኑ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እንዲሁም ከእናት ፓርቲ የበረታ ተቃውሞ ገጥሞታል።
አብን ከትላንት በስቲያ እሁድ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት “በሀገሪቱ ፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጀው ድርጅት ቁንጮ አመራሮችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና ማብራሪያ ከእስር በመፍታት፤ የሀገር እና የህዝብን ጥቅምና ክብር በፅኑ የሚጎዳ ታላቅ ታሪካዊ ስህተት ፈጽሟል” በማለት ተቃውሟል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን መንግስት እርምጃ “በይቅርታ እና በሰብአዊነት ስም የተፈፀመ ኢ-ሰብአዊና ኢ-ፍትሃዊ ውሳኔ” በማለት የገለጸው አብን፤ ውሳኔው “በኢትዮጵያውያን ለሀገር ህልውና የተከፈለውን መስዋዕትነት ዋጋ የሚያሳጣ” ብሎታል። ፓርቲው “ግብታዊ እና ኢ-ፍትሃዊ” ያለውን ይህን ውሳኔ “በመንግስት ህጋዊ እና ሞራላዊ መሰረት ላይ እየጎሉ የመጡ ክፍተቶችን የሚያረጋግጥ፤ በመንግሥትና በህዝብ መካከል በየጊዜው እየጨመረ የመጣው ርቀትና ያለመተማመን የሚያጎላ” መሆኑን በመግለጫው ጠቁሟል።
እንደ አብን ሁሉ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካቢኔ ወንበር የተሰጠው ኢዜማም፤ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በኩል ባለፈው እሁድ ባወጣው መግለጫ ተመሳሳይ አቋም አራምዷል። ፖለቲከኞቹ የተመሠረተባቸው ክስ ተቋርጦ ከእስር የተለቀቁት “በእነሱ አነሳሽነት የተቀጠፉ ህይወቶች ቁስል ባልሻረበት እና የወደሙ አካባቢዎች እስካሁን ባላገገሙበት ሁኔታ” መሆኑን የገለጸው ኢዜማ፤ በኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ ላይ ተቃውሞ አቅርቧል።
ውሳኔውን “ከሕዝብ ጋር ምክክር የጎደለው ግብታዊ እርምጃ” በማለት የገለጸው ኢዜማ “ተበዳይ ፍትህ ሳያገኝ እንዲሁም ሳይካስ በዳይን ነፃ ማውጣት በፍትህ ስርዓቱ መቀለድ፣ የሕዝባችንን ጉዳትም ማቃለል ነው” በማለት በጥድፊያ የሚደረጉ ውሳኔዎች ፍትህን በመጨፍለቅ የተቋማቱን ተአማኒነት በሒደት እንደሚሸረሽሩ ገልጿል። የኢዜማ መግለጫ እንደሚለው ውሳኔው “አመፀኝነትን የሚያበረታ እና መከፋፈልን የሚያጠነክር እጅጉን አሳሳቢ ተግባር ነው።”
እናት ፓርቲ በበኩሉ “በሽብርተኛነት የተፈረጀ ድርጅት መስራች እና ዘዋሪዎች” ሲል የገለጻቸው ግለሰቦች ክስ መቋረጥ “ህጋዊ ሂደትን ያልጠበቀ” ነው ሲል ተቃውሞታል። ፓርቲው ውሳኔው ይፋ በሆነ ማግስት ባወጣው መግለጫ ክስ እንዲቋረጥ እና ፖለቲከኞቹ ከእስር እንዲፈቱ “የጤና እና የዕድሜ ሁኔታ” እንደ መመዘኛ መቅረቡ “ማታለያ እና ውሃ የማይቋጥር ምክንያት” ሲል አጣጥሎታል።
ፓርቲው ኢትዮጵያውያን ቁስላቸው ሳያገግም፣ ቁጣቸው ሳይበርድ እና ከሀዘናቸው ሳይጽናኑ ተወሰነ ያለውን ውሳኔ “የፓርቲውን አምባገነንነት የሚያሳይ” ነው ብሎታል። “የህግ አሰራርን የጣሰ፣ በግለሰቦችና ገዢው ፓርቲ ፍላጎት ብቻ የሚታሰሩበት እና የሚፈቱበት መሆኑን ማሳያ ነው” በማለትም ነቅፎታል።
መንግስት በርከት ያሉ ፖለቲከኞችን ከእስር ለመፍታት መወሰኑን ይፋ ሲያደርግ “የኢትዮጵያን ችግሮች ሰላማዊ በሆነ፣ ከእልህ እና ከመጠፋፋት በራቀ ሁኔታ፣ በሀገራዊ ምክክር በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል መንገድ” መክፈት አንዱ ዓላማው መሆኑን አስታውቆ ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊውን ውይይት “ለሀገር በአጠቃላይ እርቅና ሰላምን ከማምጣት አኳያ በጉጉት እንደሚጠብቀው” የገለጸው እናት ፓርቲ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ፖለቲከኞች የፈታበትን ውሳኔ የጣልቃ ገብነት ማሳያ አድርጎ አቅርቦታል።
“የህግ አሰራርን ወደ ጎን በመተው በስሜትና በማን አለብኝነት የሚወሰኑ ውሳኔዎች” ኢትዮጵያን “አሁን ካለችበት ሁኔታ ወደ ከፋ አዘቅት” ሊወስዳት ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው ፓርቲው በአንክሮ ገልጿል። “እንዲህ ያሉ አላስፈላጊ ጣልቃ-ገብነቶች የሚኖሩ ከሆነ ውጤቱ ከነበረው የተለየ እንደማይሆን አንድ ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል” ያለው እናት ፓርቲ፤ “አስፈጻሚው አካልም በሕግ የተገደበ ሥልጣኑን ብቻ እንዲወጣ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እና ሊካሄድ የታቀደው ብሔራዊ ውይይት “ተደበላልቀው ሊሄዱ አይገባም” የሚል አቋም ያለው ኢዜማ፤ “ሁለቱን ጉዳዮች አጣብቆ ማምጣት መንግሥት ሆን ብሎ እየተከተለው ያለ መንገድ መሆኑ” በግልጽ እንደታየ ገልጿል። ብሔራዊው ውይይት “ለዘመናት የቆዩ ችግሮቻችንን ጭምር የምንፈታበት በመሆኑ ይህ በዘመናት አንዴ የሚገኝን ዕድል ወቅታዊ ችግሮችን ብቻ እንዲፈታ አድርጎ መጠምዘዝ ከትርፉ ኪሳራው ያመዝናል” ሲል ፓርቲው በመንግስት አካሄድ እንደማይስማማ አሳውቋል።
የመንግስት አካሄድ በኢትዮጵያ ውስጥ “በተደጋጋሚ መጥተው የከሸፉ የለውጥ ጭላንጭሎችን ዕጣ-ፈንታ መልሶ ከመድገም ውጪ የሚያመጣው ዘላቂ ጥቅም አይኖርም” ሲል ኢዜማ ነቅፏል። በሀገራዊው ምክክር የተሳታፊዎችን ማንነት እና አጀንዳዎች የመወሰን ስልጣን በቅርቡ ለተቋቋመው ኮሚሽን የተሰጠ መሆኑን ያስታወሰው ፓርቲው፤ “መንግሥት በቅርቡ ከእስር የፈታኋቸውን ሰዎች የፈታኋቸው፤ ‘በሀገራዊው ምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ ነው’ በማለት ከወዲሁ ተሳታፊዎቹን እየመለመለ ይገኛል” በማለት ተችቷል።
ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በአንጻሩ የኢትዮጵያ መንግስትን ውሳኔ በአዎንታዊ መንገድ ተቀብሏል። ፓርቲው “እውነተኛ ሀገራዊ ምክክር እና መግባባት የፖለቲካ እስረኞች በእስር ቤት ባሉበት” እንዲሁም በአንደኛው የኢትዮጵያ ጫፍ “አውዳሚ ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ ሊካሄድ አይችልም” የሚል አቋም እንዳለው ትላንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ አሳውቋል። መንግስት “ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት የወሰደው እርምጃ” ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ የሚከፍሉትን ዋጋ ለማስቆም እንዲሁም ፖለቲካዊ መረጋጋት ለመፍጠር ካለው ፋይዳ ባሻገር “ሊካሄድ ለታሰበው ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት አዎንታዊ ሚና” እንዳለው ፓርቲው ገልጿል።
ከእስር የተፈቱት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮች ዛሬ ማክሰኞ ጥር 3 ቀን ባወጡት መግለጫም በኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት “አሳዛኝ እና አውዳሚ” ሲሉ በተመሳሳይ መልኩ ገልጸውታል። “በአውዳሚው ጦርነት የተጎዱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን መከራ እና ያስከተለውን ሰብዓዊ ቀውስ” ይከታተሉ እንደነበር የጠቀሱት የኦፌኮ አመራሮች “ሀገራችን ከውድቀት አፋፍ ስትደርስ እና ማህበራዊው መስተጋብር ሲበጣጠስ ከእስር ቤት ክፍላችን በጭንቀት ከማልቀስ እና ለተሻለ ቀን ይመጣ ዘንድ ከመጸለይ ውጪ አማራጭ አልነበረንም” ብለዋል።
አስራ ሶስት ወራት የዘለቀው “የእርስ በርስ ጦርነት” በኢትዮጵያ እና በዜጎቿ ላይ ያደረሰውን ውድመት ለመቀልበስ ጊዜው እጅግ መዘግየቱን የገለጹት የኦፌኮ አመራሮች፤ የመንግስት ድምጸት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከግጭት እና ግብግብ ይልቅ ወደ ሰላም እና እርቅ መቀየሩን አድንቀዋል። “እነዚህን አበረታች ተስፋዎች ተጨባጭ እና የማይቀለበሱ እርምጃዎች ሊከተሉት” እንደሚገባም ገልጸዋል።
አቶ ጃዋር መሐመድ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ባለፈው ቅዳሜ ከእስር የተፈቱ የኦፌኮ አመራሮች የሰሜን ኢትዮጵያውን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚታዩ ግጭቶች እንዴት ይቋጩ በሚለው ረገድ ያላቸውን አቋም ይፋ አድርገዋል። እነ ጃዋር በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና በትግራይ እየተካሄዱ በሚገኙ ጦርነቶች የሚሳተፉ ወገኖች በሰላም እና በድርድር መፍትሔ እንዲያበጁ ጥሪ አቅርበዋል።
የኦፌኮ አመራሮች ጥሪ በድርድር አጠቃላይ የተኩስ አቁም ላይ እስኪደረስ፤ ውጊያ የገጠሙ ኃይሎች የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት፣ ንብረት እና መሠረተ-ልማት እንዲጠብቁ የሚለውን ያካተተ ነው። “ጦርነት ለኢትዮጵያ ውስብስብ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሔ አይደለም” ያሉት የፓርቲው አመራሮች፤ ለአብዛኞቹ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች የአስራ ሶስቱ ወራት ክስተት ይህን እውነታ ግልጽ አድርጎላቸዋል የሚል እምነት እንዳላቸው በመግለጫቸው ጠቁመዋል። በኦፌኮ አመራሮች እምነት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው “በብሔር እና ብሔረሰቦች መካከል በሚደረግ ሐቀኛ ድርድር እና ውይይት ብቻ” ነው።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የደረሰበትን ምዕራፍ በተመለከተ ኢዜማ እና አብን ከኦፌኮም ሆነ ከመንግስት የተለያየ አተያይ እንዳላቸው መግለጫዎቻቸው ይጠቁማሉ። አብን “መንግስትና ገዥው ፓርቲ ጦርነቱ በአሸናፊነት እንደ ተደመደመ፣ የህልውና አደጋው እንደተቀረፈ” አድርገው እያቀረቡ ነው የሚል ትችት ሰንዝሯል።
ይህን ትችት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የሚመሩት የኢዜማ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚጋራው ነው። ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው “ጦርነቱ አንዳለቀ ተደርጎ መቅረቡ” ሊታረም የሚገባው እንደሆነ ገልጿል። አብን “ህዝባችንም ለአፍታም ቢሆን ሳይዘናጋ በሁሉም አውደ ግንባሮች የሚያደርገውን ፍልሚያ አጠናክሮ እንዲቀጥል” የሚል ጥሪ ሲያቀርብ፤ ኢዜማ በበኩሉ “አሁንም ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በንቃት መጠበቅ ላይ ሊተኮር ይገባል” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)